>
5:21 pm - Sunday July 21, 4576

የዶክተር በያን አሶባ ጆኒያ ሙሉ ውሸትና ኦነጋዊ የፈጠራ ትርክት ...!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

የዶክተር በያን አሶባ ጆኒያ ሙሉ ውሸትና ኦነጋዊ የፈጠራ ትርክት …!!!
አቻምየለህ ታምሩ

እሬቻ ቃሉ አማርኛ፣ ባሕሉም የገርባ እንጂ የትክክለኛው ኦሮሞ የቦረና አለመሆኑን፤ የገዳ ሥርዓት የባንቱ እንጂ የኦሮሞ ሥርዓት አለመሆኑን፤ ኦሮሞ የገዳ ሥርዓትን የወረሰው ከባንቱ መሆኑን የታሪክ ምንጮችን ጠቅሼ በጻፍዃቸው ጥናቶች ጥንቢራቸው እስኪዞር ድረስ በጥላቻ ከሰከሩ፣ ጺማቸውን እየነጩ ጨጓራቸው ከተቃጠለባቸውና ነርቫቸው ከተነካባቸው ኦነጋውያን መካከል ዶክተር Beyan H. Asoba አንዱ ነው። ስለ እሬቻና ገዳ ምንነትና የማንነት በበቂ ሁኔታ ማስረጃዎችን ስላቀረብሁ በዛሬው እለት የማቀርበው ጽሑፍ ስለ እሬቻና ገዳ የታሪክ ምንጮችን ዋቢ አድርጌ በመጻፌ የኦሮሞ ጥላቻ እንዳለብኝ የከሰሰኝ ዶክተር በያን አሶባ በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ክፍል ቀርቦ ያስተጋባውን ኦነጋዊ የፈጠራ ትርክት እሱ ራሱ ሊያጣቅስ በሄደው የታሪክ ማስረጃ ላይ ብቻ በመመስረት እውነታው ምን እንደሚመስል ለተከታይ እናቀርባለን!
አሜሪካን አገር የሚኖረው ዶክተር በያን አሶባ ፖለቲካ የጀመረው  የደርግ ካድሬ በመሆን ነበር። በደርግ ካድሬነቱ ከኢትዮጵያ እስከ አውሮፓ የሰራውን ስራ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። ደርግ ከወደቀ በኋላ ደግሞ ኦነጋዊ አሰላለፉን ይፋ አድርጎ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በኦነግና ቅርንጫፎቹ  እየተዘዋወረ አመራር ሆኖ ሰርቷል። ዶክተር በያን ባለፉት ዓመታት ደግሞ ከሌንጮ ለታና ዲማ ነገዖ ጋር በመሆን ኦዴግ የሚባል ድርጅት መስርተው ዐቢይ አሕመድ በአገዛዙ መንበር እስኪሰየም ድረስ የዲያስፖራ ታጋይ ነበር።
በዚህ ጽሑፍ የማቀርበው ትችት የኦዴግ አመራር አባል የሆነው ዶክተር በያን አሶባ በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የአማርኛው ክፍል ቀርቦ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ «አከራካሪ ጉዳዮች» ተብለው በቀረቡት ቅራቅንቦዎቹ ዙሪያ  ከሁለት ፕሮፈሰሮች ጋር በጋዜጠኛ ትዝታ በላቸው አጋፋሪነት ሲወያይ ያነሳቸውን የፖለቲካቸው መሰረቶች ነው።
ዶክተር በያን አሶባ  ከታች በሚሰማው ድምጽ ላይ በአሜሪካ ድምጽ ቀርቦ የክርክሩን ጭብጥ ባስቀመጠበት የመግቢያ ንግግሩ ለኦነግና ለሎች ተገንጣይ የዘር ድርጅቶች ትግል መነሻ የሆናቸው ያለውን  «የብሔረሰብ ጭቆና » ትርክት  ከተረተረ በኋላ የብሔር ጭቆና ተብዮውን ያሳያል ያለውን ዋና ማሳያ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፤
«የአጼ ምኒልክ ወረራ ሁለት ሕዝቦችን ነው ኢትዮጵያ ውስጥ የፈጠረው፤ ለዚህ መረጃ የመጀመሪያው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግሥት ሲሰራ፤ ኢትዮጵያዊ ማነው? ለሚለው ጥያቄ የመጀመሪያው አንቀጽ ነው መልስ የሰጠው። ያ ሕገ መንግስት. . . ምንድን ነው የሚለው ኢትዮጵያ ከሁለት ሕዝቦች ነው የምትመሰረተው፤ በእንግሊዝኛ ቋንቋ Natives ከሚባሉትና subjects የሚባሉት በጋራ ነው የኢትዮጵያን ህዝብ የሚመሰርቱት ይላል»
ዶክተር በያን በዚህም አላበቃም። ኦነጋዊነት በሰጠው ድፍረት እየተመካ መተርተሩን በመቀጠል «በአንድ አገር ውስጥ Native የሚለውን National ወይንም ዜጋ እንበለው፤ subjects የምንላቸው ደግሞ ዜጋ ያልሆኑ ወይንም ከዜጋ ያነሰ መብት ያላቸው እንደማለት ነው።» ሲል ይቀደዳል።
ቀጠል አድርጎም  ከጓዶቹ ጋር ሆኖ ኦነግን መስርተው ለመገንጠል እንዲታገሉ ያደረጋቸውን መነሾ ሲያስረዱ እንዲህ ይላል፤
«ይሄ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሕዝቦች ከመንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት [ሕገ መንግሥቱ ዜጋ የሆነና ዜጋ ያልሆነ ይላል ያለውን  ማለቱ  ነው]፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸው status [ደረጃ] ነው የሚያታግለን»
ልብ በሉ! ዶክተር በያን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ነገዶች ስለመጨቆናቸው ማስረጃ አድርጎ የጠቀሰው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ አንድን ነው።  ኦነጋውያን ነጻ አውጪ ድርጅት መስርተው እንዲታገሉ አደረጋቸው ያለውም ይህን “ዜጋ የሆኑና ዜጋ ያልሆኑ” በሚል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ አንድ ላይ ተጸፎ ይገኛል ያለው የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ነው።
ዶክተር በያን አሶባ የሕግ «ምሁር» እንደሆነ  በቃለ መጠይቁ መግቢያ ላይ ተጠቅሷል። ሆኖም ግን በኛ አገር የግራ ፖለቲከኞች ዘንድ «ምሁርነት» ማለት ለፖለቲካ መጠቀሚያ የሚንጠለጠል ማዕረግ እንጂ ማገናዘብን፣ ማመሳከርንና ማጣራትን፤ ደግሞ ደጋግሞ መፈተሽን የሚጨምር አይመስልም። በአገራችን የግራ ፖለቲከኞች ዘንድ ምሁርነት የእንጀራ መበያ ካባና የሕዝብ ማታለያ ጭንብል እንጂ የእውነት ማጣሪያ ልቀት [የexcellence ደረጃ] አይደለም። ያገራችን የግራ ፖለቲከኛ ምሁራን እግራቸውን አስንተው ሲዋሹ፤ የፈጠራ ታሪክ እያመረቱና መጽሐፍ ሲደርቱ ለፖለቲካ እስከ ጠቀማቸው ድረስ የኅሊናም ሆነ የሞያዊ ስነ ምንግባር ልጓም የላቸውም።
ዶክተር በያን አሶባና የትግል ጓዶቹ  ኦነጋውያን ላለፉት አርባ ሰባት ዓመታት ኦነግን እየመሩ ሲታገሉና ሲያታግሉ፤ የውሸት ሮፓጋንዳ ሲሰሩ የኖሩት «የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝቦች ዜናጋ ዜጋ ያልሆኑ በሚል ስለሚከፍል፤ ኦሮሞ በሕገ መንግሥቱ የዜግነት status ስላልተሰጠው፤ የራሳቸውን አገር መስርተን ኦሮሞ የዜግነት status እንዲኖረው እናድርግ» በሚል ራሳቸው በፈጠሩት ተረት ላይ ተመስርተው ነው። ሰው እየተማረ ሲሄድ በአስተሳሰብና በስብዕው ላይ የአመዛዛኝነትና የኃላፊነት ስሜት ነው አብሮ እያደገ ይሄዳል። ባገራችን ግራ ፖለቲካ ኩሸት የተፈጠሩት የአገራችን የዘር ፖለቲከኞች ግን እየተማሩ ሲሄዱ የሚያገኙትን የዶክተርነትና ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የአመዛዛኝነታቸው መለኪያ ሳይሆን የፈጠራ ታሪካቸው ለማስረጽ የሚጠለቅ ክታብ አድርገው ያንሱበታል።
እስቲ ዶሴው ይውጣና እውነቱ ዶክተር በያን አሶባ ካስተጋባው ትርክት አኳያ ምን እንደሚመስል ይታይ። በ1923 ዓ.ም. የጸደቀው የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት አንቀጽ አንድ እንደሚከተለው ይነበባል. . .
«የኢትዮጵያ መሬት፡ ከወሰን እስከ ወሰን በሙሉ የንጉሰ ነገሥት መንግሥት ነው። በንጉሠ ነገሥት ግዛር ውስጥ በዜግነት የሚኖር የኢትዮጵያ ተወላጅ ሁሉ ባንድነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።»
ዶክተር በያን አሶባ በ1923 ዓ.ም. የጸደቀው የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ «ዜጋ የሆኑና ዜጋ ያልሆኑ» ወይንም «Native እና Subject» ይላል ያለውን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ አንድም ላይ ይሁን በተቀሩት አንቀጾች ላይ በመብራት ስንፈልግ ብንውል አናገኘውም። ዶክተር በያን ሕገ መንግሥቱ «ዜጋ የሆኑና ዜጋ ያልሆኑ» ወይንም «Native እና Subject» ይላል ያለው የኦነግ ፍጹም ፈጠራ እንጂ በሕገ መንግሥቱ የመጀመሪያው አንቀጽ ላይ እንደዚያ የሚል አገላለጽ የለም።
እኔ የሚገርመኝ የተማሩ ተብለው ዶክተርና ፕሮፌሰር እየተባሉ የሚጠሩ ፖለቲከኞች ሲናገሩና ሲጽፉ፤ እንደ ወረደ የሚቀበል እንጂ እያንዳንዷን ነገር በአንክሮ የሚከታተል፤ የሚመለከትንና የሚናገሩትንም ሆነ የሚጽፉትን ነገር የሚፈትሽ፤ መረጃና ማስረጃ አገላብጦ እውነቱን የሚያወጣና የሚሞግታቸው ሰው የሚኖር አይመስላቸውም።
እነዚህ የውሽት ታሪክ እየፈጠሩ ለማሰብ ፍቃደኛ ላልሆነው ጭፍን ተከታያቸው የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ የሚሰሩ የዘር ፖለቲከኞች እስከ ዛሬ ድረስ እግራቸውን እያነሱ ለተከታዮቻቸው ሲዋሿቸውና ሲያታልሏቸው ሲኖሩ ከተከታዮቻቸው መካከል አንድም ሰው ተነስቶ እንደሚንቋቸውና እንዴት እንደደብ እንደሚዩዋቸው ተገንዝቦ ሲያጋልጣቸው አለማየታችን ሁል ጊዜ ይደንቀኛል።
ዶክተር በያን አሶባ እንደነገረን ከትግል አጋሮቹ ጋር ሆኖ  ኦነግን መስርተው እንዲታገሉ ያስገደዳቸው በ1923 ዓ.ም. በአማርኛ ተጽፎ የጸደቀው የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት የመጀመሪያው አንቀጽ ላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ «ዜጋ የሆነና ዜጋ ያልሆነ» ተብሎ «መለያየቱ» ነበር ካለንና ከዚህ ሁኔታ ለመውጣት መፍትሔው የኦሮሞን ነጻ አገር መስርተው በአዲሱ አገር ውስጥ ኦሮሞን ዜጋ ለማድረግ መታገል ነው» ብለው ሕዝቡን ካደራጁና ካታገሉ፤ « የትግላችን መንስዔ ነው» በማለት በ1923 ዓ.ም. የጸደቀው «የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ «ዜጋ የሆኑና ዜጋ ያልሆኑ» ወይንም «Native እና Subject» ይከፍላል ያለው  ያልተጻፈ፣ ያልነበረና ደረቅ የፈጠራ ክስ ከሆነ ኦነግ የኦሮሞን መንግሥት ለመመስረት የታገለው ራሱ በፈጠረው የውሸት ትርክት ላይ ተመስርቶ ነው ማለት ነው። የዶክተር በያን ንግግር በማስረጃ ሲፈተሽ የምንደርስበት ድምዳሜ ቢኖር ይህ ብቻ ነው።
ከታች ከታተመው በ1923 ዓ.ም. የጸደቀው የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት ማየት እንደሚቻለው አንቀጽ አንድ ዶክተር በያን አሶባ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ሕዝብ «ዜጋ የሆኑና ዜጋ ያልሆኑ» ወይንም «Native እና Subject» ተብሎ አልተከፈለም። የሌላ ታሪክ ፈጥሮ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ «ዜጋ የሆኑና ዜጋ ያልሆኑ» ወይንም «Native እና Subject» ይላል በማለት በፈጠራ ክስ አንድ ሕዝብ ማታለልና መዋሸት የሚያሳየው ነገር ቢኖር ኦነጋውያን ለሚዋሹት ሕዝብ ያላቸውን ንቀት ብቻ ነው።
አንድ ሕዝብን የሚያከብር ድርጅት ሕዝብን ሆን ብሎ  አይዋሽም! በስህተት ከዋሸም የዋሸውን ሕዝብ ይቅርታ ይጠይቃል። ኦነግ ግን የኦሮሞን ሕዝብ ስለሚንቅ ያልተጻፈ የሕገ መንግሥት አንቀጽ እንደተጻፈ በማስመሰል በልብ ወለድ ፈጠራ ««የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝቦች ዜናጋ ዜጋ ያልሆኑ በሚል የኢትዮጵያን ሕዝብ ይከፍለዋል» እያለ ሲያስተጋባ ስለኖረው ውሸት የጠየቀው ይቅርታ የለም፤ ይልቁንም  ነጻ አወጣዋለሁ የሚለውን ሕዝብ ክብር አይገባውን ብሎ ስለሚያስብ ሕጻን ሳይቀር የሚሳለቅበትን ውሸት እያመረቱ ኦሮሞ ግን የምንነግረውን ሁሉ ሳይጠራጠር ያምነናል በሚለው ንቀታቸው እየተመሩ በአገሩ ላይ እንዲያምጽ ሲቀሰቅሱት ይውላሉ።
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ዶክተር በያን አሶባ እንደሚለው ሳይሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሁሉ የአንድ ቤተሰብ እኩል ዜጋ ከማድረጉ ባሻገር ኦነግ ባወጣው የመሬት ላራሹ አዋጅ የመሬት ባለቤትነት መብቱ ተነጥቆ የደርግና የወያኔ ጭሰኛ ከመሆኑ በፊት የኢትዮጵያን ገበሬ የግል የመሬት ባለቤትነት ያረጋገጠና በኢትዮጵያ ታሪክ ከተጻፉት ሕገ መንግሥቶቹ ሁሉ በተራማጅነቱ ታይቶ የማይታወቅ ሕገ መንግሥት ነበር።
እነ ዶክተር በያን አሶባ ግን ሁለት ጸጉር አብቅለው፤ በዲግሪ ላይ ዲግሪ ደርበው፤ የሰሩትን ደባና ያጠፉትን ጥፋት ለመሸፈን ሲሉ ብቻ ንግግራቸውንና ጽሑፋቸውን የሚመረምር ሰው ያለ ስለማይመስላቸው ከ47 ዓመታት በፊት አጀንዳ ያላቸው አላዋቂዎች የፈጠሩትንና በሐሰት የመሰረቱትን የፈጠራ ክስ አሁንም እያመነዠኩ ሲዋሹት የኖሩትን ትውልድ እንደ ጴጥሮስ ደግመው ደጋግመው ዛሬም ይክዱታል፣ ያታልሉታል፣ ይንቁታል፤ ክብር እንደሌላቸው በአደባባይ ያሳዩታል። ይህንን ውሸታቸውን የሚያጋልጣቸውን ደግሞ በኦሮሞ ጥላቻ እየከሰሱ አፍ ሲያስዘጉ ሲኳትኑ ይውላሉ።
ዶክተር በያን አሶባና ድርጅቱ  ኦነግ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ «ዜጋ የሆኑና ዜጋ ያልሆኑ» ወይንም «Native እና Subject» ሲል ይከፍላል በማለት የፈጠረው የኃጢያት ክስ አንባቢ ያገናዝብ ዘንድ በእጄ ያለውን በ1923 ዓ.ም. የጸደቀው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ኦሪጅናል የአማርኛ ቅጂ የመጀመሪያ አንቀጽ «ኢትዮጵያዊ ማነው?» ለሚለው ጥያቄ የሕገ መንግሥቱን መልስ ወረድ ብዬ ባተምሁት የሕገ መንግሥቱ የመጀመሪያ ገጽ ላይ በቀይ መስመር አስምሬበታለሁ።
ይህንን የተሰመረበት የመጀመሪያ አንቀጽ ነው እንግዲህ ዶክተር በያን አሶባ « የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ «ዜጋ የሆኑና ዜጋ ያልሆኑ» ወይንም «Native እና Subject» ይላል፤ የታገልነውም በዚህ ምክንያት ነው» ሲሉ የታገሉት በውሸት ታሪክ እንደሆነ በአደባባይ ራሳቸውን የሚያጋልጡት።
ዶክተር በያን አሶባና ሌሎች  ኦነጋውያን በኦነጋዊ ድፍረት እየተመኩ ያመረቷቸውን የኦነግ የፈጠራ ትርክቶች  ወደፊትም በማስረጃ ታግዘን በምናቀርባቸው ጽሑፎች እንመለስባቸዋለን።
Filed in: Amharic