>
5:21 pm - Saturday July 20, 1568

ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለመታደግ ከተፈለገ…… (ፊልጶስ)


ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለመታደግ ከተፈለገ……..

 

ፊልጶስ


በማንኛውም ዘመን ቢሆን ጦርነት አስፈላጊ የሆነበት ግዜ የለም፤ ግን ድግሞ ዓለማችን በተለይም እኛ ብዙው ታሪካችን እና ኑሯችን  የጦርነት ነው።  ለዘመናት ያደረግነውና እይደረግነው ያለው የ’ርስ በርስ ጦርነት  የዓለም ጭራ ብቻ ሳይሆን ግዛታችን እና እንድነታችን እየፈረስ ጠረፍ አልባ ለመሆን በቅተናል።  ትልቅ ከመሆን ትንሽ መሆንን መርጠናል::

አሁን ያለው ጦርነት  የአገርና የህዝብ የህልውና ጦርነት በመሆኑ በድል መወጣት የግድ ይለናል። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ህዝብና መንግስት ተናቦ፣ በሰከነ መንፈስ ከሴራ ፓለቲካና ከመንደርተኛ አስተሳሰብ ወ’ተን፤ የሁላችን መዳኛ ኢትዮጳያን ኢትዮጵያ መሆኖን ከተቀበልን ብቻ ነው።

በዚህ ወቅት የጦርነቱ ሁኔታና የመንግሥትን አቋም ካየነው ወያኔ ወደ መቀሌ በመመለሱ አትሪፊ ነው። ከበቂ በላይ ዘርፋል፣ ገሏል፣ የቻለውን ጭኖ ያልቻለውን አውድሞ ሄዷል። በተቃራኒው በወሎ፣ በጎንደር፣ በሸዋና በአፋር ሰው ሰርቶ ሊተካው የማይችል ለዘምናት የሚቆይ አዕምሯዊና ቁሳዊ ውድመት ደርሶል።

ኢትዮጵያ  ተጎሳቁላለች1 አልቅሳለች! ደምታለች!


በ’ርግጥዱቄትሆኗል ያለው መንግሥት ከዚህ ደረጃ እስኪደርስ፤ 

1/ እንዴት ተፈቀደለት? 

2/ ተጥያቂውስ ማነው

3/ በጦርነቱ ወቅት አመራር እየሰጡ ያሉታ ወያኔን ከተንቤን በርሃ አውጥተው ሸዋ  እንዲገባ ያደርጉት ከጠ/ አብይ አህመድ ጀምሮ ለፍርድ ይቀርባሉ ወይ? ሌላው ቢቀር ለሰሩት ስህተት ወይም አሻጥር  የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ይጠይቃሉ ወይ?

4/ ህዝብስ የደረስበት ግፍ ምንም ዓይነት ምድራዊ ካሳ የማይክሰው ቢሆንም እውነቱን እንኳን የማወቅ መብት የለውም ወይ

5/ ጦርነቱስ እስከምን ድረስ  ነው?


 በመንግሥት፣ በአንዳንድ ወገኖችና ካድሪዎች (መስሎ አዳሪዋች) በኩል ያለው ስሜታዊ የድል ጭፈራና ፋከራ ጦርነቱ  ያለቀ አስምስሎታል። ትግራይን ተቆጣጥሮ ፤ወያኔን እስከ አመለካከቱ ወደ ማይመለስበት መቅበር ካልቻለ፤ ምዕራቡን ዓለም ከጎኑ ያሰለፈው ወያኔ እንደገና እንደሚያንሰራራ ሳይታለም የተፈታ ነው። 

እናም ህዝብም ሆነ በእውነት ለኢትዮጵያ እንድነት ቁመናል የምንል በአሁኑ ወያኔን ወደ መቀሌ የመመለስ ድል አንዘናጋ፤ ከፊት ለፊታችን ትልቁ ጦርነት ይጠብቀናልና። መንግሥት ግልጽ ሆኑ ከኦነጋዊ ብልጽግና ድብቅ ዓላማና አሻጥር ራሱን አጽድቶ ፤ ህዝብን አስተባብሮ ከታገል ወያኔ እስከ አመለካከቱ እስከመጨረሻው እንደሚሸኝ ጥርጥር የለውም። 

ወያኔ ትግራይ ውስጥ እንዲመሽግ ከተፈቀደለት ግን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ምንግዜም ዕረፍት አይኖረንም፤ ተረኛዎቹ ገዥዎች ኦነጋዊ ብልጽግናም የወያኔን መኖርና እነሱ እንገነባታለን ለሚሏትኦሮሚያማረጋገጫ ይሆናል። 

ጥያቄው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ይፈቅዳል ወይ ነው።  መልሴ መፍቅድ አይደለም መታሰብም የለበትም ነው። ከአሁን በኋላ ህዝብ ከትላንቱ ስህተቱ መማር የግድ ይለዋል ብቻ ሳይሆን መንግስትንም ሆነ ሌሎቹን ምክንያት በማድረግ  ወያኔና አመለካከቱ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲኖር ከፈቅድን ለምከፍለው ዋጋ ተጠያቂ  እኛ እንጂ ማንም ሊሆን አይችልም።

ጦርነቱን በድል ለማጠናቀቅና ኢትዮጵያን ለመታደግ ከተፈለገ መንግሥት  ከጦርነቱ ጎን ለጎን  ከወያኔ የወርሳቼንና አሁን እየተጠቀመባቸው ያሉ የጸረ-ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ ላይ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቅና አስፈላጊም ከሆነ ማስገደድ የወቅቱ ትግል ነው። ስለዚህ ፤

1/ህገመንግሥቱ=> ስለ ወያኔና ኦነግ ህገ-መንግሥት ( ነፍሳቼውን ይማረውና ፕ/መ መስፍን ”ህገ-አራዊት” ይሉት ነበር።) አሁን ላለንብት የሰቆቃ ዘመን አድርሶናል። ይሁን እንጂ  ብልጽግናዎች በደማችን ያገኘነው ”አይነኬ” መሆኑን አስረግጠው ነግረውናል። የኢትዮጵያዊያን ”ተራጀዲ” ተውኔት የሚያስመስለው ደግሞ፤ ትላንት ህገ-መንግሥቱ እስከ አለ ድረስ ኢትዮጵያ አገር አትሆንም ሲሉን የነበሩትና ህገ-መንግሥቱ አይውክለንም ያሉት፤ አሁን  ህገ- መንግሥቱን ተቀብለው ብቻ አይደለም ጠባቂና አስጠባቂ  መሆናቸው ነው።አሁን አገራችን የምትተዳደረው በአስቼኳያ ግዜ አዋጅ ነው። ስለዚህም አስቼኳይ አውጁን መሰረት አድርጎ ህገ-መንገሥቱንም በተመሳሳይ መንገድ ማገድ ይቻላል።   እውነት በእውነት የብልጽግና መንግሥት በተለይም ጠቅላይ ሚኒስተሩ  በተግባር የሚፈትኑበት በመሆኑ እና  በእውንት ኢትዮጵያ ! ኢትዮጵያ የምንልም ይህ እንዲተገበር ፊለፊት መናገርና መጋፈጥ የግድ ይለናል። 

2/ክልል=>  አሁን ያለው ጎሳንና ቋንቋን መሰረት ያደረገ ክልል ወያኔ የቀበረው ቦምብ፤ ኦነጋዊያን የሚመጻደቁበት ጸረ-ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ጸረ-ተፈጥሮ ነው። ይህ የክልል እስተዳደር እስከአለ ድረስ መቸውንም ቢሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ‘ረፍት ማግኘት አይደለም ከጦርነት አዙሪት አይወጣም። ስለዚህም  የክልል አስተዳደር መልካ ምድርንና ምጣኔ ሃብትን መሰረት ያደረገ አውቃቀር እንዲኖረው  ገዥዎቻችንን ማስገደድና  የኢትዮጵያ ህዝብ ታግሎ ማስፈጸም ያለበት ለነገ የሚባል ጉዳይ ነው ፤ ምክንያቱም መከረውና ግፋ የተረፈው ለህዝብ እንጅ ለገዥዎቻችን አይደልምና። ገዥዎቻችንማ የስልጣናቸው ማራዘሚያና ለሚሰሩት ወንጀል  መደበቂያ  የጎሳ ክልላቸው ነው።

3/ሰንደቅ ዓላማችን =>   አረንጓዴ፣  ቢጫና ቀይ የኢትዮጵያዊን ሰንደቅ ዓላማ ነው።ይህ ሰንደቅ ዓላማችን ሚሊዮኖች የተሰውለት አሁንም እየተሰውለት ያለና ወደፊትም ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ መሰዋአት የሚከፍልበት የማንነቱና የአንድነቱ  አርማው ነው።  ይሁን እንጂ እንደምታዮት አሁንም በጦርነትም ላይ ይሁን በማንኛውም ቦታ  መንግስትም  የሚጠቀመው ወያኔ ሰፍቶ የሰጠውን  ባለአምባሻው”  ነው ክልሎችም የሚያውለበልቦት ወያኔ የሰራላቸን ምንም ዕይነት ታሪክ የሌለው ነው።ርግጥ ነው በአፋር፣ በጎንደር፣ በጎጃምና በወሎ የሚገኙ ተዋጊዎች የሚይዙት ነባሩን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ነው።   ለአንድ አገር እንደነት ለሚደረግ ጦርነት ሁለት ዓይነት ሰንደቅ ዓላማ ይዛ ያለች አገር እስከማውቀ ደረስ የእኛዋ ብቻ ነች። ያወም ጠላታችን ሆኖ እየወጋን ያለው ኃይል  የጫነብንን ሰንደቅ ዓላማ።

ስለዚህ መንግሥት  ነባሩ   አረንጓዴ፣  ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማችን እንዲጠቅም መጠየቅና  መታገል   ከህዝብ ይጠበቃል።  

ትላንት በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አንደራደርም ሲሉን የነበሩት ዛሬ የስልጣን ወንበሩን ሲፈናጠጡ የወያኔን ሰንደቅ ዓላማ ከጀርባቸው ሰቅለውእዩኝ ! እዩኝ! “ ሲሉ ማየት የሚያስተዛዝብ ቢሆንም የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ለሰንደቅ ዓላማው ከዚህ በኋላ መክፈል ያለበትን መስዋእትነት መክፈል አለበት። 

4/የፓለቲካ እስረኞችን ማስፈታት=> የፓለቲካ እስረኞች በተለይም  የባልደራስ  አመራር አባላት እነ አቶ እስክንድር ነጋ እና በአመለካከታቸው ብቻ የተሰሩ ጋዜጠኞችን ሳይውል ሳያድሩ እንዲፈቱ ማደረግ የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳይና ኃላፊነት ነው። መንግሥት ለኦነጋዊ ብልጽግ ዓላማ እንቅፋት ይሆናሉ ተብለው ያለፍርድ የታሰሩ ዜጎችን አሳሰረን አንድነታችን እና ኢትዮጵያዊነታችንን ልናስከብር አንችልም።

5/ አዲስ አበባ=> አዲስ አባባ በኦነጋዊን ብልጽግናኬኛተብላ መዲናነቷ ለኢትዮጵያ ሳይሆን ለኦነጋዊያን እንድትሆን  መስራት ከተጀምረ ዓመታት አስቆጠርን።  የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነትን አሻራ   ነው የተባለ  ሁሉ  እንዲጠፋና እንዲወድም ተፈርዶብታል።  በዚህ ከቀጠልን ነገ ከነገ ወዲያ ከአዲስ አበባ ውጡ መባላችን እንደማይቀር ተገንዝበን፤ ኦነጋዊ ብልጽግና ከዚህ እኩይ ድርጊቱ እንዲታገድ ማድረግና አዲስ አበባ የሁላችን የኢትዮጵያው  መሆኗን ማረጋገጥ  መቻል አለብን። በተለይ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት የኦነጋዊነትን የበላይነት በከተማዋ ውስጥ ለማረጋገጥ ሌት-ተቀን እየሰራ ስለሆነ መራራ ትግል ያስፈልገናል።

6/ ግድያው ይቁም => በተለይም በወለጋና በቢሻንጉል እንዲሁም በተለያዮ እካባቢዎች  በተለይም በአማራ  ህዝብ ላይ የሚፈጸመው ግድይ ማስቆም  አለብን። ግድያውን ማሽሞንሞን አያስፈልግም፤ በኦሮሚያ ብልጽግና መዋቅር ተዘርግቶለት የሚካሄድ የዘር ማጥፋት ወንጅል ነው። ስለዚህ ይህን  የዘር ፍጅት በልመና እና በልቅሶ የሚቀር ሳይሆን በትግል ነውና  ከላፈው ተምረን ይህን መንግስታዊ ግድያ ማስቆም መቻል አለብን።

7/ የአገራችን የውጭ ግንኙነት=> ምዕራቡ ዓለምም ሆነ ሱዳን እና ግብጽ እንዲህ እንዲፈነጩብን ያደራጋቸው የመንግሥት ድክመት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ  በመንግሥት ደካማነት የተፈጠረውን ክፍተት መሙላትና አገራችንን በምንም መስፈርት ቢሆን የውጩ ዓለም  የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት መታገልና መቋቋም  የህልውናችን ጉዳይ መሆን አለበት፥፥አንዳንድ ወገኖች ገዥው  ኦነጋዊ ብልጽግና ከወያኔ የሚለይበት በስልጣን እንጅ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ናቸው፤ ስለዚህ ጣልቃ ግብነቱን በገዥው ኃይል እስከሆነ ድረስ መቃዎም የለብንም የሚሉ አሉ።  ነገር ግን ምዕራቡ ዓለም  እንደተለመደው የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት  በእኛ ላይ ለመጫን እንጂ፤ በምንም ዓይነት መስፈርት ቢሆን ኢትዮጵያን ሊታደግ ጣልቃ የሚገባ  የውጭ አገር የለም። ችግሩ ከወያኔ ጋር ብቻ ሳይሆን ከህዳሴው ግድብ ጋር የተያያዘና የምዕራቡ ዓለም የዘመናት ፀረ-ኢትዮጵያዊነትና የማዳከም ሴራ መሆኑን መገንዘብ ይገባናል። ሊያንግሱልን የፈለጉት እኮ ወያኔን እና የቤተ-መንግሥቱ ግማሽ አካል የሆነውን ኦነግ ሸኔ ነው። እናም ለአገራችን እኛው በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ከተደራጀንና ኃይል ከፈጠርን፤ የአገራችን እጣ በእኛው እጅ ነው።

ማሳሰቢያ፤

ይድራስ  በኢትዮጵያ /  አብይ አህመድ ጥሪ ተደርጎላችሁ ወደ አገር ቤት ለምትገቡ ኢትዮጵያዊያን

ከላይ ላነሰዋቸው ጉዳዮች  እናንተንም ይመለከታለና በቆይታችሁ  ለጋበዛችሁ መንግሥት አቅርባችሁ ለተፈጻሚነቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ቁማችሁ እንደምትታገሉና የድርሻችሁን እንደምትወጡ ተስፋ አደርጋልሁ። መቼም  ለዛ  በጦርነት የምድርን ፍዳ ሁሉ ላየ  ምጻተኛ ህዝብ ጮማ ቆረጣና  በውስኪ  መራጨትን ልታሳዮት እንዳልተጋብዛችሁ እምነቴ ነው። በእርግጥ ውጤቱን አብረን የምናየው ይሆናል።

 

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!

 

ፊልጶስ :E-mail: philiposmw@gmail.com

Filed in: Amharic