>
5:21 pm - Sunday July 20, 7941

ታዋቂው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ህይወቱ አለፈ....!!! (ሚልኬሳ ቶሎሳ)

ታዋቂው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ህይወቱ አለፈ….!!!

 

ሚልኬሳ ቶሎሳ


በ53 ዓመት ዕድሜው ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን የቅርብ ቤተሰቦቹ  ይናገራሉ!

ተስፋዬ ገብረአብ ለወራት በሕመም ላይ የቆየ ሲሆን በኬንያ ዋና ከተማ ውስጥ ሕክምና ሲከታተል ቆይቶ ነው አርብ ከሰዓት በኋላ ታኅሣሥ 15/2014 ዓ.ም ያረፈው።

በሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹ በስፋት የሚታወቀው ተስፋዬ ነሐሴ 22/1960 ዓ.ም ከኤርትራውያን ቤተሰቦቹ ከአዲስ አበባ በስተምሥራቅ 40 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው በቢሾፍቱ ከተማ ነበር ተወልዶ ያደገው

ተስፋዬ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ጽሑፍ ፍቅርና ዝንባሌ ስለነበረው ከወጣትነት ዘመኑ አንስቶ ከበርካታ ታዋቂ የኢትዮጵያ ጸሐፊያን ጋር የቀረበ ግንኙነት እንደነበረው ይናገራል።

በደርግ ዘመን ማብቂያ አካባቢ በጦር ሠራዊቱ ተመልምሎ ሥልጠና ከወሰደ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወታደራዊው መንግሥት ወድቆ ከኢሕአዴግ ጋር ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ በጋዜጠኝነት ሲያገለግል ቆይቷል።

ተስፋዬ ታዋቂዎቹን ዕለታዊ የመንግሥት ጋዜጦችን የሚያሳትመው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ለመሆን የቻለ ሲሆን፣ ድርጅቱን በሚያስተዳድርበት ወቅት በዕለታዊዎቹ ጋዜጦች ላይ መሠረታዊ ለውጥ እንዳመጣ ይነገርለታል።

ተስፋዬ በጋዜጦቹ ላይ ታዋቂ ጸሐፊያን እንዲሳተፉ በማድረግ እንዲሁም በተለይ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ይወጡ በነበሩት ህትመቶች ላይ ከፍተኛ ለውጥ በማድረግ አስተዋጽኦው የጎላ እንደነበር ባልደረቦቹ ይመሰክራሉ።

በተጨማሪም ከገዢው ኢሕአዴግ ፓርቲ ጋር ጥብቅ ቁርኝት የነበረው “እፎይታ” መጽሔትን በመምራትም ይታወሳል።

ተስፋዬ በኢትዮጵያ ሳለ ከጋዜጠኝነት ሙያው ጎን ለጎን መጽሐፍቶችንም አሳትሟል፣ ከገዢው ፓርቲ ጋር በነበረው አለመግባባት ኢትዮጵያን ጥሎ ከወጣ በኋላ በኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኔዘርላንድስ እና ሌሎችም አገራት ኗሯል።

ተስፋዬ የጋዜጠኝነት ሥራውን ካቆመ በኋላ አስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ በመሆን ከስምንት በላይ ሥራዎችን ለአንባቢያን አድርሷል።

ከስምንት በላይ ሥራዎችን በአማርኛ ያሳተመው ደራሲው፣ በአንባቢያን ዘንድ በስፋት ያስተዋወቀው “የቡርቃ ዝምታ” የተሰኘው ረዥም ልብ ወለዱ ነው።

ይህ የልብ ወለድ መጽሐፉ በበርካታ የአማርኛ ልብ ወለድ አንባቢያን ዘንድ ነቀፌታን አሰንዝሮበታል።

ከዚህ በኋላም ደራሲ ተስፋዬ የግል ማስታወሻ፣ ልብ ወለድ፣ አጫጭር ልብ ወለድ እንዲሁም ወግ በመጻፍ አድናቆትን አትርፏል።

በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ በዚህ ዘመን ከሚጠቀሱ ጸሐፊያን መካከል አንዱ እንደሆነ በርካቶች ይመሰክሩለታል።

ተስፋዬ በሥነ ጽሑፍ ችሎታው የሚወደሰውን ያህል በሥራዎቹ በሚያነሳቸው ጉዳዮች የሚተቹት ሰዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።

በተለይ በኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች መካከል መቃቃርን ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል በሚል በርካቶች ይወቅሱታል።

በሌላ በኩል ጽሑፎቹ የተዳፈኑ የጭቆና ታሪኮችን ያነሳሉ፣ የተገለሉ ማኅበረሰቦችን እውነታም ያንጸባርቃሉ ብለው የሚከራከሩ ወገኖች አሉ።

ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ የእፎይታ መጽሔት ዋና አዘጋጅ በነበረበት ወቅት፤ እሱ በወጣትነት ጊዜው የገጠመውን የአሳታሚ እጦት ችግር ለመቅረፍ በሚል፤ የበርካታ ወጣት ደራሲያን ሥራዎችን በማሰባሰብ በተከታታይ ቅጾች ሥራዎቻቸው እንዲታተሙ ዕድል ከፍቷል።

ተስፋዬ “እፍታ” በሚል ርዕስ በሁለት ተከታታይ ዓመታት (ከ1992-1993 ዓ.ም) አምስት ቅጾችን በማሳተም ለንባብ አብቅቶ ነበር።

ይህ “እፍታ” የተሰኘ የተለያዩ ወጣትና ታዋቂ ደራሲያን ሥራዎች በአንድ ቅጽ ለንባብ እንዲበቁ ያደረገበት ሥራው ለደራሲያኑም ሆነ ለአንባቢያን አዲስ ዕድልን የከፈተ እንደነበር ይነገራል።

በተጨማሪም ከህወሓት የትግል ጅማሬ አስከ ኢሕአዴግ አዲስ አበባ መግባት ድረስ ያለውን ዋና ዋና ታሪክና ገድል የሚተርከውን ተከታታይ ቅጽ ያለውን “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” መጻሕፍትንም በማሳተም ይታወቃል።

ተስፋዬ በጋዜጠኝነቱና በሥነ ጽሑፉ ዘርፍ የገዢው ኢሕአዴግ ዋነኛ ሰው በመሆን የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰራ የቆየ ሲሆን፣ እሱ እንደሚለው ከአገሪቱ ዋነኛ ፖለቲከኞች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ኢትዮጵያን ለቅቆ ለመሰደድ በቅቷል።

ከአገር ከወጣ በኋላም ብዙ መነጋገሪያ የሆኑ የገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግና የባለሥልጣናቱ የውስጥ ምስጢር የሆኑ ጉዳዮችን የያዙትን “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” እና “የደራሲው ማስታወሻ” የተሰኙ መጻሕፍቶችን ለንባብ አብቅቷል።

በድንቅ የጽሑፍ ችሎታው በርካቶች የሚያደንቁት ተስፋዬ ገብረአብ፤ የሩሲያ ደራሲያን የዶስቶቭስኪ፣ የማክሲም ጎርኪ፣ የፑሽኪን እና የቶልስቶይ ተጽዕኖ እንዳለበት በተደጋጋሚ ሲናገር ይደመጣል።

ተስፋዬ ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላ በተለያዩ አገራት ውስጥ በስደት ከቆየ በኋላ ወደ ኤርትራ በመሄድ ሙሉ ጊዜውን ለሥነ ጽሑፍ ሥራው በማዋል የተለያዩ መጻሕፍትን ለንባብ አብቅቷል።

ተስፋዬ እስካሁን ለህትመት ያበቃቸው ሥራዎቹ በሙሉ በአማርኛ ቋንቋ የጻፋቸው ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ወደ እንግሊዝኛ እና ኦሮምኛ ተተርጉመዋል።

   ⇑ ተስፋዬ በመጨረሻው ሰአት

Filed in: Amharic