>
5:13 pm - Thursday April 20, 7978

ኢትዮጵያን ለመከራ የዳረጋት አረመኔው ጠላቷ ሳይሆን " ይቅር ባይ መንግሥቷ¡¡¡" ነው! (አሳዬ ደርቤ)

ኢትዮጵያን ለመከራ የዳረጋት አረመኔው ጠላቷ ሳይሆን ” ይቅር ባይ መንግሥቷ¡¡¡” ነው!
አሳዬ ደርቤ

ለማስረጃም ያህል….
ኢትዮጵያን ሲዘርፍና ዜጎቿን ሲጨፈጭፍ 27 ዓመት የኖረው አረመኔ በወጣቶች ተጋድሎ ከሥልጣኑ ተነሳ፡፡
ይቅር ባዩ መንግሥትም እኒህን ወንጀለኞች ወደ እስር ቤት በመላክ ፈንታ ወደ ቤተ-መንግሥት ጠርቶ ከጋበዛቸው በኋላ በክብር ሸኛቸው፡፡
አረመኔዎቹም ወደ መቀሌ ከሄዱ በኋላ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ከበጀት ውጭ ምንም አይነት ግንኙነት የለንም›› ብለው ሦስት ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያን ሲያቃጥሏትና በደም ሲያጨቀዮት ኖሩ፡፡
አርቆ አሳቢው መንግሥትም ፍጹም በተረጋጋች ክልል ውስጥ ተቀምጦ አገር የሚያቃጥለውን ድርጅትና መሰሪውን ፕሬዝዳንት ሊያወግዘው ሲገባ ‹‹ደብረ ጽዮንን ልናግዘው ይገባል›› እያለ ሦስት ዓመት ሙሉ እሳት በማጥፋት አሳለፈ፡፡
አረመኔው ቡድንም ‹‹ከክልሌ ያለው ሠራዊት ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግሥት ሳይሆን ለክልሉ መንግሥት ነው›› የሚል አዋጅ ካጸደቀ በኋላ ባንዱ ሌሊት ሰሜን እዝን በመጨፍጨፍ በቅራቅርና በራያ በኩል ወረራ ፈጸመ፡፡
ደጉ መንግሥትም በቴሌቪዥን ቀርቦ ስለተፈጸመው ክህደት ካብራራ በኋላ አገራዊ ጥሪ አቀረበ፡፡
የአማራና የአፋር ልዩሃይልና ታጣቂም ጥሪውን ተቀብሎ ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመሰለፍ ከፍተኛ ዋጋ ከከፈለ በኋላ አሸባሪውን ከመቀሌ ወደ ቆላተንቤን መሸኘት ቻለ፡፡
አብዛኛው የጁንታው ታጣቂም ከባድ መሳሪያውን በቤተ-እምነቶች ውስጥ ከደበቀ በኋላ በሲቪል ልብስ ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀላቀለ፡፡
በዚያች ክልል የሚጨክን ልብ የሌለው የፌደራል መንግሥታችንም የመቶ ቢሊዮን ብር በጀት ከደለደለ በኋላ ወደ ምርጫ ዝግጅት ገባ፡፡
አረመኔው ቡድንም ይሄንን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ሁለተኛውን ክህዴት በሠራዊታችን ላይ ሰነዘረ፡፡
ጨዋው መንግሥትም የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ ደጀን ፍለጋ ሠራዊቱን ስቦ አስወጣ፡፡
እብሪተኛው አሸባሪም ‹‹የማዋርደው ብሔር፣ የማፈርሳት አገርና በቁጥጥር ስር የማውለው አመራር አለኝ›› በሚል ፉከራ አማራና አፋር ክልልን ወርሮ በዋጋ የማይተመን ሰብዓዊ ጉዳትና ወደ ግማሽ ትሪሊዮን የሚጠጋ ሐብት ማውደምና መዝረፍ ቻለ፡፡
ይሄንን አድርጎ ሲጨርስ ‹‹ከዚህ በኋላ የአራት ኪሎን ወንበር መቆጣጠር እንጂ መደራደር አይታሰብም›› በሚል ፉከራ ወደ ሸዋ ማምራት ጀመረ፡፡
መንግሥትም ሳይወድ በግዱ በሚዲያ ብቅ ብሎ ‹‹ ይሄን አሸባሪ ቡድን በመደበኛ ሠራዊት ማሸነፍ እንደማይቻል ከገለጸ በኋላ ‹‹እኔ ወደ ግንባር እያመራሁ ስለሆነ አገር መታደግ የምትፈልጉ ሁሉ ተከተሉኝ›› የሚል ጥሪ አቀረበ፡፡
እኒያ የፈረደባቸው የሁለት ክልል ሕዝቦችም ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር ተሰልፈው ከፍተኛ ዋጋ ከከፈሉ በኋላ ወረራውን መቀልበስ ቻሉ፡፡
አረመኔው ቡድንም ለሰላም ሲል ከአፋርና ከአማራ ክልል ሠራዊቱን ማስወጣቱን ገልጾ ውይይት ይጀመር ዘንድ ጥሪ አቀረበ፡፡
ይቅር ባዩ መንግሥትም የአሸባሪውን ጦር እግር በእግር የመከታተል ዓላማ እንደሌለው ገልጾ ስለ ድርድር ያወራ ጀመር፡፡
ምን ልልህ ፈልጌ ነው?
በብልጽግና ዘመን እጅግ በጣም ቀላሉ ነገር ተከዜን ተሻግሮ በሆነ ሕዝብ ላይ አረመኔያዊ ተግባር ፈጽሞ መመለስ ሲሆን የማይቻለው ደግሞ ይሄንኑ ወንዝ አልፎ ወንጀለኛን መቆጣጠር ነው።
‹‹ክቡር አሸባሪ-
ጨፍጭፋ የምትሸሽ- ዘርፋ የምትከስስ
የተረገመ ሕዝብ-
ሲታረድ ሰንብቶ- ባዶ እጅ የሚመለስ›› እንደማለት…
Filed in: Amharic