>

“ውሳኔዎቻችን በስሜት የሚወሰኑ ሳይሆን ዘላቂ ጥቅምን ያገናዘቡ ናቸው!” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

“ውሳኔዎቻችን በስሜት የሚወሰኑ ሳይሆን ዘላቂ ጥቅምን ያገናዘቡ ናቸው!”
 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ 

በዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት የተጀመረው ማጥቃት አሸባሪውን ሕወሐት ከአማራና ከአፋር ክልሎች በማስወጣት የመጀመሪያውን ግብ አሳክቷል። መንግሥትም የመከላከያ ሠራዊቱ አሁን በያዛቸው አካባቢዎች ላይ እንዲቆይ ትእዛዝ ሰጥቷል፤ ይሄንን ውሳኔ የወሰንነው በስሜት ሳይሆን የሚያስገኘውን ዘላቂ ጥቅም ከግምት አስገብተን ነው። ኢትዮጵያን ዘላቂነት ባለድል የማያደርግ አካሄድ ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለጠላቶቻችን ብርታትን የሚፈጥር፣ የሽብር ቡድኖች እድሜያቸውን የሚያረዝሙበትን ሰበብ እንዲያገኙ መፍቀድ ነው። አለፍ ሲልም በስሜት የሚወሰኑ ወታደራዊ ውሳኔዎች ሀገራችንን በተራዘመ ጦርነት አዙሪት ውስጥ እንድትዘፈቅ ያደርጋል።
ኢትዮጵያን ለማዳከም የተከፈተው ዘመቻ መልከ ብዙ ነው። የሕልውና አደጋው በግልጽ ብቻ አይደለም በስውርም ይፈጸማል። ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የመረጃ ጦርነቶች የሚካሄዱብን በተቀናጀና በረቀቀ መልኩ ነው። እኛ እየመከትን ያለነው ውጊያውን ብቻ ሳይሆን ዘመቻውን ጭምር ነው። የዘመቻው ግንባሮችም ብዙዎች ናቸው። አንዳንዶቹ ፊት ለፊት የሚፈጸሙ ሲሆን፣ አንዳንዶቹም በወጥመድ መልክ የሚከወኑ ናቸው። መንግሥት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ህልውና ላይ የተከፈተውን ግልጽና ረቂቅ ዘመቻ ለመመከትና ለመቀልበስ ብሎም በዘላቂነት የኢትዮጵያን አሸናፊነት ለማረጋገጥ የነደፈው ዕቅድ ሁለገብና ሁሉንም ግንባሮች ለመመከት የሚያስችል ስልት ነው።
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ችግር መከሠት የጀመረው ለውጡን ተከትሎ መሆኑን ሕዝባችን ያውቃል። “እኔ ብቻ የማልገዛት ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት” ብሎ የሚያምነው ሕወሐት ክልሉን ምሽግ አድርጎ ችግር መፍጠር የጀመረው በለውጡ መባቻ ነበር። መንግሥት ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት እንዳይፈጠር፣ የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት እንዳይደፈርስና በኢኮኖሚው ላይ ከባድ ጫና እንዳይደርስ በማሰብ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተሞክሮ ነበር። አሸባሪው ሕወሐት ግን ከጥፋት መንገድ በቀር ሰላማዊ መንገድ የማይታየው ሆነ።
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ሰላም መነሻ በማድረግ፣ በሌሎች አካባቢዎች ያለውንም የሥጋት ደረጃ በመመርመር፣ ሠራዊታችንን ከኢትዮ ኤርትራ ድንበር ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማንቀሳቀስ ስንሞክር፣ በትግራይ ሕዝብ ውስጥ መሽጎ የሚገኘው አሸባሪው የሕወሐት ቡድን፣ ሕጻናትን መንገድ ላይ እያስተኛ፣ አረጋውያንንም እንዲለምኑ እያደረገ፣ ሠራዊቱ ከትግራይ እንዳይወጣ ማድረጉ ይታወሳል። ይሄንን በሕዝብ ጥያቄ የተሸፈነ እኩይ ተግባር በአንድ በኩል እያከናወነ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን ለመውረር ከሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ጋር በምሥጢር ይደራደር ነበር።
ኢትዮጵያን ለመውጋት ከውጭ ኃይሎች ጋር ያደረጉትን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ሲሉ፣ በሕዝቡ ልመና በትግራይ የቆየውንና ሕዝቡን በደሙና በላቡ ሲያገለግል የኖረውን ሰሜን ዕዝን በግፍ መሣሪያውን ለመንጠቅ ዘግናኝ ጥቃት ሰነዘሩ። የሀገር የመጨረሻው ደጀን በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት የሉዓላዊነትና የህልውና ጥቃት ነው። የአሸባሪው ሕወሐት ዋና ዓላማም የሰሜን ዕዝ የታጠቃቸውን ትጥቆችና ስንቆች በመንጠቅ ኢትዮጵያን ለመውረርና ለማፈራረስ ነበር። ይሄንንም ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር መክሮና ተቀናጅቶ ያደረገው ነበር። የዛሬ ዓመት በጥቅምት መጨረሻ፣ የመከላከያ ሠራዊት በወሰደው አፋጣኝ የማጥቃት ርምጃ ጁንታው ተሸንፎ ወደ ተንቤን በረሐ ፈርጥጦ ነበር። በዚህ የህልውናና ሕግ የማስከበር ዘመቻ የተነጠቅናቸውን መሣሪዎያችና የተማረኩብንን የሠራዊት አባላት አስመልሰናል። ከሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች የተወሰኑ ወንጀለኞችን ለሕግ እንዲቀርቡ ማድረግ የቻልን ሲሆን አሻፈረኝ ያሉትም እርምጃ ተወስዶባቸዋል።
ሠራዊታችን በትግራይ ሕዝብ ጥያቄ መሠረት ለስምንት ወራት በክልሉ ቆይቷል። በቆይታውም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲቀላጠፉ መሥዋዕትነት ከፍሏል። መሠረተ ልማቶች እንደገና እንዲገነቡ፣ የሕዝብ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ፣ ሰብአዊ እርዳታዎች በተሻለ ሁኔታ ተደራሽ እንዲሆኑ የሚቻለውን ሁሉ አደርጓል። ይኼን በሚያደርግበት ወቅት ሠራዊታችን በሁለት በኩል ዋጋ ሲከፍል ነበር። አንደኛ በዚያ የነበረው ቆይታ በጠላት ፕሮፓጋንዳና የጠላትን ፕሮፓጋንዳ በሚያስተጋቡ የውጭ ሚዲያዎች ያለ ስሙ ስም ተሰጥቶታል። ሁለተኛ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ በሆነው የክልሉ ማኅበረሰብ ከጀርባ ለመውጋት ተገደደ።
ሠራዊታችን ደም ከፍሎ በሰጠው አገልግሎት የተረፈው ወቀሳና መጥፎ ስም ሆነ። ለሰብዓዊ ተግባራትና ለመልሶ ግንባታ ከ100 ቢልዮን ብር በላይ ማውጣታችን ከምን ሳይቆጠር አስተዳደሩና የጸጥታ ኃይሉ ባልዋለበት መወቀስ ጀመረ። የትግራይ ገበሬም በአንበጣ ምክንያት የተጓጎለበት የእርሻ ሥራ በጦርነቱ ምክንያት ዳግም ስለተጎዳበት ፋታ ማግኘት ያለበት ደረጃ ላይ ደረሰ። ይሄንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም መንግሥት በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተኩስ አቁም ስምምነት አድርጎ የመከላከያ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል የማስወጣት ውሳኔ ሊተላለፍ ቻለ።
አሸባሪው ሕወሐትና አንዳንድ ዓለም አቀፍ አጋሮቹ ግን ሠራዊታችን ለሰብአዊነት ብሎ ከትግራይ መውጣቱን እንደ መሸነፍ ሲቆጥሩት ተስተውለዋል። በስምንት ወራት መታከት ውስጥ የቆየው ሠራዊታችን ፋታ ሳያገኝ ማዳከም ስለተፈለገ፣ ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት በቀረ የሕዝብ ማዕበል የጦር ስልት አሸባሪው ቡድን ዳግም የማጥቃት እርምጃውን ጀመረ። ይሄንን ወረራ ለመቀልበስ እንዲቻል፣ ለዝግጅት በቂ ጊዜ ወስደን፣ የአመራር ጥበብን፣ የተቀናጀ ዕቅድንና ቴክኖሎጂን በመጠቀም፣ የደረሰብንን ወረራ ስንከላከል ቆይተን የጥፋት እርምጃውን ቀልብሰነዋል። ጠላት ከወረራቸው አካባቢዎችም ተጠራርጎ ወጥቷል።
መንግሥት ህልውና የማስከበር ዘመቻው ባለ ብዙ መልክ መሆኑን ዐውቆ ለሁሉም ግንባር የሚሆን በቂ ዝግጅት አድርጓል። ህልውናችንንና ሉዓላዊነታችንን የምናስከብርበት ሜዳ የጦር ሜዳው ብቻ አይደለም። ከወታደራዊ ዘመቻው ጋር አብረው ልንዘምትባቸው የሚገቡ ሌሎችም ሜዳዎች አሉ። መንግሥት የሚወስናቸው ውሳኔዎች ሁሉንም ግንባሮች መሠረት ያደረጉ እንጂ በተናጠል እይታ የታጠሩ አይደሉም። የመጀመሪያው ዕቅዳችን አሸባሪውን ቡድን ከአፋርና ከአማራ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ማጽዳት ነው። ይሄንንም መቶ በመቶ ሊባል በሚችል መልኩ አሳክተናል። ሠራዊታችንንም ስትራቴጂያዊ በሆኑ ቦታዎች እንዲሠፍር በማድረግ የጠላትን እንቅስቃሴ በአንክሮ እንዲከታተል አድርገናል።
ይሄንን እንድንወስን ያደረጉን ብዙ ምክንያቶች አሉ። አንደኛ የግዛት አንድነታችንና ሉዓላዊነታችነን የሚያሠጋ ነገር ከገጠመን በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ወደ ትግራይ ክልል ገብቶ የሀገርን ደኅንነት ለማስከበር የመከላከያ ሠራዊቱ ሕገ መንግሥታዊ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም አለበት። በሌላም በኩል ሕወሐትና አፈ ቀላጤዎቹ መንግሥትንና ሠራዊቱን ለመክሰስ ወደ አዘጋጁት የሤራ ወጥመድ መግባት እንደሌለብን እናምናለን። በዚህ ወቅት የእኛ ወደ ክልሉ መግባት ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው። የትግራይ እናቶች ይሄንን ሁሉ ምስቅልቅል ያመጣባቸውንና ልጆቻቸውን ነጥቆ ያስጨረሰባቸውን አሸባሪ ኃይል መጠየቅ አለባቸው። ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄንን አሸባሪ ከጫንቃው ላይ ያስወገደው በመራራ ትግሉ ነው። የትግራይ ሕዝብም እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ይሄንን አሸባሪ ታግሎ የማስወገድ አቅምና ችሎታው አለው። ድጋፍና እርዳታ በአስፈለገ ጊዜም የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከክልሉ ሕዝብ ጎን ይቆማል።
የማንኛውም ውሳኔያችን መርሕ ኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ድል እንድትጎናጸፍ ማስቻል ነው፤ ግዛታዊ አንድነታችን የሚጠበቅበትና በዘላቂነት ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆንበትን መንገድ መቀየስ ነው። ከእንግዲህ አሸባሪው ኃይል በቃዠ ቁጥር የፈለገውን የሚያደርግበት ሁኔታ የለም። የለም ስንል አይፈልግም ወይም አይሞክርም ማለታችን አይደለም። ነገር ግን እንደ ከዚህ በፊቱ አንድነታችን ጠብቀን እስከቆምን ድረስ መቼም ቢሆን ኢትዮጵያ አትሸነፍም፡፡ የኢትዮጵያ ድል መሠረቱ የጠላት ድክመት ሳይሆን የእኛ ብርታትና ትብብር መሆኑን አውቀን፣ ይበልጥ አንድነታችንን አጠንክረን መቆም ይገባናል፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ታህሳስ 15፣ 2014 ዓ.ም
Filed in: Amharic