ሰለሞን አላምኔ
*….. በ15/04/2014 ከነበረው የችሎት ውሎ የተወሰደ
ሰኞ ዕለት ለዛሬ አርብ (15/4/14) ቀሪ ሁለት ምስክሮች ተይዘው መጥተው ፍርድ ቤቱ እንዲመሰክሩ በቀጠረው ችሎት መሰረት እነ እስክንድር ላይ የሚመሰክሩት ሁለቱ ምስክሮች አለመቅረባቸውን አቃቢ ህጉ (ሩቭ ራስታዋ አቃቢ ህግ ነበር ዛሬ ተረኛ) ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ ፧ 1ኛው ምስክር እንዲታለፍለትና 2ኛው ምስክር ግን ታስሮ መጥቶ ፍርድ ቤት እንዲመሰክር ጠይቆ ለ22/4/14 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ።
የመስቀሉም ታሪክ የሚጀምረው ከዚህ በኃሏ ነበር። ፍርድ ቤቱም ተለዋጭ ቀጠሮውን ሲጨርስ የህሊና እስረኛው አቶ ስንታየሁ ቸኮል እጁን እያውለበለበ ፍርድ ቤቱን መጠየቅ የሚፈልገው ነገር እንዳለ እና እድል እንዲሰጠው ጠይቆ ተፈቅዶለት አቶ ስንታየሁም ማይኩን ጠጋ አድርጎ እንዲህ አለ
” አመሰግናለሁ የተከበረው ፍርድ ቤት! እኛ የህሊና እስረኞች እንደሚታወቀው በፖለቲካው በኩል በሴራ ብንታሰርም ነገር ግን በፈጣሪ ዘንድ ሁሉን ነገር የሚያደርገው ለበጎ ነው። እዚህም ስንመጣ በፈጣሪ ፈቃድ ነው። እኛ ከዚህ በኃላም ልንወጣ የምንችለው በፈጣሪ ፈቃድ ነውና በመካከላችን የንስሃ አባታችን ይገኛሉ እና የተከበረው ድርድ ቤቱ ፈቅዶልን በክርስቶስ መስቀል አባታችን እዚህ ችሎት ውስጥ ሁላችን እንዲያሳልሙን ፍ/ቤቱ ፈቃዱን እንዲሰጠን እጠይቃለሁ። “
አቶ ስንታየሁ ቸኮል ይህን ሲሉ የቃሊቲ/ቅሊንጦ ጠባቂ እና አጃቢ በሙሉ ተነሰሱ እና በችሎቱ ውስጥ ውጥረት ነገሰ። ፖሊሶቹም አበባ እንዳየ ንቭ እኛን ይዞሩን ጀመር። ነገሩ ሌላ ሆነ። በመቀጠልም የግራ ዳኛው ማይካቸውን አብርተው ” አልገባኚም! እስኪ አብራሩልን ሚን ላማለት ፈልጋቹ ኖ!! ” ሲል ያ ጀግና ፅኑው የማይበገረው እስክንድር ዞር ዞር ብሎ ከተመለከት በኃላ ብዲግ ብሎ ተነሳና ማይኩን ተቀብሎ….
” የተከበረው ፍርድ ቤት ያነሳነው ጥያቄ በጣም ቀላል ነው። በተለይም በሰወኛ አስተሳሰብ በጣም ቀላል ነው። አባታችን ሁላችንምም በመስቀላቸው እንዲያሳልሙን ነው የጠየቅነው ወቅቱ የፆም ወቅት ነው የገና ፆም። እናም ለዚህ ነው ይህንን የጠየቅነው። እዛው እስር ቤት መጥተው ማሳለም ይችላሉ በውነት ለመናገር አባታችን!! ነገር ግን ቂሊንጦ ለእርሳቸው ሩቅ ስለሆነ ከመጡ ላይቀር አሳልመውን እንዲሄዱ ፈልገን ነው። የ5 10 ደቂቃ ነገር ነች እና ፍርድ ቤቱ እንዲፈቅድልን እንጠይቃለን። በተለይም ፍ/ቤቱ በሰወኛ እንዲያይው!! “
ይህን ካለ በኃሏ ዳኞች እርስ በእርሳቸው ሌላ ክርክር ውስጥ ገቡ። ፍርድ ቤቱ እርስ በእርስ ንግግር ውስጥ ገበያ መሰለ። ውጥረት በውጥርት። ከ30 ደቂቃ በላይ የጨረሰ የክርክር ጊዜ ካሳለፉ በኃሏ ዳኞች ውሳኔያቸውን በወረቀት ያሰፍሩ ጀመር። እኔም በዚህ ሁነት ውስጥ እራሴን ማግኜቴ ገርሞኝ ለምን እነ እስክንድር ይህንን ጥያቄ ክርክር በታጀበለት መልኩ ማቅረብ ፍለጉ? ሌሎች ጥያቄዎችን ራሴን እየጠየቅኩ በህሊናየ ወደ እንድ ቅዱስ መፅሃፍ ውስጥ ሄድኩ።
” መስቀል ሃይላችን ነው
መስቀል ቤዛችን ነው
መስቀል መዳኛችን ነው
አይሁዶች ይክዱታል
እኛ ግን እንድንበታለን ድነንበታልም።” የሚል ውዳሴ ጀሮየ እያቃጨለብኝ ድንገት ዳኛው ወሳኔያቸውን መናግር ሲጀምሩ ነቃሁ። በውሳኔውም በሁለቱ ዳኞች ፈቃድ በአንደኛው ዳኛ ተቃውሞ እኛ የችሎቱ ታዳሚዎች ከችሎቱ ከወጣን በኃሏ ለ5 ደቂቃ ተፈቀደላቸው። እኛም ከችሎቱ ወጥተን እስክንድር ያነሳው ሀሳብ ሁሌም ለምን ይሆን ተቃውሞ የሚገጥመው!? ከተቃውሞ በኋላ ማሸነፉ ላይቀር!? አይ እስክንድር ነጋ….! እያልን በመጣንበት መንገድ የዘወትር ክርክር እያደርግን ወደመጣንበት መመለሰሱን ተያያዝነው ከጀማው ጋራ።
ለታሪክ እንዲቀመጥ በ15/04/2014 ተፃፈ።