>
5:21 pm - Thursday July 19, 6238

ቲሞቲ ስናይደር - አስደንጋጭና አስገራሚ ትንቢቶቹ - እና የዘመኑ አጣብቂኝ ምርጫ! (አሳፍ ሀይሉ)

ቲሞቲ ስናይደር – አስደንጋጭና አስገራሚ ትንቢቶቹ – እና የዘመኑ አጣብቂኝ ምርጫ!
አሳፍ ሀይሉ
“The Road to Unfreedom –  Russia, Europe, America” 
(Timothy Snyder, 2018)

ይሄ ሰው ማነው? ደራሲውን የምታውቀው ከመሰለህ አልተሳሳትክም፡፡ ከዚህ በፊት «On Tyranny – Twenty Lessons from the Twentieth Century» የሚለውን አስደማሚ መጽሐፉን «አምባገነንነትን ለመውጋት – 20 የሰብዕና ትጥቆች» በሚል ፅሑፍ አጋርቼው ነበር፡፡
ቲሞቲ ስናይደር፡፡ ጥልቅ አሰላሳይ ነው፡፡ ግልጽና ቀጥተኛ ነው፡፡ ሲናገር መሙን አይስትም፡፡ ነፃነትን የሚሰብከውን ያህል፣ ሲጽፍም ነፃነትን ተሞልቶ ነው፡፡ በተለይ በራሺያና በባልካን፣ በምስራቅ አውሮፓ ፖለቲካና ታሪክ ላይ የተራቀቀ አዋቂ ነው፡፡ ከዚህ መጽሐፉ በፊትም፣ «Ukrainian Histories, Russian Politics, European Futures» በሚል ርዕስ ኦሪጂናሉን መጽሐፍ በሁለት ቋንቋዎች በማሳተም (በዩክሬይንና በሩስኪ) ሰፊ ተነባቢነትና አድናቆትን ያገኘ ደራሲም ነው፡፡
ቲሞቲ ስናይደር የቼኮችን ፖለቲካ – በሞትና በህይወት ትንቅንቅ የተቃኘ ሲል ይጠራዋል፡፡ የሶቭየቶችን ወደ ምስራቅ አውሮፓ የተሻገረ ስታሊናዊ የአገዛዝ ዓይነት – በብዙዎች የተኮረጀ ረግጦ የማስገበር ፖለቲካ ይለዋል፡፡ የባልካኖችን አውሮፓዊ የመሆን ምኞትና ፈተና ሰሚ ያጣ ጩኸት ይለዋል፡፡ አይሁዳውያን በናዚዎች እጅ የተቀበሉትን የሆሎካስት ጭፍጨፋ – ዓለም ትምህርት ያልወሰደበት ትልቅ ትምህርት ሲል ያብራራዋል፡፡ አውሮፓ ከሂትለርና ከስታሊን መሐል የወደቀች የደም ምድር እንድትሆን እንዴት እንደፈረደባት – ወይ እንደተፈረደባት – በአውሮፓ ታሪክ መድብሉ ይተነትናል፡፡
ቲሞቲ ስናይደር – የአውሮፓን ታሪክና ፖለቲካ ብቻ አዋቂ አድርገህ አትገምተው፡፡ ውቅያኖስን ተሻግሮ ስለ ሰሜን አሜሪካና አውሮፓ ግንኙነቶች፣ እና አሁን በካርታ ላይ ተሰምረው ስለምናገኛቸው የየሀገሩ ድንበሮች ሲተነትንልህ አፍ ያስከፍታል፡፡ በዚህኛው አዲሱ (በ2018 መጨረሻ የታተመ) መጽሐፉ የአሜሪካኖችን የውስጥ ፖለቲካ – ከትራምፕ የጀርባ ታሪክ ጀምሮ – እስከ ምርጫ ቅስቀሳውና መመረጡ – ከተመረጠም በኋላ በአሜሪካና አውሮፓ ምድር በትራምፕ አማካይነት ስለተፈጸሙ ጉዶች ሲጎለጉል ለጉድ ነው፡፡
ስናይደር ሁሉንም ነገር ለሀሳቡ አስረጅ አድርጎ ሲያጎርፍ ላየው ይደንቃል፡፡ ስነጽሑፎች አይቀሩትም፡፡ ልብወለዶች፡፡ ፊልሞች፡፡ የጋዜጣ ዜናዎች፡፡ የዌብሳይት አርቲክሎች፡፡ የሰዎች የቴሌቪዥን ቃለመጠይቆች፡፡ የግለሰቦች የፌስቡክ ፖስቶች፡፡ የራሺያው የፌስቡክ አምሳያ የ«ቪኮንታክት» ልጥፎች፡፡ የፔንታጎን መግለጫዎች፡፡ የሂላሪ ትዊቶች፡፡ የትራምፕ የምሽት ግብዣ ንግግሮች፡፡ የኤፍ ቢአይ የምርመራ ፋይሎች፡፡ የራሺያ የፀጥታ ቢሮ – የኤፍ ኤስ ቢ – እና የሚሊቴሪ ደህንነት ኤጀንሲ – የጂ አር ዩ – እንቅስቃሴዎች – አይቀሩትም፡፡
የአንጌላ መርከል የጓዳ ንግግሮች – የፑቲን ፈገግታና አግቦ የተሞላው ንግግር – የትራምፕ የኪሳራ ገመና – በቃ የሚቀረው የለም፡፡ ከተጻፈ 200 ዓመት የሞላውን የታወቀ የግጥም መድብልም ሆነ፣ በዩክሬን ጎዳናዎች በሩሲያ ወታደሮች የተዘመረን የወታደር ሀይሎጋ-ሆ ግጥም፣ ወይም በሩሲያ ትያትር ከያኒያን የቀረበን ጀግና-የጀግና-ዘር የሚል ግጥም፣ ምንም አይቀረውም ቲሞቲ፡፡
እጅግ የሚገርም ሁሉን ነገር የመቃረምና – ሁሉንም አጥልሎ – ወደ አንድ ለአንባቢ ወደሚገባ የአስተሳሰብ መስመር የማምጣት ብቃት አለው፡፡ ብዙ ነገሮችን ሰብስቦ – ወደ አንድ ወጥ ወደሆነ ትረካ የመቀየር አቅሙ ለጉድ ነው፡፡ ደግሞ ብዙ ነገሮችን ሲቃርም – በዳሰሳ መልክ አይደለም፡፡ እጅግ ጥልቅ «ክሪቲካል» ሆኖ ነው፡፡
ይህን ዓይነቱን ጥልቅነትና ሁሉን-ዳሳሽነት «the quality of being critical and comprehensive at the same time» በምዕራቡ ዓለም ምሁራን እጅ በተጻፉ መጻሕፍት ሁሉ ላይ በብዛት የሚታይ የሚያስቀና ብቃት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከእነዚህ ምሁራዊ ስራዎች የምንማራቸው ብዙ ነገሮች ያሉ ይመስለኛል፡፡
ቲሞቲ ስናይደር በራሱ አንደበት – የአንድ ሀገር ኤሊቶች – እውነትን ይዘው ሥልጣንን ካልሞገቱ፣ እውነትን ይዘው ጠብመንጃና የፖለቲካ መንበር ያነገቡ ጉልበተኞችን በብዕር ካልሞገቱ፣ ዓለማችን ተመልሳ ወደ እነ ስታሊንና ሂትለራውያን ዘመን መመለሷ አይቀርም ይለናል፡፡ ስለዚህ በየሀገሩ ያሉ ፊደል የቆጠሩና ማገናዘብ የሚችሉ ሁሉ በቻሉት መንገድ በየግዛታቸው ለነገሱት ሥልጣናት አውነት እውነቱን እያፈረጡ ለህዝብ እይታ ማጋለጥ አለባቸው፡፡ «Telling the truth to power equipped with factualities!»፡፡ ይህን በቀደመው On Tyrnanny.. መጽሐፉ ውስጥ የምናገኘውን ጠንካራ አቋሙን ነው በዚህም መጽሐፍ ከመስመሮች መሐል የምናገኘው፡፡
በእርግጥ ደስ ይላል፡፡ ፅኑ፣ ትጉ፣ እና ለእውነት ዘብ የቆሙ ሆኖ መገኘት፡፡ እንደ ቲሞቲ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? ወገንተኝነቱ ደግሞ ለጉድ ነው! የአውሮፓን – በተለይ ካለፉት 8 ዓመታት ወዲህ በዩክሬይን እየተካሄደ ያለውን የራሺያኖችና የዩክሬኖች ታሪክ – ቲሞቲ – እንደ አዲስ እየከለሰ፣ አዲስ ቅርጽና ምክንያት አላብሶት እየጻፈው ነው ማለት ይቻላል፡፡
በዚህ መሐል ቲሞቲ የሚጽፈው ራሺያኖቹ እያደረሱት ያለውን ግፍ ብቻ ነው፡፡ በራሺያኖቹ አዕምሮ ውስጥ ስለሚውጠነጠነው ፀረ-አሜሪካ እና ፀረ-ምዕራባውያን በቀል ብቻ ነው፡፡ ራሺያኖቹ በተቀረው ነጻ ዓለም ላይ ስላወጁት አዲስ ዓይነት የኢንፎርሜሽንና የቴክኖሎጂ ጦርነት ነው የሚጽፈው፡፡
ቲሞቲ የሚናገረው ሁሉ እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙዎቹን ትንተናዎች እያደነቅን እንቀበልለት፡፡ ነገር ግን በአንድ እጅ ነው የሚያጨበጭበው፡፡ ለምሳሌ ቲሞቲ ስናይደር ከሶስትና አራት ዓመት በፊት – በዚህ መጽሐፉ – ራሺያኖች ክሪሚያን ጠቅልለው ብቻ እንደማያቆሙ በስድስት ነጥብ እየደጋገመ ያሰመረበት ጉዳይ ነበር፡፡ አሁንም የሆነው እንደዚያው እርሱ አስረግጦ እንደጻፈው ነው፡፡
እንደ ቲሞቲ ትንተና – ራሺያኖች – በታሪክ የራሺያ አካሎች ናቸው – ነገር ግን በአሜሪካ የሚመራው ምዕራቡ ዓለም ደካማ ጊዜያችንን ጠብቆ የከፋፈለንና የበታተነንን – ኖቮሮሲያ – (በሩስኪ አዲሱ-ራሺያ) የሚባለውን ግዛታችንን ከዩክሬን ወስደን እንጠቀልላለን – ብለው እንደሚያስቡ፣ እንደሚዘጋጁ፣ እንደሚለፍፉ፣ እና ህዝባቸውን ብቻ ሳይሆን ዩክሬን ውስጥ ያሉ ራሺያ ተናጋሪዎችን ሁሉ አሳምነው እንደጨረሱ ይናገራል፡፡ እና ያንን የዩክሬንን ግዛት ሁሉ ሳይጠቀልሉ ራሺያኖች ክንዳቸውን አያጥፉም፡፡
በዚህ ከሶስት ዓመት በፊት በቲሞቲ ስናይደር በተጻፈው መጽሐፉ ውስጥ በትክክል የጠቀሳቸው – ራሺያ በ2014 እንዳደረገችው – በቀጥታ ወታደሮቿን አዝምታ እንደምትወርራቸውና ከእናት ሀገራቸው እንደምታዋህዳቸው የተናገራቸው አሁን በዩክሬን ስር የሚገኙ የኖቮሮሲያ ግዛቶች አሉ፡፡
ለምሳሌ ራሺያ በቅርቡ እውቅና የሰጠቻቸው የዶኔትስክ ሪፓብሊክ፣ እና የሉሃንስክ ሪፓብሊክ (በድምሩ «ዶምባስ» ተብለው የሚጠሩት የደቡብ ምስራቅ የዩክሬን ግዛቶች) አሉ፡፡ ይኸው ቲሞቲ ያለው አልቀረም፡፡ አሁን ይህን ስጽፍ እነዚህ ግዛቶች በነዋሪዎቻቸው ድጋፍና እልልታ ጭምር ታጅበው ወደ ሩሲያ እየተጠቀለሉ ወይም በሩሲያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው፡፡
ቲሞቲ ከሶስት ዓመት በፊት፣ ራሺያ በዚህ ብቻ አታበቃም ብሎ አስረግጦ የነገረን ሌሎችም በዩክሬን ሥር የሚገኙ የኖቮሮሲያ ግዛቶችም አሉ፡፡ የታሪካዊቷ የኦዴሳ ግዛት፣ የሚኮላየቭ ግዛት፣ የኬርሰን ግዛት፣ የድኒፕሮፔትሮቭስክ ግዛት፣ የካርኪቭ ግዛት፣ የዛፖሪዚያ ግዛት፡፡ እነዚህ ሁሉ – ሌላ ቀርቶ ዩክሬንን ተጎራብታ የምናገኛት የትንሿ የሞልዶቫም ደቡባዊ ግዛት – አሊያም ሁለመናዋን ከነነፍሷ፡፡ እነዚህ ሁሉ በራሺያ መጠቅለል አይቀርላቸውም እያለ በእርግጠኝነት ነው የሚናገረው ቲሞቲ ስናይደር፡፡
አሁን እየሆነ ያለውን ስናይ – ቲሞቲ ከሚናገረው ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ እጅግ አስደማሚ ነው፡፡ ቲሞቲ በአንድ ሥፍራ ላይ – በ2014ቱ የዶምባስ ጦርነት ወቅት – ወደ ዩክሬን የዘመቱ የራሺያ ‹‹በጎ-ፈቃደኛ›› የተባሉ ሚሊሻዎች የተናገሩትን እያስታወሰ እንዲህ ይላል፡፡ ወታደሮቹ የሚናገሩት – ከዩክሬን ጋር እየተዋጉ ሳይሆን – ከአሜሪካ ጋር እየተዋጉ እንደሆነ ነው፡፡ ራሳቸውን ከሚመስሉና፣ የራሳቸውን ቋንቋ ከሚናገሩ ጎረቤቶቻቸው ጋር እየተፋለሙ እንደሆኑ ሳይሆን፣ ከአሜሪካ ሶዶማውያን፣ ከአሜሪካ ፋሺስቶችና ከአውሮፓ ናዚዎች ጋር እየተዋጉ እንደሆነ ነው የሚያስቡት፡፡
እንዲያውም – ይለናል ቲሞቲ – አንዱ ወታደር በሄልሜቱ (በብረት ቆቡ) ላይ የተሳለውን የስታሊን ማጭድና መዶሻ ለካሜራው እያሳየ – አሁን በሠይጣኖቹ አሜሪካኖች ላይ 11ኛውን የስታሊንን በትር የምናሳርፍበት እድል እጃችን ላይ ቀርቦልናል፣ ወደኋላ ማለት የለም፣ ዩክሬንን እንደምንበታትነው፣ አሜሪካንንም እንበታትናታለን!
ሌላኛው የራሺያ ወታደር ደግሞ – እኔ የምመኘው ነገር ቢኖር – ይህ የጀመርነው ታላቁ ጦርነት ሲያበቃ – ቀዩን የስታሊንን ባንዲራ በዋሺንግተን ላይ ስናውለበልበው ለማየት ብቻ ነው! ደግሞ ሌላኛው የአየር ኃይል አብራሪ እንዲህ ይላል ይለናል ቲሞቲ – ‹‹እኔ የምመኘው እነዚህ ቲ-50ዎች (ወደ ስቲልዝ ፋይተሩ ጣቱን እየጠቆመ) በዋይትሃውስ አናት ላይ የሚደንሱበትን ቀን ለማየት ነው!››፡፡
ቲሞቲ ስናይደር – ይህ የራሺያኖች ጦርነት – የትልቁ የአውሮፓ ህብረትንና አሜሪካንን ለማፍረስ የሚደረገው ታላቅ ፕሮጀክት – ቅንጫቢው ነው ይለናል፡፡ እና ይህን አስተሳሰብ ለማምጣትና ሕዝቡን ለማስተባበር – በፑቲን የሚመራው የራሺያ ፕሌቶክራሲና የጥቂት ከበርቴዎች ኦሊጋርካዊ አስተዳደር – ብዙ የውሸት ትረካዎችንና ድራማዎችን በሀገሩ ላይ እንደዘራ ይነግረናል፡፡
ቲሞቲ በጣም በመገረም – ራሺያ ወታደሮቿን አሰማርታ ዩክሬንን ስትወራትና በሚሳይሎች ስትደበድባት ዓለም በግልጽ እያየ – አብዛኛው የራሺያ ሕዝብ ግን የሚያምነው – በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ባለውና በዓመት 800 ሚሊየን ዶላር ባጀት በሚመደብለት አር ቲቪ (በራሺያ ቲቪ) የሚነገረውን – ራሺያ ጦርነት ውስጥ ተገዳ የገባችው ራሷን ዳግመኛ በናዚዎችና ፋሺስቶች ከተቃጣባት ወረራ ለመከላከልና – ከጅምላ ጨፍጫፊዎችና ከህጻናት አራጆች ምስኪን ዩክሬኖችን ለማዳን አልማ ነው የሚለውን – ሐሰተኛ የፕሮፓጋንዳ ወሬ ነው – ይለናል፡፡
በአጠቃላይ ቲሞቲ በዚህ መጽሐፉ ይህ የራሺያኖች የዩክሬን ጦርነት በቀላሉ እንደማይበርድ፡፡ ቢበርድም ራሺያ የእኔ ግዛት ናቸው የምትላቸውን የኖቮሮሲያ ግዛቶች ሳትጠቀልል እንደማይበርድ ይገልጻል፡፡ ይህም እጅግ አደገኛ መሆኑን፣ ብዙ ደም እንደሚያፋስስ፣ ብዙ ውድመት እንደሚያስከትል – በዝርዝር ሳያብራራ የሆነ ክፉ ንግርት በሚመስል መልኩ ይናገራል፡፡
ደራሲው ራሺያኖች በማደናገርም ይሁን በወታደራዊ አቅም ዩክሬኖችን ማንበርከክ እንደሚችሉ የሚናገረው ቲሞቲ፣ ታዲያ ለምን ይህ ነገር እንደማይቆምና የብዙዎችን የሰው ልጆች ህይወት እንደሚቀጥፍ ለምን ክፉ ንግርቱን ይለቅብናል? የደነቀኝ ጥያቄ ነው፡፡ ቻይና ብቻ ነች ከዚህ የራሺያ ጦርነት የምታተርፈው፡፡ አሜሪካም፣ አውሮፓም፣ ራሺያም አያተርፉም ይለናል፡፡
ግን ለምን? በምን ምክንያት? ቲሞቲ ስናይደር – የራሺያን እንቅስቃሴዎች ሁሉ ከስታሊንና ከሂትለር ጋር አመሳስሎ በመተረክና በመተንተን አውሮፓውያንና አሜሪካኖች ልክ ሂትለርን ለማስቆም እንደተነሱት – ራሺያኖችን ለማንበርከክ ጦራቸውን ሰንቀው መነሳታቸው አይቀርም፣ እና ይሄ ደም የመፋሰስ ነገር መብረጃ የለውም – እያለ እየተነበየ፣ ወይ እያስጠነቀቀን ይሆን? አላውቅም! ምናልባት ይሆን ይሆናል! ምናልባት ቃላትን በለመደበት ዘዬ ፊት ለፊት ሳያወጣ – ከፊታችን የሚጠብቀን እንደዚያ ያለ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ነው እያለን ይሆናል!
በአጠቃላይ ይህን መጽሐፍ ያየ – በምሁርነት ኃይል መደነቁ አይቀርም፡፡ ምሁር ያለፈውን ያበጥራል፡፡ የዛሬውን ያብጠለጥላል፡፡ የወደፊቱን ይመነጥራል፡፡ ቲሞቲ ስናይደር ለእኔ አንድ ይህን ምሁራዊ ኃይል የታጠቀ አስደናቂ ሰው ነው፡፡ ከአንድ ነገር በስተቀር – ብያለሁ ቀደም ብዬ፡፡ በፍርዶቹ ወደ አንድ ወገን ከማጋደሉ በስተቀር፡፡
እነ አሜሪካ፣ እነ ኔቶ፣ እነ ምዕራብ አውሮፓስ – በራሺያኖች ላይ ያደረጉት፣ እያደረጉት ያሉት፣ እና ወደፊትስ ሊያደርጉ የሚያስቡት ነገር ስለ ምን ለቲሞቲ ስናይደር አልታየው አለ? ስለምን የራሺያኖቹን ስጋት ሁሉ ሌሎችን ለመውረር እንደሚነዛ ሂትለራዊ ፕሮፓጋንዳ ብቻ አድርጎ ይቆጥረዋል?
የኔቶዎችስ ወደ ምስራቅ አውሮፓ መስፋፋት፣ ራሺያኖችን መክበብ፣ የአሜሪካኖች የጦር ሰፈሮች በቻይኖች ዙሪያ መደርደር፣ የዓለም የንግድና የፖለቲካ የዲፕሎማሲ አሰላለፎች ሁሉ – ስለምን በምዕራቡስ ዓለም በኩል እየተከናወኑ ያሉትን እንደ ራሺያኖቹ ያሉ ሸፍጦች ለቲሞቲ የሆነ ተመሳሳይ ፍንጭ በሌላውም አቅጣጫ መኖሩን አላሳዩትም?
ቲሞቲ የዓለማቀፉን የድረገጽ ዓለም ሁሉ ለራሺያኖቹ አዲስ ዓይነት የኢንፎርሜሽንና የሳይበር ጥቃት የተመቻቸ የራሺያኖች መጠቀሚያ የሆነ የአዋቂዎች የጦር አውድማ እንደሆነ ደጋግሞ ይነግረናል፡፡ ግን ይሄንን ዓለማቀፍ የቨርቹዋል ዓለም የዘረጉት እነማን ናቸው? ኢንፎርሜሽንንና ሚስኢንፎርሜሽንን እንደ ዓይነተኛ ሕዝብን የማደናገሪያ፣ እውነቱን የመከለያና፣ ጠላትን እንደማደባያ ስልቶች ቆጥረው የተጠቀሙባቸው፣ ከፍ ወዳለ የልህቀት ደረጃ ያደረሷቸው እነማን ናቸው? ቲሞቲ የሚሞግትላቸው ‹‹ምዕራባውያን››? ወይስ ቲሞቲ የሚረግማቸውና የሚያስጠነቅቀን ራሺያውያን?
በእውነት ዓለም የምዕራቡን ዓለም ፈለግ ብትከተል፣ አሁን በዓለም ላይ ከሰፈነው የሕዝቦች የገቢ አለመመጣጠን፣ የሀይል እርምጃዎች መበርከት፣ የኢኮኖሚ ዝርፊያ፣ የብዙሃን የበዪ ተመልካችነት፣ እና የነጻነትና እኩልነት እጦቶች ትገላገላለች? እውን የምዕራቡ ዓለም የዲሞክራሲ አስተሳሰብና አተገባበር ለዓለም ህዝቦች የነጻነት ጎዳና ተደርጎ የሚሰበክ ነው?
ዓለም ተቃራኒውንስ የእነ ቻይናን፣ የላቲኖችን፣ የአፍሪካኖችን፣ የእነ ራሺያን፣ የአረቡን ዓለም፣ ወዘተ የአገዛዝና የአኗኗር መንገዶች ወደ መከተል ብታዘነብል – እውን ከእውነተኛው የነፃነትና እኩልነት መንገድ እያፈነገጠች ነው ማለት ነው? እውነት ደራሲው ቲሞቲ ስናይደር – በተባ ብዕሩና የማሰብ አቅሙ ተጠቅሞ በመጽሐፉ ለማሳየት እንደሚሞክረው – አንዱ መንገድ ወደ ገነት መግቢያ የሚወስድ የህይወት መንገድ፣ ሌላኛው ግን ወደ ገሃነም ደጆች የሚወስድ የሞት መንገድ ናቸው?
መልሱን ለአንባቢው ትቼ፣ መጽሐፉን ያገኘ እንዲያነበው (ከብዙ አድናቆት ጋር) ጋብዤ፣ የዘርፈ-ብዙ ዕውቀቶችና የበርካታ መጻሕፍት ባለቤት የሆነውን ደራሲውን ከልብ አመስግኜ፣ ለዛሬ አበቃሁ፡፡
ሠላም ለዓለማችን ይሁን!       
ፈጣሪ ኢትዮጵያችንን ይባርክ!
Filed in: Amharic