>
5:14 pm - Wednesday April 30, 2651

በ1925 ዓ.ም ብርሃኑ ዘሪሁን የሚባል ደማም ብዕረኛ አለማችንን በለቅሶ ተቀላቀለ ...!!! (ታሪክን ወደኋላ)

በ1925 ዓ.ም ብርሃኑ ዘሪሁን የሚባል ደማም ብዕረኛ አለማችንን በለቅሶ ተቀላቀለ …!!!
ታሪክን ወደኋላ

ኢትዮጵያ ውስጥ በ1925 ዓ.ም አንድ ታላቅ ሰው ተወለደ። ይህ ሰው እያደገ ሲመጣ የብዙ ሚሊዮን ህዝቦችን ታሪክ፣ ባህል፣ እምነትና አስተሳሰብ የሚገልፅ ደራሲ ለመሆንም በቃ። ብዕሩ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ላይ በሰፊው ያተኩራል። የዚህችን ሀገር ታላላቅ ጀግኖች ታሪክ እያነበበ እና እየመረመረ ለትውልድና ለእናት ምድራቸው ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ውበትና ለዛ ባላቸው የገለፃ ጥበቦቹ እየፃፈ የሚሊዮኖችን መንፈስ ሲያረካ ኖሯል። ኢትዮጵያም ታላላቅ ደራሲዎቿን ማነሳሳት ስትጀምር ስሙ እና ተግባሩ ከፊት ከሚሰለፉት የብዕር አርበኞች መካከል ያደርገዋል። አንዳንድ ሃያሲያን ደግሞ የተዋጣለት የድርሰት ገበሬ ነው ይሉታል። በኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ ለዘላለም እንደ ከዋክብት ሲያበሩ ከሚኖሩት ደራሲያን እና ፀሐፊ- ተውኔቶች ውስጥ ታላቁን የሊትሬቸር ሰው ብርሃኑ ዘሪሁንን በጥቂቱ አነሳሳላችኋለን።
ብርሃኑ ዘሪሁን የተወለደው ድሮ የበጌምድር ጠቅላይ ግዛት ርዕሰ ከተማ በሆነችው እና በተለይም የ17ኛው እና የ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የስልጣኔ ማዕከል እንደነበረች በሚገለፅበት በሰሜናዊቷ ክፍለ -ግዛት በጎንደር ከተማ ነው። ዘመኑም 1925 ዓ.ም ነበር። አባቱ መሪ ጌታ ዘሪሁን መርሻ የሚባሉ ሲሆን እናቱ ደግሞ ወ/ሮ አልጣሽ አድገህ ይባላሉ። አባቱ መሪ ጌታ ዘሪሁን የቤተ-ክህነት ሰው ስለነበሩ እና በዘመናቸውም የተማሩ ስለሆኑ ለልጃቸው ትምህርት የሚጨነቁ ነበሩ። እናም አራት ዓመት ሲሆነው እቤት ውስጥ ከርሳቸው ዘንድ የሚማረው ትምህርት ተጨምሮ የቤተ-ክህነትን ትምህርት ተማረ።
ብርሃኑ ዘሪሁን ጎንደር ውስጥ የሚሰጠውን የቤተ-ክህነት ትምህርት ከተከታተለ በኋላ ወደ ዘመናዊ ት/ቤት ገባ። ይህ ዘመናዊ ት/ቤት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ት/ቤት በመባል ይጠራ ነበር። ብርሃኑ ዘሪሁን የሀገሩ ኢትዮጵያን ባህላዊ፣ ታሪካዊና ኃይማኖታዊ ትምህርቶችን በቤተ-ክህነት ውስጥ ከተከታተለ በኋላ ወደ ዘመናዊ ት/ቤት ሲገባ ልዩ ተሰጥኦው ብቅ አለ። ይህም አንባቢነት ነው። ፈረንጆቹ “Book Worm” እንደሚሉት መፅሐፍን የሚያነብ ብቻ ሳይሆን እንደ ምግብም የሚጠቀምባቸው አይነት ሰው እንደነበር የህይወት ታሪኩ ያወሳል።
ብርሃኑ ዘሪሁንን ቀልቡን ከሚከቡት ታሪኮች መካከል ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው። ኢትዮጵያን በመፃህፍቶቿ አማካይነት እያነበባት አወቃት። እርሱ ያልነበረበትን ዘመን በሰፊ ንባቡ እና ጠያቂነቱ የማንነቱን ክፍተት ሞላው። እናም ሙሉ ኢትዮጵያዊ እየሆነ መምጣት ጀመረ።
የብርሃኑ ዘሪሁንን ቀልብ ከሳቡት ታላላቅ መፃህፍት ውስጥ ደብተራ ዘነብ የፃፏቸው ታሪኮች ናቸው። አንደኛው የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክን የሚያወጣው መፅሀፍ ነው። ደብተራ ዘነብ በቴዎድሮስ ቤተ-መንግስት ውስጥ የነበሩ እና ከቴዎድሮስ ጎን የማይጠፉ የዚያን ዘመን ሊቅ ብሎም ፈላስፋ ናቸው። ታዲያ እርሳቸው የፃፉትን የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ብርሃኑ ዘሪሁን ይወደው ነበር። ከዚህ መፅሀፍ በተጨማሪም ደብተራ ዘነብ “መፅሀፈ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሳዊ” የተሰኘች መፅሐፍ አለቻቸው። ይህች መፅሃፍ ሃይማኖት ላይ መሰረት አድርጋ የተዘጋጀት ከኢትዮጵያ የፍልስፍና ጽሁፎች መካከል አንዷ ናት። ብርሃኑ ዘሪሁን ይህችን መፅሀፍ የመፅሀፎች ሁሉ ቁንጮ አድርጓት በየጊዜው ያነባት ነበር። በነገራችን ላይ ይህች መፅሃፍ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሳዊ በውስጧ ምን ቢኖር እንዲህ የተወደደችው ለሚል ሰው ሁለቱን ነጥቦችን እናንሳ።
መፅሃፏ በዋናነት አላማዋ ሃይማኖትን ማስተማር ቢሆንም፣ የተጻፈችበት ቴክኒክ ግን ፍፁም በተለየ አቀራረብ ነው። ለምሳሌ ፈጣሪን የምትወቅስ እየመሰለች የፈጣሪን ታላቅነት የምታስተምር ናት። እንዲህ የሚል ሃሳብ አለባት “እየሱስ ስራብ አላበላችሁኝም፣ ስጠማ አላጠጣችሁኝም፣ ስታረዝ አላለባሰችሁኝም ይለናል። ለመሆኑ ከርሱ የበለጠ ሃብታም አለ ወይ? ለምን ይጨቀጭቀናል…” እያሉ ደብተራ ዘነብ ጽፈዋል። የደብተራ ዘነብ አፃፃፍ በዚህ ብቻም አያቆምም። እንዲህም የሚል ሃሳብ ያንፀባርቃል። “እንደ አይሁድ ጅል አላየሁም” የአለሙን ጌታ በ30 ዲናር ሸጠው። ወየሁ እኔ ባገኘሁት” እያለ ከተለመደው የስብከት መንገድ ወጥቶ ሌላ የአፃፃፍ እና የአተያይ መንገድ የከፈተ መጽሐፍ ነው። ብርሃኑ ዘሪሁን ደብተራ ዘነበን አእምሮው የተሳለ ፈላስፋ ይላቸው ነበር። እናም ደብተራ ዘነብ የብርሃኑ ዘሪሁንን አእምሮ ገና በልጅነቱ ስለውለታል ማለት ይቻላል።
በነገራችን ላይ ደብተራ ዘነብ የአፄ ቴዎድሮስን ልጅ ልዑል አለማየሁን በቤት ውስጥ የሚያስተምሩ መምህርም ነበሩ።
ብርሃኑ ዘሪሁን በንባብ ልምዱ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ከሚላቸው መካከል ነጋድራስ /ፕሮፌሰር/ አፈወርቅ ገ/እየሱስን ነው። እርሳቸውም በኢትዮጵያ የታሪክ እና የልቦለድ ጽሁፍ ውስጥ ከከፍተኛ ተዕዕኖ ፈጣሪ በመሆናቸው የብርሃኑ ዘሪሁንን የልጅነት እውቀት በመፃፍቶቻቸው አስፍተውለታል። የእነብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ስላሴ እና የክብር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል መፃህፍት ኢትዮጵያዊ እውቀቱን በከፍተኛ ደረጃ እንዳጎለመሱለት ይነገራል።
ብርሃኑ ዘሪሁን በ1945 ዓ.ም ላይ ብዙ እውቀቶችን ከገበየበት ጎንደር ከተማ ተነስቶ አዲስ አበባ መጣ። በአዲስ አበባም ቆይታው ተግባረ ዕድ ት/ቤት ገብቶ የሬዲዮ ቴክኒሻንነት በመማር በ1948 ዓ.ም ላይ በዲፕሎማ ተመረቀ። ታዲያ በዚያ በምረቃ ወቅት ከተማሪዎቹ ሁሉ አንደኛ ወጥቶ ተሸላሚ የነበረው ብርሃኑ ዘሪሁን ነው።
ብርሃኑ ዘሪሁን ተግባረ ዕድ ት/ቤት ሲማር የታላላቅ የአለማችንን ደራሲያን ስራዎችን ለማንበብ ዕድሉን አገኘ፡ የነ ዊሊያም ሼክስፒርን፣ የአሌክሳንደር ዱማስ ፔሬን፣ የቻርልስ ዲክነስን፣ የነ አሌክሳንደር ፑሽኪንን እና የሌሎችንም መፃህፍት አነበበ። እውቀቱንም እያስፋፋ መጣ። በንባብ የተከማቸው እውቀቱም በፅሁፍ መውጣት ጀመረ። እዚያው ተግባር-ዕድ ት/ቤ ሲማር የት/ቤቱ ልሳን የነበረችውን “ቴክኒ-ኤኮ” የምትሰኘውን መፅሄት አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል። ከዚህ በተጨማሪም እዚያው ተማሪ ሳለ በ1947 ዓ.ም ተውኔት ጽፎም አሳይቷል። እናም እንግዲህ በኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ሊወስድ ብርሃኑ ዘሪሁን የሚባል ብዕረኛ ወደ አደባባይ ብቅ ማለት ጀመረ።
ብርሃኑ ዘሪሁን ተግባረ ዕድ ውስጥ ውጤቱ ከፍተኛ ስለነበር እዚያው ት/ቤት ውስጥ ተቀጠረ። ከት/ቤቱ ውስጥም ሆኖ ለተለያዩ ጋዜጦች ይፅፍ ነበር። ከተግባረ ዕድ ት/ቤት በመልቀቅ በወቅቱ አጠራር የጦር ሚኒስቴር በአሁኑ መከላከያ ሚኒስቴር በሚባለው መስሪያ ቤት በአስተርጓሚነት ተቀጥሮ መስራት ጀመረ። እዚያም ብዙ ሳይሰራ 1952 ዓ.ም ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተዘዋወረ።
ብርሃኑ ዘሪሁን ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ወዲያው “የኢትዮጵያ ድምጽ” ተብሎ በሚታወቀው ጋዜጣ ላይ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሰራ። ታዲያ በዚህ ወቅት ጋዜጣዋን ታዋቂ ከማድረጉም በላይ በብዙዎች ዘንድ የሚነበቡ መጣጥፎችን እና ታሪኮችን በመፃፍ ዝነኛ እየሆነ መጣ። ቀጥሎም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ተዘዋወረ። ብርሃኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያዊያን አንባቢያን ልብውስጥ ሰተት ብሎ ገባ። በአንድ ጊዜ ስሙ እና ዝናው እየናኘ መጣ። ብርሃኑ ዘሪሁን በድርሰት ዓለም ውስጥ በተለይ በ1958 ዓ.ም አዲስ የታሪክ አብዮት ማቀጣጠል ጀመረ። “የቴዎድሮስ ዕንባ” የሚሰኝ መፅሐፍ አሳተመ። መፅሀፉ የአፄ ቴዎድሮስን አነሳስ እና ለኢትዮጵያ ያላቸውን ርዕይ ብሎም የመጨረሻውን የህይወት ፍፃሜ የሚያሳይ ነበር። በወቅቱ ማለትም ብርሃኑ ይህን መፅሀፍ ከማዘጋጀቱ በፊት የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ በጭካኔያቸው ላይ ተመስርቶ ብቻ የሚዘጋጅ በመሆኑ የቴዎድሮስን ውስጣዊ ስብዕና ያን ያህል ጎልቶ አይነገርም ነበር። እናም ብርሃኑ ዘሪሁን አፄ ቴዎድሮስ ብሔራዊ ጀግና መሆናቸውን የሚገልፅ ድርሰት ፅፎ በማቅረቡ በዘመኑ በጣም ታዋቂ ሆነ። ይህን “የቴዎድሮስ ዕንባ” የተሰኘውን ታሪክ መስፍን አለማየሁ ወደ መድረክ ቀይሮት በኢትዮጵያ የቴአትር አለም ውስጥም ከታላላቅ ቴአትሮቹ ተርታ የሚሰለፍ አድርጎታል።
በቴአትሩ ውስጥ የእንግሊዙ ቆንሲል አፄ ቴዎድሮስን እንዲህ ይላቸዋል “ጃንሆይ እኔ ተልኬ የመጣሁት ከታላቋ የብሪታኒያ የጦር ጀነራል ከናፒር ዘንድ ነው” ይላቸዋል።
ቴዎድሮስም “እና ምን ይዘህ መጣህ” አሉት።
መልዕክተኞች “ጃንሆይ ጦርነቱ እየከፋ ስለመጣ በሰላም እጅዎን ለታላቋ የብሪታኒያ መንግስት እንዲሰጡ ነው። እጅዎን በሰላም ከሰጡ የእንግሊዝ መንግስት በእንክብካቤ ይይዝዎታል” ይላቸዋል።
ቴዎድሮስም “ኧ ኧ ኧ ኧ ብለው የምፀት ሳቅ ከሳቁ በኋላ “ስማ! እኔ እንደ ፈረንጅ ጅል አላየሁም! መንጋ መሳፍንት እና መኳንንት ያንቀጠቀጠ ነበልባል እጄን ልያዘው አለ? የሚፋጅ የእሳት አሎሎ ነው በለው! ደግሞ . . . እጅህን ብትሰጥ በክብር ትያዛለህ ይለኛል። በየት አገር ነው እስረኛ በክብር የሚያዘው? ወይስ በሌላ የአፍሪካ ሀገር እንደለመዱት እኔን እስረኛ አድርገው ሀገሬ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ሊይዙ? እኔ እንደሁ ህይወቴ እያለች ሀገሬ ኢትዮጵያን ከጥቁር ዘራፊ አውጥቼ ለነጭ ዘራፊ አልሰጥም ብሎሃል በለው! ሂድ ንገረው! ውጣ!” እያሉ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር የሚገልፁበት ታሪካዊ ተውኔት ነው።
አፄ ቴዎድሮስ ወታደሮቻቸውን ሁሉ ከነ መሳሪያቸው ካሰናበቱ በኋላ ራሳቸውን ሊያጠፉ በሚወስኑበት ወቅት ባለቤታቸው እቴጌ ጥሩወርቅ እንዲህ አሏቸው።
“ኧረ በለአማየሁ፣ በአለማየሁ ይሄን ሃሳብዎን ይተው!” ይሏቸዋል።
ቴዎድሮስም “ለአለማየሁ ምንም የማወርሰው ነገር የለኝም። ብቻ ሲያድግ አባትህ አንዲት ኢትዮጵያ በአይኑ እንደዞረች ሞተ ብለሽ ንገሪው”
በእንዲህ አይነት ሀገራዊ ፍቅር የታጀቡት የብርሃኑ ዘሪሁን የአፃፃፍ ቴክኒኮች ዘመን ሰበር ታሪኮች ሆነው ዛሬም እናወጋቸዋለን።
ብርሃኑ ዘሪሁን በድርሰት ዓለም ውስጥ ሲያዥጎደጉዳቸው ከነበሩት መፃሐፍት መካከል በ1961 ዓ.ም “የእንባ ደብዳቤዎች” በሚል ርዕስ ያሳተመው በሰፊው የተነበበለት ሲሆን ከዚያም በመለጠቅ “ድል ከሞት በኋላ ነው” የሚለውም መፅሐፉ እንዲሁ በወቅቱ ይቀነቀን የነበረውን ተራማጅ እንቅስቃሴ የሚያቀጣጥል ነበር። “የበደል ፍፃሜ” እንዲሁም “ጨረቃ ስትወጣ” የተሰኙትም መፅሐፍቶቹ በኢትዮጵያ ስነ-ፅሁፍ ውስጥ የብርሃኑ ዘሪሁንን ስም እናማንነት እየገነቡ የመጡ ስራዎቹ ናቸው። ብርአምባር ሰበረልዎ የተሰኘው መፅሐፉም ታትማ ስትወጣ አምራች ደራሲነቱን /Productive Author/ የሚል ቅፅል አሰጥታዋለች።
በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሶስት ተከታታይ የሆኑ መፃሐፍትን በማሳተም ረገድ ብርሃኑ ዘሪሁን በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ አለም ውስጥ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ይጠቀሳል። በ1970ዎቹ ውስጥ ብርሃኑ ዘሪሁንን በሥነ-ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ስሙ እንዲነሳለት ያደረጉት እነዚህ ሶስት መፅህፍቶቹ “ማዕበል የአብዮቱ ዋዜማ”፣ “ማዕበል የአብዮቱ መባቻ” እና “ማዕበል የአብዮቱ ማግስት” ይሰኛሉ። መፅሐፎቹ በአንድ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ወሎ ውስጥ ተከስቶ በነበረው የረሃብና የድርቅ አደጋ ላይ ተመስርቶ የፃፋቸው ውብ መፅሀፎቹ ናቸው። እንዲህ አይነት ሶስት መፃህፍትን ፈረንጆቹ /Trilogy/ ይሏቸዋል። እናም በኛ ሀገር ደግሞ “ስልስ ድጉስ” ብለው የተረጎሙት ሰዎች አሉ። ብርሃኑ ዘሪሁን የስልስ ድጉስ መፃሐፍትም ደራሲ ነው።
ብዙም ሳይቆይ ደግሞ በኢትዮጵያዊያን የመፃህፍት አንባቢያን ዘንድ በእጅጉ የተወደደውን እና በተደጋጋሚ የታተመውን መጽሐፍ በ1978 ዓ.ም አሳተመ። መፅሀፉ “የታንጉት ምስጢር” ይሰኛል። በአፄ ቴዎድሮስ ዘመድ በታንጉት እና በቴዎድሮስ የጦር አበጋዝ በሆነው በፊታውራሪ ገብርዬ ጎሹ መካከል ያለውን ፍቅር እና የዘመኑን ታሪክ የፃፈበት ውብ ድርሰት ነው። ሶስቱን ማዕበሎች እና የታንጉት ምስጢርን በኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ ድንቅየው ተዋናይ ወጋየሁ ንጋቱ በመተረኩ ከህዝብ አእምሮ እና ልቦና ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።
ብርሃኑ ዘሪሁን ከደራሲነቱ ባሻገር ፀሐፊ-ተውኔት ነው። የቴአትር ፅሁፎችን በማዘጋጀት እና በኢትዮጵያ መድረክ ላይ ግዙፍ ሰብዕና የሰጡትን ስራዎች አቅርቧል። ከቴዎድሮስ እንባ በኋላ በ1972 ዓ.ም “ሞረሽ” የተሰኘ ተውኔት በብሔራዊ ቴአትር ቤት አቅርቧል። በ1975 ዓ.ም ደግሞ “ጣጠኛው ተዋናይ” የተሰኘ ተውኔት በሐገር ፍቅር ቴአትር ቤት አቅርቧል። በ1976 ደግሞ “የለውጥ አርበኞች” የተሰኘ ተውኔት ጽፏል። በኢትዮጵያ የታሪክ ተውኔቶች አለም ውስጥ በዘመን አይሽሬነታቸው ከሚጠቀሱት ቴአትሮች መካከል “ባልቻ አባነፍሶ” የተሰኘው ቴአትር ነው። ይህን ቴአትር በ1977 ዓ.ም የፃፈው ይኸው ጎምቱ ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን ነው።
ብርሃኑ ዘሪሁን ከደራሲነቱ እና ከፀሐፊ ቴውኔትነቱ ባሻገር ሃያሲም ነበር። የተለያዩ ደራሲያንን ስራዎችን ፅሁፎችን እየተከታተለ ሂሳዊ መጣጥፎችን ያቀርብ ነበር። ከዚህ በላይ ደግሞ የተዋጣለት ጋዜጠኛ ሆኖ በዘመኑ በብዕሩ የናኘ ስብዕና የተጎናፀፈ ሰው ነበር።
ይህ የድርስት ገበሬ ስራዎቹ በበርካታ የስነ-ጽሁፍ እና የታሪክ ተመራማሪ በሆኑ ምሁራን ጥናት ተደርጎባቸዋል። የዩኒቨርስቲ የመመረቂያ ጽሁፎችም ሆነው በርካቶችን አስመርቀዋል። ሞልሸር የተባለው የኖርዌይ ዜጋ እና የኢትዮጵያን ደራሲዎች ታሪክ Black lions በሚል ርዕስ የፃፍው ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁንን ከኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን ተርታ ያስቀምጠዋል። ብርሃኑ ዘሪሁን ተግቶ በማንበቡ እና በመመራመሩ በኢትዮጵያ ሥነ -ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ለትውልድ ውለታ ውለው ካለፉ ጥበበኞች መካከል አንዱ ሆኖ ይጠራል። ሀገርን እና ትውልድን በብዕሩ ቀለማት ሲዘክር የኖረው ይህ ሰው ሚያዚያ 16 ቀን 1979 ዓ.ም በ54 ዓመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየ። ቀብሩም በባለወልድ ቤተ-ክርስቲያን ተፈፀመ። ዛሬ በአፀደ ስጋ ከኛ ጋር ባይኖርም ስራዎቹ ግን ዘመንን እየተሻገሩ ገና ወደፊትም ስሙን ያስጠሩታል።
Filed in: Amharic