>
5:21 pm - Wednesday July 19, 1905

"በተማሪዎች ንቅናቄ ጊዜ ከተፈበረከ ውሸት ነፃ መውጣት ትልቁ ብሔራዊ ተልዕኳችን ነው...!!!" (አቶ እስክንድር ነጋ፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት)

” አዲስ አበባ ውስጥ ኦሮሚኛ የሥራ ቋንቋ ይሁን ከተባለ፣ አማርኛ ኦሮሚያ ውስጥ በክልል ደረጃ የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት፡፡
 
“በተማሪዎች ንቅናቄ ጊዜ ከተፈበረከ ውሸት ነፃ መውጣት ትልቁ ብሔራዊ ተልዕኳችን ነው…!!!”
አቶ እስክንድር ነጋ፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት
 ሪፓርተር 

ኢሕአዴግ በ1983 ዓ.ም. ሥልጣን ላይ ሲወጣ ወዲያውኑ ለሕዝብ መድረስ ከጀመሩ የፕሬስ የኅትመት ውጤቶች ውስጥ አንዱን ካስጀመረ በኋላ፣ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ጠፍቶ አያውቅም፡፡ በጋዜጠኝነት የተጀመረው ጉዞው ገጽታውን እየቀያየረ አሁን ወደ ፖለቲከኝነት አድርሶታል፡፡ በጋዜጠኝነቱም ሆነ በፖለቲካው ከእስር ቤት ደጃፍ ያልራቀው አቶ እስክንድር ነጋ፣ ታኅሳስ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. በገና በዓል ምሽት ከእስር ቤት ወጥቶ በቀጥታ የፖለቲካ እንቅስቃሴውን ቀጥሏል፡፡ በ2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተመሠረተውና በፕሬዚዳንትነት የሚመራው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲም ወደ አገር አቀፍ ፓርቲነት ሊያድግ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት ሒደት ላይ ነው፡፡ ሳምሶን ብርሃኔና አማኑኤል ይልቃል ከአቶ እስክንድር ነጋ ጋር ስለፖለቲካ ጉዞውና አጠቃላይ ምልከታው ያደረጉት ቃለ መጠይቅ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡
ሪፖርተር፡- የመጀመሪያ ጋዜጣህ የሆነችውን ኢትዮጲስ እንዴት ነበር የጀመርካት? ምን አነሳሳህ?
አቶ እስክንድር፡- ለብዙ ጊዜ የኖርኩት፣ እንደ አጋጣሚ ስመለስ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ነበር፡፡ በጊዜው ብዙ መጽሔቶችና ዕይታ የምትባል አንዲት ጋዜጣ ነበሩ፡፡ መጽሔቶቹም ዳር ዳር ነበር የሚሉት፣ ፊት ለፊት ወጥተው መንግሥትን ለመተቸት ድፍረቱን አላገኙም ነበር፡፡ እኔ የተለየ ድፍረት ኖሮኝ ወይም አንዳንዶች እንደሚሉት ጀብደኛ ሁኜ ሳይሆን፣ አሜሪካ ውስጥ ነፃ ፕሬስ ምን እንደሆነ አውቅ ስለነበር እዚያ ያለውን ተሞክሮ ወደዚህ አመጣሁት፡፡ አሜሪካ ጋዜጣ ላይ አልሠራሁም፡፡ ግን እንደ ማንኛውም ሰው አነብ ስለነበር ዓውዱን አውቃለሁ፡፡ እዚህ መጥቼ ኢትዮጲስ ጋዜጣን ከጀመርኩ በኋላ ፊት ለፊት መንግሥትን ለመተቸት የደፈረው የእኔ ጋዜጣ ነበር፡፡ በዚያ መልክ ነው እስከ ጥቅምት 1998 ዓ.ም. የቀጠልነው፡፡ ከዚያ በኋላ ከመንግሥት፣ ከሕወሓት ጋር አንድም ቀን ሰላም ኖሮን አያውቅም፡፡ ብዙ ውጣ ውረድ ነበረው፡፡ አሥር ዓመት ታስሬያለሁ፣ ብዙ ዓይነት የአካል ድብደባ ተፈጽሞብኛል፡፡ ተዘቅዝቆ ከመገረፍ እስከ እጅ መውለቅ ድረስ፡፡ ግን በዚያ ዘመን ውስጥ የነበረኝ ተሳትፎ በጋዜጠኝነት ብቻ የተወሰነ ነበር፡፡ ያኔ ሕወሓት ነበር አሁን ኦሕዴድ ነው ያለው፡፡ ኦሕዴድ ወደ ሥልጣን ከወጣ በኋላ ደግሞ አንድ ዓመት ተኩል ጨምሮልኛል፡፡ በጥቅሉ 11 ዓመት ተኩል ታስሬያለሁ ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለመጀመሪያ ጊዜ የታሰርከው ‹‹ፋሺዝም በትግራይ›› በሚል ርዕስ ከወጣ ጽሑፍ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ‹‹ፋሺዝም በትግራይ›› ልትል የቻልክበት ምክንያት ምንድነው? መታሰሬ ተገቢ ነበር ትላለህ?
አቶ እስክንድር፡- ‹‹ፋሺዝም በትግራይ›› የሚለው ሁለተኛ ዕትም ነበር፡፡ የመጀመሪያ ዕትም ‹‹ጭፍጨፋ በስድስት ኪሎ›› የሚል ነበር፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኤርትራ መገንጠልን በመቃወም ተማሪዎች ወጥተው መንግሥት ተኩሶ ገድሏቸው ስለእነሱ ያወጣነው ዘገባ ነበር፡፡ ይኼ ጽሑፍ መንግሥት አስቆጥቶ ነበር፡፡ ‹‹ፋሺዝም በትግራይ›› እዚህ ላይ ተጨመረ፡፡ ነፍሱን ይማረውና ተፈራ አስማረ የሚባል  ዋና አዘጋጅ ነበር፣ እኔ ያኔ አሳታሚ ነበርኩ፡፡ ጋዜጠኝነቱን ግን አብረን ነበር የምንሠራው፡፡ ‹‹ፋሺዝም በትግራይ›› ልንል የቻልነው በስሜት ወይም የነበረው መንግሥት ላይ ጥላቻ ስለነበረን አይደለም፡፡ መሬት ላይ የነበረው ሁኔታ ይኼንን ያመላክት ስለነበረ ነው፡፡ በሰዓቱ በትግራይ ውስጥ ከሕወሓት ውጪ የሌላ ፖለቲካ ድርጅት አባል ሆነህ ከተገኘህ መታሰሩ ቢቀር ከዕድር ትባረራለህ፡፡ የዕቁብ አባል መሆን አትችልም፣ ሰው ካንተ ጋር ማውራት ይፈራል፣ ቤትህ መምጣት ይፈራል፡፡ በአጠቃላይ ከማኅበራዊ ሕይወትህ እንድትገለል ነው የምትደረገው፡፡ በጊዜው የነበረው የትግራይ ሰው ‹‹ደርግ ወድቆ ሸዋ ነፃ ሲወጣ ትግራይ የባሰ ነገር አጋጠማት›› የሚለው ነገር ነበር፡፡ በትግራይ ውስጥ የነበረው ሁኔታ ‹‹ቶታሊተሪያኒዝም›› ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ነበር፡፡ ይኼም ማለት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴህን መቆጣጠር የሚፈልግ መንግሥት ነበር፡፡ ፖለቲካው ውስጥ ገብተህ እንዳትቃወመው ብቻ ሳይሆን የዕለተ ዕለት እንቅስቃሴህ ውስጥ መግባት የሚፈልግ አስተዳዳር ነበር፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ደግሞ ‹‹አውቶሪተሪያኒዝም›› ነበር የነበረው፡፡ ልዩነቱን በቀላሉ ለመግለጽ፣ ትግራይ ውስጥ ነፃ ፕሬስ/የግል ፕሬስ የሚባል ነገር አይታሰብም፡፡ አዲስ አበባ ግን ለይስሙላም ቢሆን የግል ፕሬስ ማሳተም ይቻል ነበር፡፡ አዲስ አበባ ደርግ ከወደቀ በኋላ ዴሞክራሲ ያለ ማስመሰል ያስፈልግ ስለነበር ከትግራይ የተሻለ ሁኔታ ነበር፡፡ ያንን ለመግለጽ ነው ‹‹ፋሺዝም በትግራይ›› ያልነው፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን አንተ እንደምትነግረኝ ‹‹ፋሺዝም በትግራይ›› የተጻፈው የትግራይ ሕዝብ ሐሳቡን በነፃነት እንዳይገልጽ በመደረጉ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚያ በኋላ አንድ የሚነሳብህ ወቀሳ አለ፡፡ ‹‹ወግድ ይሁዳ›› የሚባል በታዲዮስ ታንቱ የሚጻፍ ዓምድ ነበር፡፡ በዚህ ዓምድ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች አንድን ብሔር በተለይ የትግራይ ተወላጆች የሚያንቋሽሹ ነበሩ የሚል ወቀሳ ይነሳብሃል፡፡ ይኼ አሁን ከነገርከን ጋር አይጣረስም?
አቶ እስክንድር፡- አዎ በጣም ይጣረሳል፡፡ አሁን ደግሞ ፀረ ኦሮሞ ተብያለሁ፡፡ ስለዚህ ዓውዱ ተቀይሯል፡፡ ምን ለማለት ፈልጌ ነው? አምባገነነኖች ሁልጊዜ ጠንከር ያለ ታቃውሞ ሲያጋጥማቸው ተቀፅላ መጠሪያ ያወጣሉ፡፡ በነገራችን ላይ ‹‹ወግድ ይሁድ›› በሚጻፍበት ጊዜ ወግድ ይሁዳን የሚቃወም ጽሑፍ ሁሌም ከጎኑ አለ፡፡ ማንም ሰው ጽሑፉ ይወጣ የነበረበት አስኳል ጋዜጣ ላይ ሄዶ መመልከት ይችላል፡፡ ‹‹ወግድ ይሁዳን›› እየጠቀሰ የሚቃወም ጽሑፍ ሁሌም ነበር፡፡ ‹‹ወግድ ይሁዳ›› ሲጀምርና በተስተናገደበት በአብዛኛው ጊዜ ሲያውጠነጥን የነበረው በታሪክ ላይ ነው፡፡ በአፄ ዮሐንስ ላይ ያውጠነጥን ነበር፡፡ ይኼንን ጊዜ ነቅሶ ያወጣበት ምክንያት እንግሊዝ ኢትዮጵያን ሊወር ወደ መቅደላ ሲመጣ የአፄ ዮሐንስ ጦር ሀማሴን ላይ ስለተቀበላቸው ነው፡፡ ከሀማሴን ተቀብሎ መንገድ እየመራ አፄ ቴድሮስ ጋ ወስዶ አፄ ቴድሮስ በዚህ ምክንያት ሞተዋል፡፡ ታድዮስ ታንቱ ‹‹ይኼ ክህደት ነው›› ነበር የሚለው፡፡ ክህደት የተጀመረበት ባህል ምንጩ ከዚያ ነው፡፡ እሱን መለየት አለብን ነው የሚለው፡፡ አሁን የክህደት ባህል መጥቷል፣ በዚህም ኢትዮጵያ ልትፈርስ ጫፍ ላይ ደርሳለች፡፡ የዚህን ምንጭ ስንፈልግ ይኼንን ታሪክ በአግባቡ አላየነውም የሚል ነው የክርክሩ ምሁራዊ መሠረት፡፡ ሕወሓትም የዚህ የክህደት ታሪክ ውጤት ነው፡፡ ሕወሓትን ከዚህ ነጥለን ማየት የለብንም፡፡
ሪፖርተር፡- ይኼ የአፄ ዮሐንስ ታሪክ የጋራ ታሪክ ነው ብለህ ነው የምታምነው? ወይስ ኃላፊነቱ ሁሉ አንድ ሕዝብ ላይ የሚጫን ነው?
አቶ እስክንድር፡- በዚያ ጊዜ እንግሊዞች ሲመጡ የተቀበሏቸው በዝብዝ ካሳ በሚለው ስም ይታወቁ የነበሩት አፄ ዮሐንስ ሆኑ እንጂ አብረው የተባበሩ ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ እንግሊዞች ዋግ ላይ ሲደርሱ የተቀበሏቸው ሳይነግሡ ዋግ ሹም ይባሉ የነበሩት አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ነበሩ፡፡ እሳቸው ናቸው አሻግረው መቅደላ ላይ ያደረሷቸው፡፡ ስለዚህ የእኛ የጋራ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው፡፡ ብቸኛው ተዋናይ በዝብዝ ካሳ ብቻ አልነበሩም፡፡ በደንብ ግን አልተመለከትነውም፡፡ እኔ በዚህ አምናለሁ፣ ለዚህም ነው ያንን ስህተት የደገምነው፡፡ ይኼንን በማሰብ ነው ጽሑፉ እንዲስተናገድ የፈቀድኩት፡፡ በነገራችን ላይ ‹‹ወግድ ይሁዳ›› ላይ ጽሑፎች ሲወጡ እያንዳንዱን መስመር ዓይቼ አላወጣሁም፣ ላደርገው የምችለው ነገር አይደለም፡፡ ሦስት ጋዜጣ ነበር ኤዲት የማደርገው በሰዓቱ፣ በጣም ጥቂት ሰው ነበር፡፡ የሽምቅ ጋዜጠኝነት ነው የምንለው በወቅቱ የነበረውን፡፡ በአንድ እጃችን ከመንግሥት ጋር እየተፋለምን ነበር፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሀብትና የሰው ኃይል እጥረትም ነበረብን፡፡ በዚህ ችግር ውስጥ ስለነበርን እኔ ሳላያቸው ያለፉ ነገሮች አሉ፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ መባል ያልነበረባቸው ነገሮች አላለፉም ብዬ አልከራከርም፡፡ ዓላማው ግን የትግራይን ሕዝብ ጥላሸት መቀባት አልነበረም፡፡ እንዳልኩት ደግሞ ሚዛኑን ለመሥራት ያንን ጽሑፍ የሚቃወም ጽሑፍ ሁልጊዜ ነበር፡፡ በእርግጠኝነት ግን የትግራይ ሕዝብ ጠላት አልነበርኩም፣ አይደለሁም፣ ልሆንም አልችልም፡፡ አሁንም በዚያው ልክ የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት አልነበርኩም፣ አይደለሁም፣ ልሆንም አልችልም፡፡ በነገራችን ላይ ታዲዮስ ታንቱ ፖለቲካ ውስጥ የገባው የጎሳ ፖለቲካን ለመቃወም ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ኢትዮጵያን የሚያጠፋ ነገር ነው፣ እየተቀጣጠለ ያለውን የጎሳ ፖለቲካ ላይ ቤንዚን የሚያርከፈክፈው ደግሞ ሕወሓት ነው ብሎ ሕወሓትን የታገለ ነው፡፡ ምንድነው ለዚህ መፍትሔው ስትለው፣ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ እንደተደረገው የጎሳ ፖለቲካ መታገድ አለበት ይላል፡፡
የጎሳ ፖለቲካውን የሚያቀጣጥለው ሕወሓትን ደግሞ ለብቻው እንደቆመ ክስተት አድርገን መመልከት የለብንም፡፡ ሕወሓት የተቀዳበት ምንጭ ታሪክ አለው፡፡ ይኼ ታሪክ ደግሞ ከእንግሊዙ ወረራ ጀምሮ የሚመጣ ነው፡፡ ይኼንን መመልከት አለብን የሚል ነው፡፡ የቀረበው ግን አሁን እኔ ባስቀመጥኩት መልኩ ነው? አይደለም፡፡ ጋዜጣው ላይ ይወጡ ለነበሩ ነገሮች እኛም እሱም ኃላፊነት አለብን፡፡ ነፃ መድረክ ነው ብለን ልቅ አድርገን ልንተወው አንችልም፡፡ እሱም ሲጽፍ ስህተት ሊሠራ ይችላል፣ እኛም ኤዲት ስናደርግ ስህተት ሠርተን ሊሆን ይችላል፡፡ በዚያ ሒደት ውስጥ ስህተት አልተሠራም ብዬ አልከራከርም፡፡ የተሠራ ስህተት ሊኖር ይችላል፣ ለተሠራው ስህተት ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ የተሠራ ስህተት ካለ፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን የትግራይን ሕዝብ በጠላትነት ለመፈረጅ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- በጋዜጠኝነት ሥራህ ሽልማቶችን ወስደሃል፡፡ ብዙ ሰዎችም ለጋዜጠኝነት ብዙ ዋጋ መክፈልህን ይናገራሉ፡፡ አንዳንዶች አቶ እስክንድር ጋዜጠኛ አይደለም፣ ወደ አክቲቪዝሙና ፖለቲካው ያደላል ይላሉ፡፡ አንተ ለጋዜጠኝነት ሙያ ምን አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ ብለህ ታስባለህ?
አቶ እስክንድር፡- ይኼ ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጋዜጠኝነትን በትክክል መተግበር የሚቻለው በዴሞክራሲያዊ ዓውድ ውስጥ ነው፡፡ የጋዜጠኝነትን ሥነ ምግባር ለመተግበር ዴሞክራሲያዊ ዓውድ የሚል ቅድመ ሁኔታን ይጠይቃል፡፡ ይኼ በሌለበት ንፁህ ጋዜጠኝነትን እተገብራለሁ ስትል መጀመሪያ የሚገጥምህ ተግዳሮት ነው፡፡ ያለው ሥርዓት የሚጣላህ የጋዜጠኝነትን ሥነ ምግባር ስላልተከተልክ አይደለም፡፡ የሚጣላህ እውነትን ስለማይፈልግ ነው፡፡ ስለዚህ ጋዜጠኝነትን ለመተግበር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግዴታ ነው፡፡ አድሎአዊ ስለሆንክ አይደለም ከመንግሥት ጋር የምትጣላው፡፡ አምባገነናዊ ሥርዓት ጋዜጠኝነትን ስለማይቀበል ነው፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ የሚገጥምህ ተግዳሮት ሙያህን ተግባራዊ ማድረግ አትችልም የሚል ነው፡፡ ሙያህን ተግባራዊ ማድረግ ሲያቅትህ የመጀመሪያ ሥራህ የሚሆነው መብትህን ማስከበር ነው፡፡ በዚህም አክቲቪስት ለመሆን ትገደዳለህ፣ መሬት ላይ ያለው ሁኔታ አስገድዶህ፡፡ የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ያለፈው በዚህ ሒደት ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያ ዓላማ ጋዜጠኝነትን መሥራት ነበር፡፡ ‹‹ፋሺዝም በትግራይ›› ብለን ባወጣን በሁለተኛው ዕትም ግን እስር ቤት ገባሁ፣ ድብደባ ተፈጸመብኝ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደበደብኩት በ‹‹ፋሺዝም በትግራይ›› ነው፣ ማዕከላዊ ውስጥ፡፡ ከዚያ በኋላ የእኔ ጥያቄ የሆነው ኅብረተሰቡ ያለው መብት ይከበር የሚል አይደለም፡፡ የእኔ መብት ይከበር የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ጋዜጠኝነቱን በአንድ እጅ አክቲቪዝሙን ደግሞ በሌላ እጅ ይዤ ለመሄድ ተገደድኩ፡፡ እኔ እንደ ግለሰብ ባወራም ይኼ በአጠቃላይ የነፃ ፕሬሱ ተሞክሮ ነው፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነት ያስተማረን ይኼንን ነው፡፡
በአሜሪካና በምዕራቡ ዓለም ያለውን ጋዜጠኝነት ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት አልቻልንም፡፡ ለምን? እነሱ የሚንቀሳቀሱበትና እኛ ያለንበት ዓውድ የተለያየ በመሆኑ፡፡ መጀመሪያ ለራሳችን መብት ለመታገል ተገደናል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ሲመጣ ስለጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር የግድ መነጋገር አለብን፡፡ በፍላጎታችን ሳይሆን በአስፈላጊነቱ የተነሳ ጋዜጠኝነቱንና አክቲቪዝሙን ጎን ለጎን ነው ያስኬድነው፡፡ ሥርዓቱን ተቀብለህ ካልቀጠልክ በስተቀር፡፡ ሥርዓቱ በሰጠህ ዓውድ ላይ ልትንቀሳቀስ ትችል ነበር፡፡ ማንኛውም ሥርዓት ላይ ሁለት ዓይነት ጥያቄዎች አሉ፡፡ የአፈጻጸም ወይም ሥርዓታዊ ችግር ላይ ልታተኩር ትችላለህ፡፡ በፖለቲካ ጋዜጠኝነት ውስጥ ገብተህ በአፈጻጸም ችግሮችና በአስተዳደር ጉዳዮች ላይ ብቻ አተኩራለሁ ካልክ መንግሥት አይነካህም፡፡ ምክንያቱም እሱም ሥርዓቱን ብቁ የማድረግ ፍላጎት አለው፡፡ ሥርዓቱ ብቁ ሲሆን ዕድሜው ይራዘምለታል፡፡ የአስተዳደር ህፀፆችን ነቅሶ የሚያወጣለትን ጋዜጠኝነት አይጠላም፡፡ ያንን መሥራት ብፈልግ ኖሮ በሰዓቱ በጣም አትራፊ እሆን ነበር፡፡ ከሥርዓቱ ጋር ተስማምቼ እየኖርኩ ብዙ ማስታወቂያዎች ያሉት ጋዜጣ ማሳተም እችል ነበር፡፡ እንዲያውም እንደ ተመላሽ ዳያስፖራ ምሳሌ እንድሆንለት ከሌሎች ጋዜጠኞች የተሻለ ዕድል ይሰጠኝ ነበር፡፡ ምርጫዬ ግን ይኼ አልነበረም፡፡ የአገሪቱ ችግሮች አስተዳደራዊ አልነበሩም፣ የሥርዓት ችግሮች ናቸው፡፡ ሥርዓታዊ ችግሮች ላይ ስታተኩር ደግሞ ይጣላሃል፡፡ ምን አበረከትክ በጋዜጠኝነት ውስጥ? ለሚለው ኢትዮጵያ ውስጥ ንፁህ ጋዜጠኝነትን የማስተግበር ጉዳይ ከሆነ ያንን ሁኔታ የሚፈጥር ዓውድ ስላልነበረ ዕድሉን አላገኘሁም፡፡ የሥርዓቱን ህፀፅ ለማጋለጥ እንደመረጠ ጋዜጠኛ ጊዜዬን ያጠፋሁት በትግል ላይ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቢኖርና ወደ ሙያዬ ብመለስ ለጋዜጠኝነት ይኼንን አበረከትኩ ለማለት የሚያስችለኝ ሁኔታ ይኖር ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ታዲያ ጋዜጠኝነቱን ሳታሳካ እንዴት ወደ ፖለቲካው ገባህ?
አቶ እስክንድር፡- ሕወሓት በ1998 ዓ.ም. እኮ ራሴን ያወጣሁትን ሕግ አላከብርም ብሎ የጋዜጣ ፈቃድ መስጠትንም ከለከለ፡፡ በ2000 ዓ.ም. ከእስር ቤት ስንወጣ ጋዜጠኝነቱም ፖለቲካውም ወደ ነበረው ይመለሳል ብለን ነበር ያሰብነው፡፡ ከወጣን በኋላ በቃ ከእንግዲህ የጋዜጣ ፈቃድ አልሰጥም አለ፡፡ የዚህን ጊዜ ከፖለቲካው በፊት ወደ ሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት ገባሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. አጋማሽ እስር ቤት ቆየሁ፣ ለስድስት ዓመት ተኩል፡፡ ወጥቼ ኢትዮጲስን ጀምሬ እየሠራሁ እያለ ደግሞ የአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ጉዳይ መጣ፡፡ ለዚህ ምላሽ ለመስጠትም ወደ ፖለቲካ ሳይሆን ወደ ተሟጋችነት ነው የገባሁት፡፡ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት የሚባል የሲቪል ማኅበሰረብ ድርጅት ነበር፡፡ በእሱ ውስጥ ሆነን ደግሞ ቆምንለትን ዓላማ የሚያስፈጽምልን የፖለቲካ ድርጅት አጣን፡፡ የምትሟገትለትን አጀንዳ የሚያስፈጽም የፖለቲካ ድርጅት ከሌለህ ሙግትህ ትርጉም የለውም፡፡ እንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት በኢትዮጵያ መድረክ ላይ ስለጠፋ፣ ሲቪል ተቋም የነበረውን በቀጥታ ወደ ፖለቲካ ድርጀትነት ልናሸጋግረው ችለናል፡፡ ሁኔታዎች አስገድደውን መጀመሪያ ከጋዜጠኝነት ወደ ሲቪል ማኅበረሰብ፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ  ወደ ፖለቲካው መጥቻለሁ፡፡ አሁን የሙሉ ጊዜ ፖለቲከኛ ነኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ከሲቪል ማኅበረሰብ ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት ሽግግር ስታደርጉ የቆማችሁለት ዓላማ የአዲስ አበባን ሕዝብ መብት ማስከበር የሚል ነበር፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ፓርቲው በአዲስ አበባ ደረጃ የተወሰነው፡፡ ከእስር ከተፈታህ በኋላ በሰጠኸው መግለጫ ላይ ግን፣ ‹‹መጀመሪያም ዕቅዳችን አገራዊ ፓርቲ የመሆን ነበር›› የሚል ሐሳብ አንስተሃል፡፡ ይኼንን እንዴት ታስታርቀዋለህ?
አቶ እስክንድር፡- የአዲስ አበባ ጉዳይ አገራዊ ፖለቲካው የወለደው ችግር ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ብቻ ተነጥሎ የመጣ ችግር የለም፡፡ አገራዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት ባለመገንባቱ አምባገነናዊ ሥርዓት የወለዳቸው ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ውስጥ አንዱ የአዲስ አበባ ጉዳይ ነው፡፡ ወደ ሲቪል ማኅበረሰብ ስንመጣ ሥርዓቱ ከወለዳቸው ችግሮች ውስጥ አንዱን ነቅሰን በአዲስ አበባ ችግር ላይ ነበር መሠረት ያደረግነው፡፡ ዓላማችን አገራዊ በሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች በኩል የአዲስ አበባን ጉዳይ ማስፈጸም ነበር፡፡ ለዚህ ትኩረት ያደረግነው፣ ተስፋችንን ጥለን የነበረው ኢዜማ ላይ ነበር፡፡ ልዩ ጥቅም የሚባል መፈጸም የለበትም ነበር የምንለው፡፡ ይኼንን አጀንዳችንን ይዘን ለመሸጥ የሄድነው መጀመሪያ ለሕዝቡ፣ ከሕዝቡ ባሻገር ደግሞ የፖለቲካ ድርጅት ብለን ለመረጥነው ኢዜማ ነበር፡፡ ኢዜማ ግን በፈለግነው መንገድ ሊሄድልን አልቻለም፡፡ ከገዥው ፓርቲ ጋር ያለው ቅርበት ምቾት አልሰጠንም፡፡ ለእኛ ብቻ አይደለም ለሕዝቡም ምቾት አልሰጠውም፡፡ የገዥው ፓርቲ አማራጭ ከመሆን ይልቅ ከሞላ ጎደል የገዥው ፓርቲ ሌላኛው የሳንቲም ግልባጭ ሆኖ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ ነው የገባው፡፡ ስለዚህ የምንሟገትለት ጉዳይ በመጪው ምርጫ ውስጥ ባለቤት አጣ፡፡ የምናስረክበው የምንሸጥለት ድርጅት አጣን፡፡ ይኼንን ሕዝቡም ተመልክቷል፣ እኛም እንደ አመራር ዓይተነዋል፡፡ ሕዝቡ የቆማችሁለትን ዓላማ ወደ መንግሥት ፖሊሲነት የምትቀይሩት በማን በኩል ነው? ራሳችሁን ወደ ፖለቲካ ድርጅት አሳድጋችሁ የምትሉትን ነገር ማስፈጸም አለባችሁ አለ፡፡
ቅድም እንዳልኩት ችግሩ አገራዊ መሆኑ ሊፈታ የሚችለው በአዲስ አበባ ደረጃ አይደለም፡፡ በፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው ሊፈታ የሚችለው፡፡ ስለዚህ ወደ ፖለቲካ ድርጅትነት ስንሸጋገር ማቋቋም የነበረብን ድርጅት ኅብረ ብሔራዊና አገራዊ፣ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ጥምረት ፈጥሮም ቢሆን በፓርላማው ውስጥ አብዛኛውን መቀመጫ መቆጣጠር የሚችል መሆን እንዳለበት ነበር የገባን፡፡ ሆኖም  ይኼን ውሳኔ ስንወስን የካቲት 2012 ዓ.ም. ላይ ደርሰን ነበር፡፡ ግንቦት ላይ ምርጫ ሊካሄድ የአራት ወር ጊዜ ነበር የቀረው፡፡ አገራዊ የፖለቲካ ድርጅት የምናደርገው ከሆነ በአራት ወር ውስጥ አገራዊ ፓርቲ መመሥረት እንችልም፣ ብዙ ቅድመ ዝግጅት አለው፡፡ የነበረን ምርጫ ወይም በአዲስ አበባ ደረጃ ብቻ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት መሥርተን፣ በአዲስ አበባ ብቻ ተወዳድረን በቀጣዩ ምርጫ አገራዊ ፓርቲ ሆነን መቀጠል ነው፡፡ እንዲህ ነበር ዕቅድ የያዝነው፡፡ ይኼንንም ደግሞ በፕሮግራማችን ላይ በግልጽ አስቀምጠነዋል፡፡ አሁን ጉባዔ የምናደርግበት ጊዜ ላይ ነን፣ ጉባዔውን ስናደርግ መጀመሪያ ላይ ያስቀመጥነውን ራዕይ የምናስፈጽምበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ከዚህ ባሻገር ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የአዲስ አበባን አስተዋፅኦ ይፈልጋል፡፡ አሁን ካለንበት ምስቅልቅል ሁኔታ ለመውጣት የአዲስ አበባ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ ከኢሕአፓና ከቀይ ሽብር በኋላ አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወጥታለች፡፡ በኢሕአፓ ቀይ ሽብር እስኪመጣ ድረስ የበላይነት የነበረው አገራዊ ፖለቲካ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ከተቀነሰ በኋላ ግን ዳር ያለው የብሔር ፖለቲካ እየጦዘ ሄደ፡፡ የአዲስ አበባ ወደ ፖለቲካው መመለስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ግንብ ሳይሆን አማካይ ድልድይ ይሆናል የሚል ዕይታ አለን፡፡
ሪፖርተር፡- ባልደራስ ከሲቪል ማኅበረሰብነት እስከ ፖለቲካ ፓርቲነት የአዲስ አበባን ጉዳይ ለማቀንቀን ነው የተቋቋመው፡፡ እንደ ፓርቲ የአዲስ አበባ ችግር ነው ብላችሁ የምታስቡት ምንድነው?
አቶ እስክንድር፡- ሰፋ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ስንመለከት የአዲስ አበባ ሕዝብ የሚፈልገው ሌላው ኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገውን አንዲት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ነው፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራዕይና ፍላጎት አንዲት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በሚለው ይገለጻል፡፡ የመበተን አደጋ ያላንዣበባት፣ አንድነቷ አስተማማኝ ዋስትና ያላት አገር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በሌላው ዓለም ያለውን ዓለም አቀፋዊ ዴሞክራሲ (universal democracy) ነው፡፡ የሚያስፈልገው ኢትዮጵያውያን ተሰብስበን የምንፈጥረው አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት አይደለም፣ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዳር ዳር እንደሚሉት፡፡ ዓለም አቀፋዊ ዴሞክራሲ የምንለው በአሜሪካ፣ በምዕራብ አውሮፓ፣ በህንድ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በጃፓንና በሌሎች አገሮች የሚሠራ ነው፡፡ በሁሉም አገር የሚሠራ የዴሞክራሲ ሥርዓት አለ፣ እሱ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ራዕይ፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ ራዕይ የዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራዕይ አካል ነው፡፡ ይሁንና አምባገነናዊ ሥርዓቶች በየቦታው የወለዷቸው የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡ እዚህ ውስጥ የአዲስ አበባም ችግር አለ፡፡ የአዲስ አበባ ችግር የምንለው ይኼ ልዩ ጥቅም የምንለው ችግር ነው፡፡ ባለአደራው በተነሳበት ጊዜ ልዩ ጥቅም የሚል ነበር ችግራችን፡፡  ይኼም ማለት አዲስ አበባ ያለው 80 በመቶ ሕዝብ መጤ ነው፣ በሰው መሬትና በሰው አገር ላይ ነው የሚኖረው የሚል ነው፡፡ የእኔ ዘመዶች ዓባይን ተሻግረው ነው የመጡት፡፡ እኔ እዚህ ብወለድም የአቶ እስክንድር ዘመዶች ዓባይን ተሻግረው ስለመጡ አቶ እስክንድር መጤ ነው፡፡ እዚህ አዲስ አበባ ላይ የነበረውን ሕዝብ አፈናቅለው ነው የተቀመጡት፡፡ ስለዚህ አቶ እስክንድር ለባለቤቶቹ ልዩ ጥቅም መክፈል አለበት የሚል ነበር የአዲስ አበባ ችግር መነሻው፡፡ አሁን ደግሞ ኦሕዴድ ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ልዩ ጥቅም የምንለው በቂ አይደለም፣ ያንሰናል፣ በአዲስ አበባ ላይ የባለቤትነት ጥያቄ ነው ያለን የሚል ሆኗል፡፡
እኔም አሁን በአዲስ አበባ ላይ የባለቤትነት ጥያቄ ነው ያለኝ፡፡ አገሬ ነው፣ የተወለድኩበት ነው፡፡ ስለተወለድኩበት ብቻም አይደለም፡፡ ምናልባት ሙያሌም፣ መቀሌም፣ ጅግጅጋም ብወለድ የባለቤትነት ጥያቄ ይኖረኛል፡፡ በዚህ መልኩ ግን አይደለም የባለቤትነት ጥያቄ እየተነሳ ያለው፡፡ መሬቱ የኢትዮጵያ ሳይሆን የኦሮሞ ነው፣ ሌሎቻችሁ ይኼንን መቀበል አለባችሁ የሚል ነው፡፡ የአዲስ አበባ ችግር ይኼ ሆኗል፡፡ ከኦሮሞ ብሔርተኞች የሚመጣ አግላይነት፣ ዜጎችን ማበላለጥ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ባለቤትና የአዲስ አበባ መጤ የሚሉት ነገር ነው፡፡ ይኼንን አጀንዳ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጥብቀው እያራመዱ ያሉት የከተማ አስትዳደሩ ባለሥልጣናት ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ኢዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው አሁን ላይ ያለው፡፡ የአዲስ አበባ ችግር ደግሞ ከእነዚህ መካከል ብሶ መጥቷል፡፡ የእኛን በርካታ አባላት ወደ እስር ቤት ያስገባውን የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ እናንሳ፡፡ የጦርነት ቀጣና የሆነውን ትግራይን ትተን ከቀሩት ክልሎች መካከል ንፁሁን ሰንደቅ ዓላማ ይዘህ አማራ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብም ክልል ብትሄድ ማንም አይናገርህም፡፡ ይህችን ሰንደቅ ዓላማ ይዘህ ግን ኦሮሚያ ውስጥ መንቀሳቀስ አትችልም፡፡ ከኦሮሚያ ውጪ ይህች ሰንደቅ ዓለማ ችግር የምትፈጥረውና ለእስር የምትዳርገው በአዲስ አበባ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ ይኼንን ሰንደቅ ዓላማ ስለማይፈልገው ነው? አይደለም፡፡ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ጥላ የማድረግ እንቅስቃሴ ስላለ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ችግር ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሶ ያለበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባን አጥፍቶ ከኦሮሚያ ከተሞች አንዷ የማድረግ ዕቅድ አለ፣ ይኼ ነው ቀዳሚው የአዲስ አበባ ሕዝብ ችግር፡፡
ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ ከተማ ኅብረ ብሔራዊ እንደ መሆኗ ከአንድ በላይ የሥራ ቋንቋ እንደሚያስፈልግ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡም በኋላ አዲስ የቋንቋ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ አምስት ቋንቋዎችን የሥራ ቋንቋ የማድረግ ዕቅድ አለ፡፡ ከዚህ አኳያ ሕዝብን ማለማመዱ፣ ተማሪዎች አዲስ ቋንቋ እንዲለምዱ ማድረጉ ምንድነው ችግሩ? በተለይ ኦሮሚኛም ሰፊ የተናጋሪ ቁጥር ስላለው፡፡
አቶ እስክንድር፡- ችግሩ ከመርህ ውጪ መሆኑ ነው፡፡ መጀመሪያ ሕጉ አዲስ አበባ ውስጥ ከአንድ በላይ የሥራ ቋንቋ ያስፈልጋል በሚል መለወጥ አለበት፡፡ መንግሥት ከሕጉ በላይ ሆኖ ሲንቀሳቀስ ሌሎቻችን በሙሉ ሕጉን እንዳናከበር ነው የሚያደርገን፡፡ ወደ ሥርዓተ አልበኝነት ይወስደናል፡፡ ከመርህ አኳያ ችግር ባይኖረው እንኳን ሥርዓቱን ጠብቆ ነው መከናወን ያለበት፡፡ ከማንም በላይ ሕግ ማክበር ያለበት መንግሥት ነው፡፡
ሌላው ደግሞ በአገር አቀፍ አኳያ ከአንድ በላይ የሥራ ቋንቋ ያስፈልገናል የሚለው ላይ ሁላችንም ስምምነት አለን፡፡ በአዲስ አበባ ግን ከአንድ በላይ የሥራ ቋንቋ መኖር አለበት የሚለው ላይ ስምምነት የለም፡፡ አዲስ አበባ ከአንድ በላይ የሥራ ቋንቋ አያስፈልጋትም፣ አማርኛ በቂ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ደረጃ ኦሮሚኛ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ ሆኖ የሚመጣበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አልተነጋገርንም፡፡ እኔ በግልጽ ልንገርህ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪ ኦሮሚኛ ሁለተኛ ቋንቋ ሆኖ እንዲመጣበት አይፈልፈግም፡፡ ይኼ ለኦሮሞ ሕዝብ ካለው ጥላቻ አኳያ አይደለም፡፡ ይኼ አጀንዳ ያለው አካል ጉዳዩን መጀመሪያ ወደ መድረክ አምጥቶት መነጋገር አለብን፡፡ በአዲስ አበባ ደረጃ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ ያስፈልጋል የሚለው ሐሳቡ እንኳን የለም፡፡ እንደ ጋዜጠኛም፣ እንደ ፖለቲከኛም፣ እንደ ከተማዋ ነዋሪም እኔ ይኼንን ሰምቼ አላውቅም፡፡
ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ግን እንደ ነዋሪ ይኼንን ጥያቄ ያነሳሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ይኼንን በምን አረጋገጣችሁ? ጥናት አላደረጋችሁም፡፡
አቶ እስክንድር፡- ጥናት አልሠራንም፣ ግን አጀንዳው ላይ የለም፡፡ አየሩ ላይ የለም፡፡ እስኪ አዲስ አበባ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ ያስፈልጋታል ተብሎ የተነገረው የት ነው? ከየት መጣ? እኔ ይኼ ጥያቄ ያለበትን ቦታ ልይና ይቅርታ ልጠይቅ፡፡
ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ መሆኗና ተገልጋዮቿም ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ መሆናቸው፣ ከአንድ በላይ የሆነ የሥራ ቋንቋ አስፈላጊነትን አያመጣም?
አቶ እስክንድር፡- ጉዳዩን በዚህ ረገድ የምናየው ከሆነ ጥያቄው እንዲያውም የኦሮሚያ ክልል ይብሳል፡፡ ነዋሪዎች ከመላው አገሪቱ የሚሰባሰቡበት ክልል ኦሮሚያ ነው፡፡ በቅርባችን ያሉትን ናዝሬትና ደብረ ዘይት ተመልከት፡፡ በኦሮሚያ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ከተሞች ውስጥ ያለ አብዛኛው ሕዝብ ኦሮሚኛ አይችልም፡፡ ይኼ ጥያቄ የሚነሳ ከሆነ በአዲስ አበባ ብቻ አይደለም የሚነሳው፡፡ ከማንም በላይ የሚነሳው ኦሮሚያ ውስጥ ነው፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ከኦሮሚኛ ውጪ አማርኛም የሥራ ቋንቋ ይሁን ተብሎ ተነስቶ ያውቃል እንዴ? የምናነሳው ከሆነ ስለአዲስ አበባ ብቻ አይደለም የምናነሳው፣ ከማንም በላይ ስለ ኦሮሚያ እናነሳለን፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ኦሮሚኛ የሥራ ቋንቋ ይሁን ከተባለ፣ አማርኛ ደግሞ ኦሮሚያ ውስጥ በክልል ደረጃ የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት፡፡ ይኼ ጥያቄ ያለው በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አለ፡፡
ሪፖርተር፡- ባልደራስ እንደ ፓርቲ ብዙውን ጊዜ የሚነሳበት ወቀሳ አንድ ሁነት ላይ ያተኩራል የሚል ነው፡፡ ኮሽታ በተሰማባቸው አካባቢዎች ላይ ይገኛሉ እንጂ መፍታት የሚችሉት መዋቅራዊ ችግር የለም የሚል ወቀሳ ይነሳባችኋል፡፡ አንተ አሁን ደግሞ እንደተናገርከው አዲስ አበባ ውስጥ ያለው ችግር ሥርዓታዊ ነው፡፡ ይኼንን ሥርዓታዊ ችግር ለመፍታት እንደ ፓርቲ ያላችሁ ዝግጁነት ምን ያህል ነው? የምታቀርቧቸው የፖሊሲ አማራጮች የመፍትሔ አቅጣጫዎች ምንድናቸው?
አቶ እስክንድር፡- ለምንድነው እንደ ቤት መፍረስ ያሉ ሁነቶችና ትንንሽ ጉዳዮች ላይ የምታተኩሩት? ትልልቅ ጉዳዮች ላይ አታተኩሩም የሚለው ስሞታ ከሁለት አቅጣጫ ይመጣል፡፡ አንዱ ከቅንነት የሚነሳ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ሥርዓቱ ላይ ውጥረት ስለፈጠረ የሥርዓቱ ደጋፊዎች እኛን ዝም ለማስባል፣ ሥርዓቱ ላይ የሚደርሰውን ትችት ለመቀነስና እኛን እስር ቤት ወደ ነበርንበት ሁኔታ ለመመለስ የሚያነሱት ነው፡፡
በመጀመሪያ እኛ የምንከታተላቸውን ሁነቶች ምንጭ መለየት ያስፈልጋል፡፡ የአስተዳደር በደል ነው ብለን ልንወስደው እንችላለን፡፡ ቤት የሚፈርሰው መስተዳድሩ ውስጥ ያሉ አስፈጻሚዎች በሚፈጽሙት የአስተዳደር በደል ነው ብለን እንደ መነሻ ልንወስደው እንችላለን፡፡ ወይም ደግሞ ቤት የሚፈርሰው ዕቅድ ስላለ ነው፣ የኦሮሙማ ፕሮጀክት አንድ መገለጫ ነው ብለንም መነሻ ልንይዝ እንችላለን፡፡ እኛ እነዚህን ሁነቶች የምናሳድደው ከታሪክ ጋር የተጣላ፣ የአዲስ አበባን ዲሞግራፊ እቀይራለሁ የሚል፣ የተረኝነት አካሄድ ካለው ፖለቲካ የሚመነጭ ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡ ወደ እነዚህ ሁነቶች ስንሄድ ፖለቲካ ፈልገን ነው የምንሄደው፡፡ የአስተዳደር በደል ነው ብለን አይደለም የምንሄደው፡፡ ይኼ ትልቅ ነገር አለ፣ ይህችን አገር ከዳር ሳይሆን ከመሀል ሊበትን የሚችል እንቅስቃሴ አለ፡፡ ይኼ ነገር አድጎ ይህችን አገር ከማጥፋቱ በፊት እዚህ ላይ በትንሹ እልባት እንስጠው በሚል መንፈስ ነው የምንሄደው፡፡ ትንንሽ ነገር ነው የሚሉት አስተዳደራዊ በደል ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ እኛ ትንሽ ነገር ነው ብለን አናምንም፣ የትልቅ ነገር መገለጫ ነው፡፡ እነዚህን መገለጫዎች እየተከታተልን ሕዝቡን መነዝነዝ አለብን፡፡ የአገርህን ጉዳይ ተከታተል ትልቅ ችግር መጥቶብሃል እያልን ነው ሕዝቡን የምንነዘንዘው፡፡ እዚያው ሥርዓቱ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ደግሞ እዚያም ልዩነት ስላለ አካሄዳችሁ ልክ አይደለም፣ አገር ያጠፋል፣ ስለዚህ እናንተም ተነጋገሩበት የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፡፡
በነገራችን ላይ መሠረታዊ የሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር ምን መፍትሔ እንደሚያሻው ለመናገር አዲስ ፓርቲ አይፈልግም፡፡ ወይም በየጊዜው የሚወጡ ፖሊሲዎችን አይጠይቅም፡፡ እናውቀዋለን ምን እንደሚፈልግ፡፡ የአተገባበሩ ዝርዝር ላይ ነው የምንነጋገረው እንጂ፡፡ ቀዳሚው መፍትሔው አንድነት ነው፡፡ በአገራችን ላይ የመጣ የአንድነት አደጋ አለ፣ ይኼንን በጋራ መመለስ አለብን፡፡ ይኼንን በቀዳሚነት የሚፈታው የፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡ እኛ በዚህ ዙሪያ መሰብሰብ አለብን፣ ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን አድርገን፡፡ ይኼ ችግር ከማንም በላይ የተጋረጠው ደግሞ በሕወሓት ነው፡፡ መፍትሔው አዲስ ፖሊሲ አዲስ ምልከታ አያስፈልገውም፡፡ ኢትዮጵያ አትገነጠልም፣ የብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል በኢትዮጵያ አይተገበርም ብለን እንደ አገር አቋም መውሰድ አለብን፡፡ ይኼንን መተግበሪያ ሰዓት ላይ ደርሰናል፡፡ ባያፍራ ከናይጄሪያ እገነጠላለሁ ብላ ስትንቀሳቀስ የናይጄሪያ መንግሥት አይቻልም ብሎ የባይፍራን ተገንጣዮች በኃይል እንደ ደመሰሳቸው ሁሉ፣ ኢትዮጵያ ውስጥም መንግሥት ለማንም ድርጅት ግልጽ በሆነ መንገድ መገንጠል አይቻልም ብሎ የአገሩን ሉዓላዊነት ካስፈለገ በኃይል ማስከበር አለበት፡፡ ሁለተኛው መፍትሔ ደግሞ ቅድምም ተናግሬዋለሁ፣ ዓለም አቀፋዊ ዴሞክራሲ ነው የሚያስፈልገን፡፡ እሱ ደግሞ ምን እንደሚያስፈልገው ይታወቃል፡፡ እሱን ለመተግበር ትግሉ ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- የብሔር ጥያቄ የራስን በራስ የመወሰን መብት ጋ ደርሶ ብዙዎች ሲያቀነቅኑት እያየን ነው፡፡ አንድ ሕዝብ በፌዴሬሽን ሥርዓቱ መቀጠል አልፈልግም፣ አገር እመሠርታለሁ ካለ ይኼንን እንዳይፈጽም በኃይል ማስገደድ ያስፈልጋል እያልክ ካለኸው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እሴት ጋር አይጣረስም?
አቶ እስክንድር፡- ህንድን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፡፡ በዓለም ላይ የዴሞክራሲ ሞዴል ተብለው ከሚጠቀሱ አገሮች ውስጥ አንዷ ነች፡፡ በህንድ ግን መገንጠል አይቻልም፡፡ ካሽሚርን ተመልከት ሌላ ጥያቄ የላቸውም፣ ከህንድ እንገንጠል ነው፡፡ ሙስሊሞች ነን፣ የፓኪስታን አካል መሆን ነው ያለብን ነው የሚሉት፡፡ ህንድ ነፃ ከወጣችበት ማግሥት አንስቶ ላለፉት 70 እና 80 ዓመታት ለመገንጠል እየተዋጉ ነው፡፡ ከካሽሚር ውጪም ዳር ላይ ያሉ ሌሎች የህንድ አካሎችም ለመገንጠል ዳር ዳር እያሉ ነው፡፡ በህንድ ግን በግልጽ በማያሻማ ቋንቋ መገንጠል አይቻልም ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል ህንድ የዴሞክራሲ ምሳሌ ነች ተብሎ በምዕራቡም፣ በአፍሪካም፣ በእስያም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትወደሳለች፡፡ መገንጠል አትችሉም ብላ ካሽሚሮችን መዋጋቷ ኢዴሞክራሲያዊ አገር አላደረጋትም፡፡ የዴሞክራሲያዊነት መለኪያው ይኼ አይደለም፡፡ በመሠረቱ የመገንጠል መብት ዴሞክራሲያዊ መብት አይደለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ኅብረ ብሔራዊ አገሮች የቀውስና የሥርዓተ አልበኝነት ጥሪ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ዓውድ እንዲፈጠር የማያደርግ ጥሪ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካም ይኼ አይቻልም፡፡ በናይጄሪያ በባያፍራ ጦርነት ላይም መገንጠል ተሞክሯል አይቻልም፡፡ ይኼ ግን አገራቱን ዴሞክራሲያዊ አይደሉም አላስባላቸውም፡፡
ወደ አውሮፓ ብንሄድ በቅርቡ ስንከታተለው የነበረው በስፔን የካታሎናውያን ጉዳይ አለ፡፡ በካታሎን ሕዝብ የተመረጠው ክልላዊ አስተዳደር መገንጠል ትፈልጋላችሁ ወይ ብሎ ሕዝብ ውሳኔ አካሄደ፡፡ አብዛኛው የካታሎን ሕዝብ መገንጠል እንፈልጋለን ብሎ ድምፅ ሰጠ፡፡ አሁን ግን የክልሉ ሹሞች ማሰሪያ ዕዝ ወጥቶባቸው ወደ ቤልጂየም ተሰደዋል፡፡ በሌሉበት ዕድሜ ልክ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ታድያ ስፔን ኢዴሞክራሲያዊት አገር ሆናለች? ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጋረጠብን የመፍረስ አደጋ ለመውጣትና ዴሞክራሲን ለመገንባት የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ መገንጠልን በማያሻማ መልኩ መከልከል ነው፡፡ ይኼንን የምንለው አጥንተና ተወያይተን፣ ባልደራስ ይኼንን ሞዴል ይዞላችሁ መጥቷል በማለት አይደለም፡፡ የባልደራስ አመራርና አባላት ይኼንን አላደረጉም፡፡ የሌላውን ዓለም ምሳሌ ተመልክተን ነው፡፡ በተፈተነው በሚሠራው መንገድ እንሂድ እያል ነው፡፡ እኛ ነን ከሌላው ዓለም ተነጥለን አዲስ መንገድ አለን እያልን ያለነው፡፡ በዓለም ላይ የመገንጠል መብት እየተከበረ ያለበት አንድም ምሳሌ የለም፡፡ ስለማይቻል ነው ሌላው ዓለም ላይ፡፡ ስለማይቻል ነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ያቃተን፡፡ ኢትዮጵያን ወደ ጦርነት የገፋት፣ አዲስ አበባ ውስጥም መጤ ያስባለን ይኼ አስተሳሰብና አንቀጽ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የመገንጠል ጥያቄ ሲነሳ አገሮችን እየጠቀሱ እነሱ አላደረጉትም ማለት ክርክሩ ላይ ህፀፅ መሥራት አይመስልህም? ሌሎች አገሮች ይኼንን አለመተግበራቸው ብቻ ሐሳቡን ውድቅ ያደርገዋል?
አቶ እስክንድር፡- እኛ እኮ ዘግይቶ እንደ ደረሰ ሰው የምናገኘው ጥቅም አለ፡፡ ከአንተ በፊት በመንገዱ ከሄዱት መማር አለብህ፡፡ ከሌሎች አገሮች መማር አለብን፡፡ ሀ ብለን መጀመር የለብንም፡፡ የእነሱን ተሞክሮ ቀጥታ አምጥተን መቶ በመቶ አንተገብረውም፡፡ ግን ሌሎች እኛም የሚመስሉ አገሮች በምን መንገድ ሄደው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ተገበሩ የሚለውን መመልከት አለብን፡፡ ከሁሉም የምንማረው የመገንጠል መብት እንደማይቻል ነው፡፡ ይኼንንም ያሉት በስሜት ተነስተው አይደለም፡፡ ይህች አገር ልትበተን ትችላለች የሚል እርግጠኛ ያልሆነ ስሜት ባለበት አገር ውስጥ የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት አትችልም፡፡ ዴሞክራሲን መፍጠር የምትችለው አገር የነበረች፣ ያለች፣ የምትቀጥል ናት ብለህ እርግጠኝነትን ከፈጠርክ በኋላ ነው፡፡ በአንድ አካባቢ ቤት የምትገነባው በአካባቢው እንደምትኖር ዋስትና ሲኖርህ ነው፡፡ ይኼንን ደግሞ ተከራክረን ማድረግ አንችልም፡፡ እንደ አገር አብረን ለመቀጠል ፈቃደኝነት ያስፈልገናል፡፡ ይኼንን ፈቃደኝነት የምናመጣው ደግሞ ይህች አገር አትፈርስም ብለን አቋም ስንይዝ ነው፡፡ ይኼንን አቋም ሳንይዝ የጋራ ኢኮኖሚና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት አንችልም፡፡ ይኼንን ከሌሎች አገሮች መማር አለብን፡፡
እኛም ላለፉት 30 ዓመታት ሞክረነው አልሠራልንም፡፡ ሕወሓት ከሥልጣን ሲወርድ አኩርፎ ወደ መገንጠል ነው የሄደው፡፡ ኦሕዴድም ነገ ከሥልጣን ውረድ ሲባል አኩርፎ ወደ እዚያዛው ይኼዳል፡፡
ሪፖርተር፡- በተለይ ከ1960ዎቹ ጀምሮ የብሔረሰቦች ጥያቄ ሲነሳ ቆይቷል፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከወጣ በኋላ ቋንቋ ላይ መሠረት ያደረገ የፌደራሊዝም ሥርዓት መዘርጋቱ ጥያቄውን በተወሰነ ደረጃ ቢመልሰውም፣ አሁንም እስከ ጥግ ድረስ መተግበር አለበት የሚል ሐሳብ ያላቸው አሉ፡፡ በብሔረሰቦች ጥያቄ ላይ የአንተ ምልከታ ምንድነው?
አቶ እስክንድር፡- በተማሪዎች እንቅስቃሴ ጊዜ ለብሔረሰቦች ጥያቄ እንደ ማስረጃ ሲያቀርቡት የነበረው የብሔረሰቦች ቋንቋ የትምህርትና የሥራ ቋንቋ አልሆነም፣ ብሔሮችም የራሳቸው ክልል የላቸውም የሚለውን ነበር፡፡ በዚህ መሥፈርት የምንሄድ ከሆነ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የብሔር ጭቆና አሁንም አለ፡፡ ጎረቤት አገር ኬንያን ጨምሮ በአንድም የአፍሪካ አገር ውስጥ የብሔረሰቦች ቋንቋ የሥራ ቋንቋ አይደለም፡፡ ኬንያ ውስጥ ኦሮሚኛ ይነገራል፡፡ ታድያ ኬንያ ውስጥ ኦሮሚኛ የሥራ ቋንቋ ባለመሆኑ ኬንያ ውስጥ ያለው ኦሮሞ የብሔር ጭቆና ሰለባ ነው? ቅኝ እየተገዛ ነው? በምን መሥፈርት ነው ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ናት ያሉት ተማሪዎቹ? አፄዎቹ የነበራቸው የቋንቋ ፖሊሲ የሌሎች አፍሪካ አገሮች ከነበራቸው የቋንቋ ፖሊሲ የተለየ አይደለም፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ በነበረው የቋንቋ ፖሊሲ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በሙሉ በአንድ ቋንቋ መማራቸው፣ በሌሎች ኅብረ ብሔራዊ አገሮች ውስጥ ካለው ተሞክሮ የተለየ አይደለም፡፡ በዚያን ዘመን የነበረው ልማድ እንደቀጠለ ነው፣ የተቀየረው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በሌሎች አገሮች ዘንድ አለመተግበሩ ማሳመኛ ሆኖ መቅረብ ይችላል?
አቶ እስክንድር፡- የእኛን ብሔር ብሔረሰቦች ሌላው አገር ላይ ካሉት ብሔር ብሔረሰቦች ምንድነው ልዩ የሚያደርጋቸው?
ሪፖርተር፡- ሕዝቡ ጥያቄውን ካነሳውስ?
አቶ እስክንድር፡- ሕዝቡ ካነሳው መመለስ አለበት፡፡ ግን ተማሪዎች ናቸው? ወይስ ሕዝቡ ጥያቄውን ያነሳው?
ሪፖርተር፡- ተማሪዎቹ ቢያነሱትም ጥያቄው እየተወረሰ የኦሮሞ ልሂቃንም ሆኑ የብሔር ፌደራሊዝሙን የሚደግፉ ሰዎች አሁንም ያቀነቅኑታል፡፡ አማራ ክልል ድረስም ሄዶ አብንን ወልዷል፡፡ እነዚህን ስንመለከት ሕዝቡ ይኼንን ጥያቄ አላነሳውም ማለት አንችልም፡፡ ስላነሳውም ነው በቅርቡ ፓርቲዎቹ ተመርጠው ፓርላማ የገቡት፡፡ ከዚህ አኳያ ሕዝቡ ጥያቄ አላነሳም ማለት ይቻላል?
አቶ እስክንድር፡- ተማሪዎቹ ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ናት ብለው በበየኑበት ጊዜ ኢትዮጵያውን አገራችን እስር ቤት ናት፣ አማራ ቅኝ እየገዛን ነው ይሉ ነበር ወይ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ አይሉም ነበር ነው፡፡ እነዚህ የተማሪው ንቅናቄ አባላት በሕወሓት በኩል መጥተው ሥልጣን ከያዙ በኋላ እንደዚህ የሚያስብ ትውልድ ተፈጥሯል የሚለውን እቀበላለሁ፡፡ 30 ዓመት ስንል ከአንድ ትውልድም አልፏል፡፡ አዲስ እውነታ ተፈጥሯል፡፡ ወደ ኋላም መሄድ የለብንም፣ እሱንም እቀበላለሁ፡፡ ግን ታሪካችንን በትክክል መረዳት አለብን፡፡ ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች እስር ቤት ነበረች ወይ? ብሔር ብሔረሰቦች በተለየ ሁኔታ የተጨቆኑባት አገር ነች ወይ? አፄዎቹ የብሔረሰቦች ጠላት ነበሩ ወይ? ብለን የምንጠይቅ ከሆነ፣ የተማሪዎች እንቅስቃሴ አባላት እንዲህ እያሉ ሲያነሱት የነበረው ስህተት ነው፡፡ ከስህተትም አልፎ ውሸት ነው፡፡
አሁን ያለውን አዲስ እውነታ ደግሞ መቀበል አለብን፡፡ ወደ ቀድሞው እንመለስ እያልኩ አይደለም፡፡ ወደ መፍትሔ ለመሄድ ግን የተሠራብንን በትክክል ማወቅ አለብን፡፡ የአገራችንን ታሪክ በትክክል ስንረዳ ነው ወደ መፍትሔ መሄድ የምንችለው፡፡
ሪፖርተር፡- ከተማሪዎች እንቅስቃሴ በፊት የብሔረሰቦች ጥያቄ አልተነሳም የሚለው ብዙ ክርክር አለበት፡፡ እንደ ባሌ የገበሬዎች አመፆች እዚህ ምድብ ውስጥ የሚወድቁ ናቸው የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ ምሁራን አሉ፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አንድ ከክፍለ ሀገር የመጣ ተማሪ ሁሉንም ትምህርቶች A አምጥቶ፣ አማርኛ ትምህርት ካላለፈ ዩኒቨርሲቲ መግባት አይችልም ነበር፡፡ ይኼ እንደ ብሔር ጭቆና ሊቆጠር አይችልም?
አቶ እስክንድር፡- ኬንያ ብትሄድ አንድ የሥራ ቋንቋ አላቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት እንግሊዝኛ መቻል አለብህ፡፡ ኮትዲቯር ብትሄድ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ፈረንሣይኛ መቻል አለብህ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ብሔራዊ መግባቢያ ቋንቋ ተብሎ የተመረጠው አማርኛ ነበር፡፡ ኬንያ፣ ኮትዲቯርና ኢትዮጵያ ውስጥም አንድ ቋንቋ ተመርጧል፡፡ እኛ የመረጥነው የአውሮፓ ቋንቋ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ነው የመረጥነው፡፡ ያንን ቋንቋ መማር አለባችሁ ተብሏል፡፡
ለምን? አንድ ተማሪ መንግሥት ሀብቱን የሚያፈስበት ወደ ኅብረሰተቡ ገብቶ እንዲሠራ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ግን አማርኛ ተናጋሪ የሆነ ማኅበረሰብ ጋ ብቻ አይደለም ሄዶ የሚያገለግለው፡፡
አቶ እስክንድር፡- ታድያ አንድ የትግራይ ተማሪ አማርኛ ካለለፈ ወላይታ ውስጥ ሄዶ በምን ሊግባባ ነው? በእንግሊዝኛ? አንድ ትግራይ ውስጥ የነበረ ተማሪ አማርኛ ይማር ነበር፣ በነገራችን ላይ አሁንም መማር አለበት፡፡ የምናስተምረው የጋን መብራት ሆኖ ዕውቀቱን ለራሱ እንዲይዝ አይደለም፣ እንዲያገለግል ነው፡፡ የወጣበትን ማኅበረሰብ ብቻ እንዲያገለግልም አይደለም፡፡ ሁላችንንም የሚያግባባው ቋንቋ ደግሞ አማርኛ ነው፡፡ እንዴት መጣ የሚለው ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም ተማሪ አማርኛን ተምሮ አገሩን ማገልገል አለበት፡፡ ምንድነው ኃጥያቱ? በምን መሥፈርት ነው የብሔር ጭቆና የሚሆነው? ነገሮች ተጣመው ነው እየተቀመጡ ያሉት፡፡ በቅንነት እየታዩ አይደለም፡፡ አማርኛ ቋንቋን መናገር የአማራ ማንነትን መላበስ አይደለም፡፡ እኔ የተሰባበረ እንግሊዝኛ ቋንቋ እችላለሁ፡፡ እንግሊዝኛ መቻሌ ግን የእንግሊዝ ወይም የአሜሪካ ማንነት አላላበሰኝም፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነትና ሰብዕና ነው ያለኝ፡፡ ቋንቋው መግባቢያዬ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንግሊዝኛ ተምሬአለሁ፡፡ ግን የብሔር ጭቆና የሚያስብል ነገር አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ለምታነሳቸውና ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚታዩት ችግሮች እንደ ባልደራስ መፍትሔ የምትሉት ምንድነው?
አቶ እስክንድር፡- በመጀመሪያ አሁን ያለው ነገር ይቀልበስ፣ ወደ ድሮው እንመለስ ብለን አናስብም፡፡ አሁን ያለው ሁኔታም በሙሉ ጥሩ ነገር የለውም ብለንም አናስብም፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ስንል ለምሳሌ የብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋ የትምህርትና የሥራ ቋንቋ መሆኑ መነሳት ይችላል፡፡ ይኼ ይቀልበስ አንልም፡፡ ከነበረውም ካለውም አደባልቀን መሄድ አለብን፡፡ ይህም የብሔር አደረጃጀትንና የብሔር ፖለቲካን የዘመናችን እውነታ እንደሆነ ተቀብለን መሄድ አለብን፡፡ ለጥሩ ነገር ነው ማዋል ያለብን፡፡ በዚያው ልክ ኅብረ ብሔራዊ አስተሳሰብ ደግሞ ጥሩ ነገር ነው፡፡ እሱንም ይዘን መሄድ አለብን፡፡ መጨረሻና ግባችን ግን ኅብረ ብሔራዊ መሆን አለበት፡፡ የብሔር አደረጃጀት ምንም ዋጋ የለውም ማለት አይደለም፡፡ እሱም ቦታ አለው፡፡ የዘመናችን መገለጫ ስለሆነ፡፡ ዘላቂ ራዕያችን ኅብረ ብሔራዊ ቅኝት ቢያስፈልገውም፣ ዘመናችንን ግን ዋጅተን መጓዝ መቻል አለብን፡፡ ምናልባት ከሌሎች ኅብረ ብሔራዊ ድርጅቶች የሚለየን ይኼ ነው፡፡ ያለውን እውነታ እንቀበላለን፡፡ የብሔር ፖለቲካ መግነኑ ለጥሩ ሁኔታ መዋል እንደሚችል፣ ወደ ኢትዮጵያዊ ቅኝት ውስጥ ልናስገባው እንደምንችል፣ የእዚህችን አገር አንድነት ለማስቀጠል፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ግብዓት ሊሆን እንደሚችል እንገነዘባለን፡፡ አሁንም ላሰምርበት የምፈልገው ግን የመጨረሻው ቅኝት ኅብረ ብሔራዊነት መሆን አለበት፡፡  ኅብረ ብሔራዊ ድርጅት ስናቋቁም በዚህ መንገድ ነው የምንሄደው፡፡ ግብና ራዕያችንም አሁን ያለውንም ሁኔታ ባጣጣመ መንገድ ነው የሚሄደው፡፡ ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ሆና አታውቅም፣ ይኼንን በጣም ላሰምርበት እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ለብሔር ብሔረሰቦቿ የተለየ ሸክም አሸክማ፣ የተለየ ዕዳ ጭና አታውቅም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ከየትኛውም አገር የተለየ መከራ አላጋጠማቸውም፡፡ ከዚህ በተማሪዎች ንቅናቄ ጊዜ ከተፈበረከ ውሸት ነፃ መውጣት ትልቁ ብሔራዊ ተልዕኳችን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከፖለቲካው እንውጣና አቶ እስክንድር ፖለቲካና ጋዜጠኝነቱ ላይ ትኩረት ሲያደርግ ለቤተሰቦቹ በቂ ጊዜ አልሰጠም ትባላለህ፡፡ መቼ ነው ለመጨረሻ ጊዜ ቤተሰቦችህን ያየኸው? ከቤተሰቦችህ አኳያ ብዙ ጊዜ እስር ቤት ውስጥ በማሳለፍህ ትግልህን ዋጋ ያለው ነው ወይ?
አቶ እስክንድር፡- እሱ የዕለት ተዕለት ሸክሜ ነው፡፡ ግን አሁን ቤተሰቦቼን ለማየት መሄድ ያልቻልኩት የአሜሪካ ኤምባሲ እስካለፈው ሰኞ ድረስ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቪዛ የማይሰጥ ስለነበረ ነው፡፡ ከእስር ቤት እንደ ወጣሁ ያደረግኩት ወደ ግንባር ሄዶ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚዋደቁትን ወንድሞቻችንን ማመስገን ነበር፡፡ ከዚህ የማስቀድመው ጉዳይ አልነበረም፡፡ ስፈታ የእኔ የምላት አገር እንድትኖር ያደረጉልኝን ማመስገን ነበረብኝ፡፡ ከዚህ ስመለስ ወደ ቤተሰቦቼ ለመሄድ ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ነበር ያቀናሁት፡፡ በየሁለት ዓመት የሚታደስ ቪዛ ቢኖረኝም፣ ስሄድ ማደስ አትችልም ነው የተባልኩት፡፡ የቪዛ አገልግሎት ቆሟል አሉኝ፡፡ ለ15 ቀናት ጠብቅ ተብዬ ብዙ 15 ቀናት አልፈዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ሄጄ አመልክቻለሁ፡፡ ውጤቱን እየጠበቅሁ ነው፡፡ ቪዛ እንዳገኘሁ ወደ አሜሪካ ሄጄ ቤተሰቦቼን ጠይቄ እመለሳለሁ፡፡ ግን በጣም የማዝነው፣ ውስጥህ ምንድነው የሚፈልገው ብትለኝ ቤተሰቦቼ ዘንድ መሆን ነው፡፡ ይህ ነው የመጀመሪያ ፍላጎቴ፡፡ ግን ሌላ ደግሞ ትልቅ ኃላፊነት አለብኝ፡፡ ያንን ፍላጎቴን መተግበር ስለማልችል ቶሎ እመለሳለሁ፡፡ የምፈልገውን ያህል ጊዜ ከእነሱ ጋር ሳላሳልፍ፡፡ ትልቁ መፍትሔና ለእኔ ጥሩ የሚሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ባሰ ችግር የሚከት አደጋ ባይኖር ኖሮ ቤተሰቦቼን ወደ አገር ቤት መመለስ ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ከእስር ቤት ከወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ይህንን የሚያስችል ዓውድ የለም ኢትዮጵያ ውስጥ፡፡ እግዚአብሔር ፈቃዱ ይሁንና አሜሪካ ኤምባሲ ቪዛ የሚሰጠኝ ከሆነ ቤተሰቦቼን ማየት ነው የምፈልገው፡፡
Filed in: Amharic