>

"... ህግ ባለበት አገር ሰውን አፍኖ ወስዶ ፊትን ሸፍኖ ባዶ ክፍል ውስጥ ለሳምንት ማስቀመጥ አሳፋሪ ተግባር ነው...!!!!" (ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ) 

“… ህግ ባለበት አገር ሰውን አፍኖ ወስዶ ፊትን ሸፍኖ ባዶ ክፍል ውስጥ ለሳምንት ማስቀመጥ አሳፋሪ ተግባር ነው…!!!!”

ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ

*… ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ የት እንደቆየ እንደማያውቅ ና ሲመልሱትም  ‹‹ፊትህን ሳታዞር ቀጥ ብለህ ሂድ…!!!››እንዳሉት ይናገራል

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሣ እየበላ ከነበረበት በተለምዶ ፈረንሣይ ከሚባለው ሠፈር፣ ጊዮርጊስ ከተባለ ምግብ ቤት ለጥያቄ ትፈለጋለህ ብለው አፍነው የወሰዱት የፀጥታ ሰዎች በማይታወቅ ቦታ ለሳምንት አቆይተው እንደለቀቁት ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ ለሪፖርተር ተናገረ፡፡ ሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት ወደ አራት ሰዓት በተለምዶ ገላን እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ የፀጥታ ኃይሎቹ እንደለቀቁት የገለጸው ገጣሚው፣ በቆይታው ወቅት የተለየ ማሰቃየትም ሆነ እንግልት እንዳልተፈጸመበት አስረድቷል፡፡

ስለታሰረበት ሁኔታ ለሪፖርተር ያስረዳው ገጣሚ በላይ፣ ባለሥልጣናት በሚሄዱበት ቪ8 እየተባለ በሚጠራ መኪና በመጡ ሰዎች ምሣ ከሚበላበት ቦታ ለጥያቄ ትፈለጋለህ ተብሎ መወሰዱን ገልጿል፡፡ መኪና ውስጥም ሆነ በወሰዱኝ እስር ቤት የፊት መከለያ ጭንብል አጥልቀው እንዳቆዩት ያስረዳው በላይ፣ ለመፀዳዳት ካልሆነ በስተቀር መውጣት ሳይፈቀድለት በጨለማ ክፍል ውስጥ መቆየቱን ተናግሯል፡፡ ‹‹ከቤተሰብም ሆነ ከማንም ጋር በስልክም እንድገናኝ አልፈቀዱልኝም፡፡ ሲወስዱኝ ያዩ ሰዎች በመጠቆማቸው ይመስለኛል መታሰሬም የታወቀው፤›› ሲል አስረድቷል፡፡

ስለተጠረጠረበት ወንጀል ወይም ለእስራት ስላበቃው ምክንያት የፀጥታ ሰዎቹ ነግረውት እንደሆነ የተጠየቀው ገጣሚ በላይ፣ ስለምርመራው ብዙም ማውራት እንደማይችል ተናግሯል፡፡ ‹‹የራሳቸውን ጥያቄ ጠይቀውኛል፡፡ እኔም መልስ ነው የምለውን መልሼላቸዋለሁ፤›› ሲል የተናገረው ገጣሚው፣ በስተመጨረሻ በማያውቀው ሁኔታ ሰኞ ምሽት አራት ሰዓት አካባቢ ፊቱን ጭንብል በማልበስ በመኪና ወስደው ገላን በሚባል አካባቢ በማውረድ፣ ‹‹ፊትህን ሳታዞር ቀጥ ብለህ ሂድ›› ከሚል ትዕዛዝ ጋር እንደለቀቁት አስረድቷል፡፡

‹‹ሕግና መንግሥት ባለበት አገር ሰውን አፍኖ ፊትን ሸፍኖ ባዶ ክፍል ውስጥ ለሳምንት ማስቀመጥ አሳፋሪ ተግባር ነው!!!፤›› ሲል የተናገረው በላይ፣ ከእስር ከተፈታ በኋላ ቢረጋጉም ቤተሰቦቹና ወዳጅ ዘመዶቹ በከባድ ጭንቀትና ሐዘን ውስጥ መቆየታቸውንም አመልክቷል፡፡

ገጣሚ በላይ በተለይ መንግሥትን በሚሸነቁጡና ወቅታዊ አጀንዳዎች ላይ ጠንካራ ትችት በሚያቀርቡ የግጥም መድብሎቹ ይታወቃል፡፡ በማኅበራዊ አንቂነቱና በህልውና ዘመቻው ወቅት በግንባር ለሚፋለሙ የኢትዮጵያ ኃይሎች ዕርዳታ በማስተባበር የሚታወቀው ገጣሚው፣ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ተቺ ግጥሞችን ሲጽፍ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡

ምንጭ: ሪፖርተር

Filed in: Amharic