>

በንጹሀን ሰዎች ላይ የሚፈጸም ግድያና አፈና ይቁም!  ( ኢሰመጉ)

በንጹሀን ሰዎች ላይ የሚፈጸም ግድያና አፈና ይቁም! 

ኢሰመጉ


የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ  በተደጋጋሚ ጊዜ ባወጣቸው መግለጫዎች በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በሸኔ ታጣቂ ቡድን እና ሌሎች በሀገሪቱ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች በተደጋጋሚ የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆኑን በመግለጽ መንግስት ይህን ድርጊት እንዲያስቆም እና በተጠናከረ መልኩ የሰዎቸን ሰላም እንዲያረጋግጥ እንዲሁም ታጣቂ ቡድኖቹ ከመሰል ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሲወተውት የቆየ ቢሆንም አሁንም ድረስ ይህ ድርጊት እየቀጠለ ይገኛል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በገብረጉራቻ ከተማ በምድረገነት ቅድስት ልደታ ቤተ ክርስቲያን ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም ሌሊት የማህሌት ጽጌ አገልግሎት ላይ በነበሩ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ላይ በሸኔ ታጣቂ ቡድን በደረሰ ጥቃት አንድ በአገልግሎት ላይ የነበረ ዲያቆን መሞቱን፣ አገልግሎት ላይ የነበሩ 11 የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋዮች በሸኔ ታጣቂ ቡድን ታግተው መወሰዳቸውን እና ይህ ሪፖርት ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ የታገቱት አገልጋዮች የት እንዳሉ እንደማይታወቅ እና አካባቢው ላይ የሚገኙ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ብዙዎቹ በአካባቢው ያለው የደህንነት ሁኔታ አስጊ በመሆኑ መዘጋታቸውን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የህዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ መኪናዎችን በማስቆም ሾፌሮች፣ ረዳቶች እና ተሳፋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ በሸኔ ታጣቂ ቡድን ጥቃት እንደሚፈጸም እና በዚህም ጥቃት ምክንያት በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን እያጡ፣ የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው እና አንዳንዶችም እየታገቱ እንደሆነና ይህም ችግር ዘላቂ መፍትሄ ስላልተበጀለት እየተባባሰ በመሄዱ በአካባቢው ለሚንቀሳቀሱ መንገደኞች ከፍተኛ ስጋት እንደሆነ ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ቢንጎአ በተባለ ስፍራ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም መንገደኞችን ይዞ ሲጓዝ የነበረ መኪና ውስጥ የነበሩ ሾፌሩን ጨምሮ 16 ሰዎች በሸኔ ታጣቂ ቡድን የታገቱ መሆኑን እና ከታገቱት ሰዎች ውስጥ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተፈትነው ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ የነበሩ ተማሪዎች እንደሚገኙበት ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡

ተያያዥ የህግ ድንጋጌዎች፡ 

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) አንቀጽ 3፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል-ኪዳንም (ICCPR) በአንቀጽ 6(1)  እና 9(1) ላይ እያንዳንዱ ሰው በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነቱ የመጠበቅ መብት እንዳለው ያረጋግጣል። ይህንኑ መብት በማረጋገጥ፣ መንግሥታት ቃል-ኪዳኑ (ICPR) የተረጋገጡትን መብቶች በግዛታቸው የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ግዴታ እንዳለባቸውም በአንቀጽ 2(1) እና 2(2)  ይደነግጋል። የአፍሪካ ቻርተር በሰዎች እና ህዝቦች መብቶች (ACHPR) አንቀጽ 4 ማንኛውም ግለሰብ በሕይወት የመኖር መብቱና የአካሉ ደህንነት መብቱ ሊከበርለትና ሊጠበቅለት እንደሚገባና እነዚህን መብቶቹን በዘፈቀደ ሊነፈግ እንደማይችል ተመላክቷል። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 14  “ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት አለው” ሲል ይደነግጋል። በተመሳሳይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 15 ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ ከተደነገገው ውጪ ሕይወቱን ሊያጣ እንደማይችል በግልፅ ደንግጓል፡፡ በተመሳሳይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት በአንቀጽ 16 ላይ ማነም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው ሲል ያስቀምጣል፡፡

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) አንቀጽ 13፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል-ኪዳንም (ICCPR) አንቀጽ 12 ላይ በአንድ አገር ግዛት ውስጥ በሕጋዊ መንገድ ያለ ማንኛውም ሰው በዚያ አገር ውስጥ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት እንዳለው ይደነግጋሉ፡፡ የአፍሪካ ቻርተር በሰዎች እና ህዝቦች መብቶች (ACHPR) አንቀጽ 6 ላይ ማንኛውም ሰው ነጻነቱና አካላዊ ደህንነቱ ተጠብቆለት የመኖር መብት አለው ሲል ይደነግጋል፡

2 ፡ በተመሳሳይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት በአንቀጽ 17 እና 32 ላይ ማንኛውም ሰው የአካል ነጻነት መብት እንዳለው እና በነጻነት በፈለገው አካባቢ የመዘዋወር መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ አባል ሀገር ባትሆንም ሰዎችን አስገድዶ ከመሰወር ለመጠበቅ የወጣው ዓለም አቀፍ ስምምነት(International Convention

for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance) በአንቀጽ 1(1) ላይ ማንም ሰው ለአስገድዶ መሰወር ተጋላጭ መሆን

እንደሌለበት በመደንገግ ይህንን ወንጀል የፈጸሙ አካላትን መንግስት በወንጀል ተጠያቂ እንዲያደርጋቸው ይደነግጋል፡፡

የኢሰመጉ ጥሪ፡

 የፌደራል መንግስት እንዲሁም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በሸኔ ታጣቂ ቡድን በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለማስቆም እየወሰዱ ያለውን እርምጃ አጠናክረው በመቀጠል የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች እንዲያስከብሩ፣

 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በገብረጉራቻ ከተማ በምድረገነት ቅድስት ልደታ ቤተ ክርስቲያን ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም የታገቱትን 11  የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ከታጣቂ ቡድኑ ነጻ እንዲያወጣ፣ ይህንን የእገታና የግድያ ተግባር የፈጸሙትን አካላት መንግስት በወንጀል እንዲጠይቅ እና የአካባቢውን ደህንነት እና ሰላም በማረጋገጥ በአካባቢው ያሉ እና የተዘጉ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት እንዲከፈቱ እንዲያደርግ፣

 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሸኔ ታጣቂ ቡድን መኪናዎችን በማስቆም የሚፈጸሙ ግድያዎችን፣ የአካል ጉዳቶችን፣ ዘረፋዎቸን እና እገታዎችን በማስቆም ሰዎች በነጻነት ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸውን እንዲያስከብር፣

 በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ቢንጎአ በተባለ ስፍራ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም መንገደኞችን ይዞ ሲጓዝ በነበረ መኪና ውስጥ የነበሩ እና በሸኔ ታጣቂ ቡድን የታገቱ 16 ሰዎችን ከታጣቂ ቡድኑ ነጻ እንዲያወጣ እና የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች የማስከበር ሀላፊነቱን እንዲወጣ፣

 በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በተደጋጋሚ በሸኔ ታጣቂ ቡድን በሚፈጸሙ ጥቃቶች ውስጥ እጃቸው ያለበትን አካላት መንግስት በህግ አግባብ ተጠያቂ በማድረግ ወንጀልን ፈጽሞ ተጠያቂ ያለመሆንን ባህል እንዲያስቀር ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

              አዲስ አበባ ፤ኢትዮጵያ

Filed in: Amharic