>
5:14 pm - Tuesday April 30, 5393

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ (ስለሰላም ስምምነቱ) ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ:_ 

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠው መግለጫ:_

እናት ፓርቲ ሕዝብ ስለሰላም ስምምነቱ

በዝርዝር እና በግልጽነት እንዲያውቅ

አለመደረጉ አሳስቦናል…!

እናት ፓርቲ የሰላም ስምምነቱ በጎ ጅምር ሆኖ ሳለ ሕዝብ ስለሂደቱ በዝርዝር እና በግልጽነት እንዲያውቅ

አለመደረጉ ግን እንደሚያሳስበው ገልጧል።

ላለፉት ኹለት ዓመታት ሀገራችን ኢትዮጵያን በእጅጉ ያደቀቀው ጦርነት በደቡብ አፍሪካ፣ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መጠናቀቁ ለአንዲት ቀን እንኳን የሰላም አየር ለናፈቃቸው በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ላሉት ወገኖቻችን የሚሰጠው ትርጉም ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ ኹሉም የሚገነዘበው ሀቅ ነው።

በዚህ ጦርነት ምክንያት ኢትዮጵያ ሀገራችን ከኹሉም በላይ መተኪያ የሌላቸውን በርካታ ውድ ልጆቿን አጥታለች፤ መሠረተ ልማት ወድሟል፤ ኢኮኖሚው ደቋል፤ የድፕሎማሲ ኪሳራ ገጥሞናል፣ የብዙዎች ማኅበራዊ ሕይወት ተናግቷል።

ፓርቲያችን አኹን ለደረስንበት ኹለንተናዊ ውድመት ከመዳረጋችን በፊት ልዩነቶች በውይይትና እርቅ እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ጥሪውን ከማድረጉ ባለፈ ጦርነቱ በእርቅ እንዲፈታ የሽምግልና ሂደት እስከጀመር የደረሰ ጥረት አድርጓል፡፡

ከረፈደም ቢሆን ጦርነቱን በድርድር ለመፍታት የተደረገው ጥረት በተለይ ሀገር ካለችበት ዘርፈ ብዙ ምስቅልቅል አንጻር የሚደነቅ ቢሆንም በተለይ በእንዲህ ያሉ ውስብስብ ጉዳዮች ሂደት ውጤትን ይወስናልና በድርድሩ የጦርነቱ ቀጥተኛ ሰለባ የሆኑት የአማራ እና የአፋር ማኅበረሰቦች አለመወከላቸው እንዲሁም የትግራይ ማኅበረሰብም በሕወሓት ብቻ ተወክሎ ድርድሩ መካሄዱ እንዲመጣ የተፈለገውን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ አዳጋች ያደርገዋል የሚል ከፍተኛ ሥጋት አለን።

በተደጋጋሚ እንደገለጽነው “የድርድሩ ጉዳይ ከኹለቱ ፓርቲዎች(ሕወሓት እና ብልጽግና) ዘለል ያለ ነው፤ ከፓርቲ ባሻገር ያሉ ገለልተኛ አካላት(ኢትዮጵያውን) ይካተቱበት፤ የድርድር ሂደቱና ውጤቱ ወደትግበራ ከመግባቱ በፊት በፓርላማው ይለፍ” ብለን የወተወትን ቢሆንም የድርድሩ ሂደት በኹለቱ ፓርቲዎች መካከል ብቻ ሆኖ ተጠናቋል።

ስለሆነም:_

፩. በድርድሩ ያልተወከሉና በጦርነቱ ቀጥተኛ ተጎጂ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች “ኢትዮጵያ አሸንፋለች” ብሎ ደጋግሞ በመናገር ለማሳመን ከመጣር ይልቅ የሚያመጣላቸውን በረከት፣ የሚያስባቸውን መዘዝ በተለይ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነውን ማኅበረሰብ በግልጽና በዝርዝር ቀረቦ ማናገር ያስፈልጋል ብለን እናምናለን፤ እንደአስፈላጊነቱም ተጨማሪ አማራጭ መፍትሔዎች የትግበራው አካል እንዲሆኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

፪. የድርድሩ ስምምነት ወደትግበራ ከመግባቱ በፊት በፓርላማው ለውይይት እንዲቀርብና እንዲያጸድቀው በአጽንዖት እንጠይቃለን።

፫. መላው ኢትዮጵያውያን ለሰላሙ መሳካት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን እያስተላለፍን በዚሁ አጋጣሚ ጦርነቱ በውይይት እንዲፈታ “ አዎንታዊ ሚና እየተጫዎቱ ላሉ አካላት ምሥጋና ማቅረብ እንወዳለን።

በመጨረሻም ፓርቲያችን በጦርነቱ እጅጉን የተጎዳውን ወገናችንን በማገዝ በኩል እንደዅልጊዜው የድርሻውን ለመወጣት እንቅስቃሴ መጀመሩን ለመግለጥ እንወዳለን፡፡

Filed in: Amharic