>

የሰላም ስምምነቱን በተመለከተ፤ ለሚነሱ ጥያቄዎች በእኔ እይታ...! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የሰላም ስምምነቱን በተመለከተ፤ ለሚነሱ ጥያቄዎች በእኔ እይታ…!

ያሬድ ሀይለማርያም


ከብዙ ሰዎች ጋር ባደረኩት ውይይት እና በውስጥ መስመርም ከብዙ ሰዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበውልኛል።

– ለምን የሰላም ስምምነቱን ደገፍክ?

– ለምን ስምምነቱ የተወሰኑ ጉዳዬችን እና አካላትን ያገለለ ወይም ያላሳተፈ ሆነ?

– የኤርትራ ጉዳይ ለምን በሰነዱ ላይ በግልጽ አልተቀመጠም?

– መንግስት እንዴት ሽብርተኛ ብሎ ከፈረጀው አካል ጋር ይደራደራል?

– ማነው በዚህ ስምምነት የተሻለ ተጠቃሚ የሆነው?

– ህውሃት ቃሉን ጠብቆ ትጥቅ ይፈታል ወይ?

– ስምምነቱ የሚጸና እና ሁለቱም ወገኖች የሚያከብሩት ይመስልሀል?

– ለዚህ ሁሉ ሰቆቃና ወንጀል ተጠያቂ ሳይኖር ነገሮች በስምምነት ስም ተደባብሰው በወንጀል መጠየቅ የሚገባቸው ሊያመልጡ ነው ወይ?

– የስምምነት ሰነዱ ለምነን የተፈጸሙ ወንጀሎች በገለልተኛ ወገን ስለሚጣሩበት ሁኔታ አላካተተም?

የሚሉ እና መሰል ጥያቄዎች ቀርበውልኛል። እነዚህን ጥያቄዎች ለጊዜው ለውይይት ክፍት ላርግና እኔ ስምምነቱን የደገፍኩበትን ዋና ምክንያት ልግለጽ።

1ኛ/ የመጀመሪያው እና ዋናው ምክንያቴ ስምምነቱ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነትን በማስቀደሙ ነው። የሕዝብ እልቂት፣ የአገር ሀብት ውድመት እና የሰሜኑ ሕዝብ ሰቆቃ መቆም ስላለበት ነው። ለአንድ ቀንም በሰላም ማደር ዋጋው በምን ይተመናል?

2ኛ/ በሁለተኛ ደረጃ ስምምነቱ የተቋረጡ ሰብአዊ እርዳታዎች እንዲቀጥሉ እና ለሁለት አመት የተቋረጡ መሠረታዊ አቅርቦቶች በአፋጣኝ እንዲመለሱ መደረጉ ነው።

3ኛ/ በሦሰተኛ ደረጃ እኩል ክብደት የሚሰጠው ነገር የህውሃት ትጥቅ ለመፍታት መስማማቱ ነው። እዚህ ላይ ሳልሸሽግ ልገልጽ የምፈልገው ነገር የኦነግ ስህተት ሊደገም የሚችልበት እድል መኖሩ ነው። የኦነግ ጦር ሽኔ የምትል ሁለት ቃል ጨምሮ እራሴን ከፖለቲካ አመራሩ የነጠለ በሚመስል መልኩ ተደራጅቶ አገር እያመሰ ነው። TDF-ሽኔ ሊፈጠር የሚችልበት አደጋ ከወዲሁ ስለታየኝ ነው።

ሌሎቹ ዝርዝር ጉዳዬች እንዳሉ ሆነው ለእኔ በዚህ ስምምነት እነዚህን፤ በተለይም የመጀመሪያዎቹ ሁለቱን ካሳካን አትርፈናል ባይ ነኝ።

እነዚህ ዘላቂ ሊሆኑ የሚችሉት ግን በቀጣይ የሚደረጉ ስምምነቶች ላይ መሠረት ያደርጋል። የአወዛጋቢ ቦታዎች የባለቤትነት ጥያቄ፣ የህውሃት ቀጣይ እጣ ፈንታ፣ የደረሱትን ጉዳቶች በገለልተኛ ወገን ማጣራት፣ የወንጀል ተጠያቂዎች ጉዳይ፣ የትግራይ እጣ ፈንታ፣ የኤርትራን ጦር ከኢትዬጵያ ግዛት ሙሉ በሙሉ ማስወጣት ብቻ ሳይሆን ጦሩ ትግራይ ውስጥ ለፈጸመው ሰቆቃ ተጠያቂ ማድረግ፣ የጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሰዎች በአፋጣኝ የመልሶ ማቋቋሚያ እና የጉዳት ካሳ መስጠት እና የወደሙ ተቋማትን መልሶ ማዋቀር ጊዜ የማዬሰጣቸው ቀጣይ ስራዎች መሆን አለባቸው። እነዚህን ነገሮች የያዘ ሌላ ዝርዝር እና ሰፊ የስምምነት ሰነድ በቅርቦ ይፈረማል ብዬ እጠብቃለሁ።

ከላይ በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ግን እንወያይባቸው። እኔም የራሴን ምልከታ አካፍላለሁ።

ቸር እንሰንብት!

Filed in: Amharic