>

ዐቅልን የመሳት አዝማሚያ አሁንም ይታያል (ከይኄይስ እውነቱ)

ዐቅልን የመሳት አዝማሚያ አሁንም ይታያል

ከይኄይስ እውነቱ


እንደ ኢኦተቤክ ሥርዓት አሁን ያለንበት ጊዜ የሱባኤ ቢሆንም በምጥ የምትገኝ የአገራችንን እና እልቂት የታወጀበትን የወገናችንን ጉዳይ በጸሎት ከማሰባችን ጎን ለጎን ዐቅማችንና ችሎታችን የፈቀደልንን ኹሉ ፍጹም ልባችንን÷ አእምሮአችንና ነፍሳችንን የዐምሐራው ሕዝባችን ፍትሐዊ ተጋድሎ ላይ አድርገን እንገኛለን፡፡ ርጉም ዐቢይና ያበቃለት አገዛዙ በሕዝባችን ላይ ከወራት በፊት የጀመረውን ጦርነት መቋቋም ሲያቅተው ዘላለማዊ አሽከር የሆነውን የብአዴን ርዝራዥ ተጠቅሞ ሕግና ሥርዓት ያለበት አገዛዝ ይመስል በተለመደው የወራዶች መሰባሰቢያ በሆነው ‹‹የአይሁድ ሸንጎ ምክር ቤቱ›› የዘር ማጽዳት ወንጀሉን ‹ሕጋዊ› ሽፋን ለመስጠት በመሞከር ፍጹም ነውረኛነቱን አሳይቷል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ርጉም ዐቢይ በሞት አልጋ ላይ ሆኖ እያጣጣረ ባለበት ሰዓት ከእንግዲህ ወዲህ በመጨረሻ የሚጨብጠው ሣር ወይም እስትፋንሱን የሚቀጥልለት ደጋፊ ‹አየር› ያለ እየመሰለው አንዴ ሳይወለድ በጨነገፈውና ‹የምክክር ኮሚሽን› በሚባለው፣ አንዴም ታሪካዊ ጠላቶቻችንን በመማፀን፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የለመደውን የሽንገላ/አጋንንታዊ ‹መንበርከክ› በመፈጸም የተጠበሰችውን የሥልጣን ክር ለመቀጠል እየተወተረተረ ይገኛል፡፡ 

በሌላ በኩል ደግሞ የዐምሐራው ሕዝብ በታሪካችን ለደረሰበት መከራ ቀዳሚ ተጠያቂ የሆነው ብአዴን የተባለ የነውረኞች ስብስብ – የአገልግሎት ዘመናቸው ባበቃ – የቀድሞ አመራሮቹ  አማካይነት በሚያደርጋቸው ንግግሮች ተማርከው ከአንዳንድ ሚዲያዎች እስከ ተራ ተከታዮቻቸው እና ‹ተንታኝ› ተብዬዎች ጭምር ዐቅላቸውን ሲስቱ ተመልከቼአለሁ፡፡ ኧረ ተዉ ሰብሰብ እንበል!!! ትግሉን በድል አጠናቅቆ ይህን ቆሻሻ አገዛዝ ለማስወገድ ለቀጣዩ ደግሞ ጥበብ÷ ማስተዋልና ብልሃት ይጠይቃል፡፡ ርጉም ዐቢይና ግብረ አበሮቹ መካንነታቸው ለበጎ ሥራ እንጂ ለአጋንንታዊ ተግባራቸው አለመሆኑን በማስተዋል እስከ መጨረሻዋ ቅፅበት ማዘናጊያና ማደናገሪያ የሚሆኑ የዕንቅፋት ደንጋዮችን እንደሚያኖሩ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ የብአዴኖች (የቀድሞቹ እነ አንዳርጋቸውም ሆኑ የሱ ወራሾች) የዚሁ ማዘናጊያ አካል መሆናቸውን ለአፍታ መዘንጋት የለብንም፡፡ 

የጥናትና የምርምር ውጤት ግኝቶች ስለመኖሩ ርግጠኛ ባልሆንም ቊጥሩ ቀላል የማይባል የሕዝባችን ክፍል ድልንም ሆነ ሽንፈትን የመሸከም ዐቅም እንደሌለው፤ ፈንጠዝያውና ኀዘኑ ልክ እንደሌለው በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ለመታዘብ ችዬአለሁ፡፡ ንጹሐን ወገኖቻችን በአየርና በከባድ መሣሪያ ጥቃት ሰለባ እየሆኑ ባሉበት በዚህ ወቅት፤ ለህልውናና ከባርነት ለመላቀቅ ክቡር የሰው ልጅ ሕይወት መሥዋዕትነት እየተከፈለ ባለበት በዚህ ወሳኝ ሰዓት ርጉም ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጣበት ጊዜ የታየውን ዓይነት የጅምላ ዕብደትና ዐቅል መሳት አዝማሚያዎችን እያየሁ ነው፡፡ መቼ ይሆን (ያውም ከቅርቡ) ከትናንት የምንማረው? 

ለመሆኑ ባገራችን የእውነተኛ ምሁር መለኪያው ምንድን ነው? በምዕራባውያን አድባረ ዕውቀት (ዩኒቨርስቲዎች) በሚታተሙ ‹የታወቁ› መጽሔቶች ላይ ‹የጥናትና ምርምር› ሥራዎቻቸው መታተሙ ነው ወይስ እነዚህ የታተሙት ሥራዎች የአገርና የኅብረተሰብን ችግር በመፍታት ረገድ በተግባር የታየ ተጨባጭ ውጤት ነው? በቅርቡ አንዱ እኔ ምሁር ነኝ የተለያዩ ጽሑፎችን አሳትሜአለሁ፡፡ እያለ በምናከብረውና አንጋፋና እውነተኛ ባለሙያ ጋዜጠኛ ፊት ሲናገር አድምጬአለሁ፡፡ የሰውየው መርበትበትና የንግግሩ ቃና በራስ መተማመን እንደሌለው ብቻ ሳይሆን ‹ምሁር› ነኝ ብሎ ከእውነቱ ሲጣላ፣ ጋዜጠኛውና ሌላው ተወያይ የሠነዘሩአቸውን ሐሳቦች ኹሉ እስማማባቸዋለሁ እያለ በተቃርኖ ሲዋዥቅና ከዚያም አልፎ በላብ ሲጠመቅ ለተመለከተው ‹በዚህ በመሸ ሰዓት› ምን ለማግኘት ፈልጎ ነው ለርጉም ዐቢይ መሸጦ በመሆን ክብርና ኩራቱን የሸጠው ያሰኛል፡፡ ላገርና ለወገን መሰናክል የሆኑ እንደነዚህ ዓይነት ሰው ርእሰ መጻሕፍቱ ወዮ ለአሰናካይ! የወፍጮ ደንጊያ ባንገቱ አጥልቆ ወደ ጥልቁ ባሕር ቢጣል በተሻለው ነበር ይላል፡፡

እንደዛሬ ግራና ቀኙን ለይቶ የማያውቀውና ኃላፊነት የማይሰማው ሁላ የማኅበራዊ ሚዲያው መድረክ ተመቻችቶልኛል በማለት ጋዜጠኝነትን እንደ አህያ ዦሮ እንደፈለገው ከመጎተቱ በፊት በእኔ ዕድሜ እና (በዕድሜ በእጅጉ ቀዳሚዎቼ ቢሆኑም) በኔ ዘመን እንደነ ጋሼ ጳውሎስ ኞኞ፣ ጋሼ ታደሰ ሙሉነህ፣ ጋሼ ንጉሤ አክሊሉ፣ ጋሼ ዐዲሱ አበበ፣ ጋሼ ሙሉጌታ ሉሌ ያሉ አንጋፋና በሳል ጋዜጠኞችን አይቼአለሁ፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ፣ ጥቂት ካነበብሁትና ካንጋፎች የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ የመደበኛ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች እንደሰማሁት በብዙው የዓለም ሕዝብ ተጽእኖ የሚያሳርፉና በወቅቱ የሠለጠነውን አስተሳሰብ የሚያንፀባርቁና ቅርፅ የሚያስይዙ መገናኛ ብዙኃኖች ዋና ዓላማ ‹ብሉያዊ› ከሆነው ሚዛናዊነት ይልቅ ‹ሐዲሳዊ› የሆነውን እውነት አንጥሮ ማውጣት ይመስለኛል፡፡ በዚህ ረገድ ጋሽ አዲስ በቅርቡ ዐምሐራውንም ሆነ ኢትዮጵያን ሊታደግ ከሚችለው መራራ ትግል ሊያናጥበን ባጉል ጊዜ ሳይጠሩት ብቅ ያለውን የርጉም ዐቢይ ‹የምክክር ኮሚሽን› ኃላፊ እና ከማከብረው ከአቶ ገለታው ዘለቀ ጋር ያደረግኸውን ቃለ ምልልስ በሚመለከት ከሚዛናዊነት ይልቅ እውነት ላይ ማተኮርህ ተገቢና የሚያስመሰግንህ እንጂ በትህትና ይቅርታ የምትጠይቅበት ጉዳይ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡

ብዙዎች በክርስትናም ውስጥ ሆነው የሚዘነጉት ታላቅ ቁም ነገር አለ፡፡ ከእግዚአብሔር አምላክ መገለጫ ባሕርይዎቹ መካከል ይቅር ባይነት እንዳለ ኹሉ በእውነት የሚፈርድ፤ በቀጥተኛ ፍርዱም የሚሠራ የሚቀጣ ነው፡፡ መጻሕፍት እንደሚያስቀምጡት ‹ፈታሔ በጽድቅ፤ ኰናኔ በርትዕ› ነው፡፡ ታዲያ ለአራት ዐሥርታት የሚጠጋ ጊዜ እንደ አባይ ሲፈስ የኖረውን የንጹሐን ኢትዮጵያውያን በተለይም የዐምሐሮችን ደም ከንቱ በማድረግ ተጠያቂ የሆኑትን ወያኔ፣ ብአዴንና የአሁኖቹን ኦነግ/ኦሕዴዶች ከፍርድ ተጠያቂነት ነፃ የሚያደርግ የስንፍና ንግግር በሚዲያዎች ጭምር መስማት በእጅጉ ያማል፡፡ ይህ የእውነተኛና ቀጥተኛ ፈራጅ የአምላክ ዕቅድ በመሆኑ ማንኛውም ምድራዊ ኃይል ሊያስቀረው አይችልም፡፡ ያለ አንዳች ጥፋታቸው በተሠዉት ወገኖቻችን ተገብቶም እንዲህ ዓይነቱን ነውር ለመዘባረቅ ማንም መብት የለውም፡፡ በርእሴ እንዳነሣሁት ይህም ዐቅልን የመሳት አንድ ማሳያ ነው፡፡

ዐምሐራው ህልውናውን ለማስከበር ብሎም የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ የሚያደርገው የሞት ሽረት ትግል የሚደመደመው በተጀመረበት ሕዝባዊ የትግል መስመር ሆኖ፣ በከይሲው ወያኔ መሠረት የተጣለውንና የእፉኝቱ ልጅ በሆነው የቀጠለውን ፋሺስታዊ የኦነግ/ኦሕዴድ አገዛዝ ከምድረ ኢትዮጵያ በማስወገድ ብቻ ነው፡፡ የሽግግር፣ የብሔራዊ ንግግርና የፍትሕ ጉዳይ የሚነሣው ፋሺስታዊው ‹ሥርዓት› ከምድራችን ከተወገደ በኋላ መሆኑን በቅጡ ያልተረዳ፣ ነገር ግን ከዐምሐራ ሕዝባዊ ትግል ጎን ነኝ የሚል ሁሉ ገና በድንቊርና ያለና የርጉም ዐቢይን የተቆረጠ ዕድሜ ለመቀጠል ከሚደረግ ነውረኛነት ተነጥሎ አይታይም፡፡

አሁንም ታላቁ መጽሐፍ ለጠቢብ ‹አንዲት ቃል ትበቃዋለች› ይላል፡፡ ነፍሳቸውን በገነት በመንግሥተ ሰማያት ያኑርልንና ጋሼ መሥፍን ‹አድማጭ ያጣ ጩኸት› እንዳሉት በወያኔም ሆነ በወራሹ የአገዛዝ ዘመን ኢትዮጵያን እንደ አገር ሕዝቧን እንደ ዜጋ ለማዳን የሚፈልግ ኹሉ አዋልደ ኢሕአዴጋውያንን ባለማመን መጀመር አለበት ብለን ለዓመታት እስኪታክተን ደጋግመን ብንጮኽም ሰሚ ዦሮ አላገኘንም፡፡ ከጉዳይም የጻፈን ያለ አይመስለኝም፡፡ ጠቢብና አስተዋይ ግን ጠፋ፡፡

መንፈሳዊው አስተምሕሮ ደዌያት ሁሉ አጋንንት እንደሆኑ ይናገራል፡፡ በዙሪያቸው ከተሰባሰቡ ጥቂት ደጋፊዎቻቸውና አድር ባዮች በስተቀር ወያኔም ሆነ ኦነጋዊው ኦሕዴድ እንዲሁም ዘላለማዊ ቋሚ ለጓሚያቸው ብአዴን የልቡሳነ አጋንንት ስብስብ መሆናቸውን ከፍሬአቸው የማያውቅ ኢትዮጵያ ያለ አይመስለኝም፡፡ ርጉም ዐቢይ ደግሞ ሰይጣንን መስሎና አኽሎ ሌጌዎን የሰፈሩበት÷ የሰበሰባቸው ‹ሠራዊተ አጋንንት አለቃ› ነው፡፡ ታዲያ የትኛው ሕዝብ ነው መንፈሱ በአጋንንት ተጠፍሮ በተያዘ ‹ሰው› አገሩና ዜጎቹ እንዲመሩ የሚፈቅድ? በመሆኑም ኢትዮጵያ ወይም ዐምሐራው ርጉም ዐቢይንና አጋንንታዊ አገዛዙን ከማስወገድ ሌላ ምርጫ የላትም፡፡ ‹እባብ› ጠላት መሆኑን ተረድቶ ‹ሰኰናችንን› ሳይቀጠቅጥ ራሱን ልንቀጠቅጠው ይገባል፡፡ ጊዜው በእጅጉ በመርፈዱ ብቻ ሳይሆን ከአጋንንት ጋር ድርድር የማይቻልና ለንስሐ ዕድል የሌላቸው በመሆኑ፡፡

Filed in: Amharic