>

የአማራ ሕዝብ የማንነትና ወሰን ጉዳይ በሕልውና ትግሉ ሂደት ቀይ መስመር ነው!

የአማራ ሕዝብ የማንነትና ወሰን ጉዳይ በሕልውና ትግሉ ሂደት  

ቀይ መስመር ነው!  

  (ከአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ በወቅታዊ የትግሉ ሁኔታ የተሰጠ መግለጫ) 

 ‹የአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ› አደረጃጀቶቹን አስፍቶ በአዲስ ምዕራፍ ወደትግል ሲገባ የሕዝባችንን ተጨባጭ ሁኔታዎች በመገምገም ነው፡፡ ቀጠናው የትግል ማዕከል ሆኖ ለረዥም ጊዜ የቆየባቸውን መነሻ ምክንያቶች ከወቅታዊ ሁኔታዎች አኳያ በማጤን፣ የአማራ ሕዝብ የተጋረጠበትን የሕልውና አደጋዎች ጠንቅቆ ይረዳል፡፡  

 ትግላችን የሕልውና ነው ስንል ጠላቶቻችን ሕዝባችንን በአገር አልባነት፣ በተቅበዥባዥነት እንዲኖር እየፈፀሙ ያለውን ፋሽስታዊ ተግባር በማየት ነው። ትግላችን የሕልውና ነው ስንል ጠላቶቻችን ቢችሉ ሕዝባችንን ጨርሶ ለማጥፋት ካልሆነም ርስትና ማንነቱን የተቀማ የተበተነ፣ የፖከቲካ ቋት የሌለው፣ በኢኮኖሚም ተንበርካኪ ማኀበረሰብ ለመፍጠር ያቀዱትን ክፉ ዕቅድና እየፈፀሙ ያለውን ተግባር በተጨባጭ በመረዳት ነው። ትግላችን የሕልውና ነው ስንል ጠላቶቻችን ተሳክቶላቸው ቢያሸንፉን በባርነት እንኳን እንዳንኖር እንደሚፈልጉ ስለምናውቅ ነው።  

 እነዚህ ተጨባጭ አደጋዎች የአማራ ሕዝብ የሕልውና አደጋ ውስጥ ከተውታል፡፡ የአማራ ሕዝብ ትግል የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኀበራዊ ጥያቄዎቹን ለማስመለስ ሳይሆን ቅድሚያ እንደሕዝብ ሕልውናውን ለማስከበር ያለመ ነው፡፡ በዚህ ትግል ሂደት ውስጥ የአማራ ሕዝብ የትግል አስኳል የሆኑ ታሪካዊ ርስቶቻችን፣ የማንነታችን አካል የሆነው ሕዝባችን ሕልውና የትግሉ ዋነኛ መነሻ ነጥብ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡  

በዚህ የሕልውና ትግላችን በጠላትነት የፈረጅነው ሕዝብ የለም፤ አይኖርምም፡፡ ነገር ግን በየትኛውም ሁኔታ የአማራ ሕዝብ ሕልውናን የማይቀበሉ፣ ሰብአዊ ክብራችን ተገፎና ተዋርደን እንድንኖር አበክረው የሚሠሩ የሕዝባችንን ሕልውና ለማጥፋት፣ ታሪካዊ ርስቶቹን በቀጥታ ጥቃትም ሆነ በሴራ ፖለቲካ ለመንጠቅም ሆነ አሳልፎ ለመስጠት የሚሰሩ የትኞቹም አካላት የሕዝባችን ጠላቶች ናቸው፡፡  

በዚህ የትግል ማዕቀፍ ውስጥ የአማራ ሕዝብ የጥቃት ምንጭ የሆነው ብአዴን-ብልጽግና እርሱ እንደትሮይ ፈረስ ያገለገላቸውና እያገለገላቸው ያሉ የእርሱ የቀድሞም ሆነ የአሁን አለቆች የአማራ ሕዝብ ጠላቶች ናቸው፡፡ የአማራ ሕዝብ አሁን ለገባበት ምስቅልቅል የዳረጉት በልጆቹ ከፍተኛ መስዋዕትነት ነጻ ያወጣቸውን ታሪካዊ ርስቶቹን አሳልፎ በመስጠት ሂደት ውስጥ ዛሬም ታሪክ ይቀር የማይለው ክህደት የፈጸመው ብአዴን-ብልጽግና ነው፡፡  

ይህን ሂደት ለማሳካት በጓዳ የፖለቲካ ስምምነት አድርገው፡- የአማራ ሕዝብ መከታ የነበረውን ልዩ ኃይል እንዲፈርስ አድርገዋል፤ ፋኖን ትጥቅ ለማስፈታት በሚል በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ዓላማ ያለው ጦርነት ታውጇል፡፡ አሁን ደግሞ ወረራውን በበጀት፣ በወታደራዊ ሎጀስቲክና በወታደራዊ ሽፋን ደግፈው መንገድ እየመሩ  በራያ አላማጣ፣ ራያ ኦፍላና ኮረም በኩል ወረራውን ማስፈጸም ላይ ናቸው፡፡  

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው እውነታ፣ የአማራ ርስቶችን ዳግም ለመውረር የተነሳው ትሕነግ፣ በእርሱ ዘንድ “ቋሚ ወዳጅ፣ ቋሚ ጠላት የለም” የሚለው ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ መርህ አይሰራም። አማራን ቋሚ ጠላቱ አድርጎታል። በ1968 ዓ.ም. በማንፌስቶው ላይ ያሰፈረውን ጠላትነት በቋሚነት ይዞት ዘልቋል፡፡ አቅምና እድል ባገኘበት ጊዜ ሁሉ አማራ ላይ የጥፋት ሰይፉን መዝዞ አጥቅቶታል። ይህ የሃምሳ ዓመት ደመኛ ጠላትነት የተከለ ኃይል የአማራና ትግራይ ሕዝብ የጋራ አብሮነት ድልድዩን ከቀደመው በከፋ ሁኔታ እየናደው ነው፡፡ ዛሬም ጊዜና ሁኔታዎችን አስልቶ በአማራ ሕዝብ ላይ የጭካኔ ሰይፉን ከአፉት የሚመዝ እንደሆነ በምስራቅ አማራ በኩል ያደረገው ሰሞነኛ ወረራ ጉልህ ማሳያ ነው፡፡  

እንደ አማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ ፖለቲካዊ ግምገማ፣ ትሕነግ ከቀደመ ስህተቱ የሚማር ሳይሆን፤ ለመሳሳት የሚኖር፤ በአማራ ጥላቻ የተለከፈ፣ የወጣበትን ሕዝብ ከወንድሞቹ ጋር ደም ማቃባትን ፖለቲካ አድርጎ ያመነበት፣ ፋሺዝምን ዕድሜ ልኩን መመሪያው ያደረገ የጥፋት ኃይል በመሆኑ ከእርሱ ሊቃጣ የሚችልን ጥቃት መመከት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡ 

  ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የአማራ ሕዝብ ሲዋደቅላቸው የኖረው ራያ አላማጣ፣ ራያ ኦፍላ፣ ኮረም፣ ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ታሪካዊ ርስቶቻችን በሁኔታዎች የማይቀያየሩ፣ ቋሚና ዘላቂ የማንነት እና የክብር ጉዳይ ነው፡፡  

 እነዚህ ታሪካዊ የአማራ ርስቶች የግዛት ሁኔታና የሕዝባችን ሥነ-ልቦናዊ ስሪት የሚወሰኑ የዕጣ ፈንታው ወሳኝ ጉዳዮች በመሆናቸው በሕልውና ትግሉ ሂደት ቀይ መስመር ሆነው የሚታዩ ናቸው፡፡  

  በመሆኑም የአማራን ሕዝብ ከበባ ውስጥ ለማስገባት በየአቅጣጫው የተከፈተውን አማራዊ ጥቃት በብቃት ለመመከት፣ በእስካሁኑ ተጋድሏችን የትግሉ ሰማዕታት በአንድነት ሕይወታቸውን የሰጡለትን  የአማራ ሕዝብ ፍትሐዊ ትግል በጽናትና በቁርጠኝነት እንደምናስቀጥል እያረጋገጥን የሚከተሉትን የትግል ጥሪዎች እናስተላልፋለን፡-  

   1) በሁሉም ቀጠና ለምትገኙ የፋኖ አመራሮቻችንና አባላቶቻችን፡- የጀመርነው የህልውና ትግል ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ግንባሮች ያሉት መሆኑ ታውቆ የጀመርናቸው ወታደራዊ ውህደቶች ተፋጥነው ‹አንድ ወታደራዊ ጠቅላይ መምሪያ› በመፍጠር ለሕዝባችን እንድናበስረው እየጠየቅን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቀወስ ጠማቂ የሆነው ትሕነግ ከተደጋጋሚ ታሪካዊ ስህተቶቹ ባለመማር በአማራ ሕዝብ ርስትና ማንነት ላይ እብሪታዊ ወረራ መፈጸሙ፣ ለዚህ ደግሞ የብአዴን ብልጽግና ችሮታ በግልጽ መታየቱ የፋኖን ወደአንድ ወታደራዊ ጠቅላይ መምሪያነት መምጣት የግድ ያደርገዋል፡፡ ስለሆነም የህልውና ትግላችን ግንባሮች እየሰፉ በመሆኑ በየአቅጣጫው የምንከፍለውን ዋጋ በሚመጥን መልኩ ለሁኔታዎች ምላሽ የሚሰጥ አደረጃጀት እንድንፈጥር ጥሪያችንን እናቀርባለን!!  

2) ለአማራ ሕዝብ፡- ተገደን በገባንበት የሕልውና ትግል፤ የአማራን ሕዝብ እንደሕዝብ ወደፊት የማሻገር አልያም እንደሕዝብ የመጥፋት ወሳኝ ታሪካዊ ዕጥፋት (historical juncture) ላይ መሆናችንን በማመን በዚህ የሕልውና ትግል ማሸነፍ ለኛ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥለው መቶ ዓመት ለሚመጡ ተከታታይ ትውልዶች የሕልውና ማረጋገጫ እንደሆነ በማመን አምርሮ መታገል ይገባል፤ በአማራ ሕዝብ ላይ  የተመዘዘው የጥፋት ሰይፍ ጠላቶቻችን “አማራ አንገቱ አንድ ነው” በሚል እምነት ሁሉንም አማራ ዒላማ ያደረገ ስለመሆኑ በተጨባጭ እያየነው ነው፡፡ ህጻን አረጋዊ፣ ሴት እናት፣ ሀብታም ደሃ፣ የተማረ ያልተማረ፣ ሙስሊም ክርስቲያን ሳይል በጅምላ የሚቀነጥስ የጅምላ ጥፋት በአማራ ሕዝብ ላይ ታውጇል፡፡ 

 በቅርቡ በተካሄደው የኮማንድ ፖስት ግምገማ የፋሽስቱ አገዛዝ ቀንደኛ አገልጋይ የሆነው ሌ/ጀኔራል ብርሃኑ በቀለ በዳዳ በተናገረው ንግግር ውስጥ፡- ‹‹የአማራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ተነስቶ እየተዋጋን ነው፤ ንጹሃን የሚባል የለም፤›› ማለቱን ከውስጥ አርበኞቻችን አረጋግጠናል፡፡ ስለሆነም የአማራ ሕዝብ ብቸኛው መዳኛው የጀመረውን ተጋድሎ አጠናክሮ መቀጠል፣ እንደሕዝብ እየደረሰበት ላለው ጥቃት ምላሹም እንደሕዝብ መሆን ይኖርበታል፡፡

3) ለትግራይ ሕዝብ ማስተላለፍ የምንፈልገው መልዕክት፡- ሥርዓት ይመጣል፣ ሥርዓት ያልፋል፤ የሕዝብ መስተጋብር ግን ቋሚና ዘላቂ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይልቁንም ደግሞ ሰሜኑ ክፍል በኢትዮጵያ ዳር ድንበር መጥበብና መስፋት ሂደት ውስጥ በርካታ ሥርዓታትን ያሳለፈ፣ በእነዚህ የታሪክ ሂደቶች ጉልበተኞች ሲነሱ ሲወድቁ፣ ሕዝቡ ግን ለጥንታዊቷ ለመካከለኛዋ አልፎም ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የግዕዝ ስልጣኔን ያወረሰ፣ ሴማዊ የባህል ተዋሃጅ፤ የውጭ ወራሪ ጠላቶችን በአንድነት በመመከት፣ አንድ ቤተሰብ ሆኖ ለሺህ ዘመናት በአብሮነት ዘልቋል፡፡ ይሁን እንጅ ትሕነግ በፈጠረው ሐሳዊ ትርክት፣ መዋቅራዊ ጥቃቶች፣ የግዛትና የማንነት ጭፍለቃዎች የተነሳ አብሮነታችን አደጋ ላይ ሊውድቅ ችሏል፡፡ በዚህም በታሪካችን ውስጥ ያልታየ የጋራ ጥፋት ለማስተናገድ ተገደናል፡፡ ካለፈው ጉዳታችን በአብሮነት ራሳችን ለማከም አንዳችን ለሌላኛችን መድሐኒት መሆን ሲገባን ትሕነግ የአማራ ርስትና ማንነቶችን ዳግም ለመንጠቅ፣ ከድርጅቱ ዕድሜ በታች የሆነ ሁለቱን ሕዝብ በማፋጀት ሥልጣኑን ለማስቀጠል ያለመ የደም ግብር የለመደ ግለሰብን አምኖ ለጦርነት ተነስቷል፡፡  

እንደአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ፣ ወደዳግም ጦርነት ተመልሰን የምንገባ ከሆነ ሁኔታዎችን አባባሽ እንጂ ገልጋይ የለንም፤ ከዚህ በኋላ የምናደርገው ጦርነት የማያቋርጥ የመጠፋፋትና የከፋ እልቂት የሚታወጅበት መሆኑን አውቃችሁ ድርጅቱ ከያዘው የጥፋት መንገድ እንዲታረም፣ ትብብር ልትነፍጉት ይገባል፡፡ ትላንት የተፈጠሩ በርካታ ስህተቶችን በጋራ እናርማለን በሚል የያዝነውን ብሩህ ተስፋ ከሚያጨልም ድርጊት እንዲቆጠብ በማድረግ የሁለቱ ሕዝብ ምሁራን እንደአንድ ቤተሰብ የሚታየውን የአማራ እና የትግራይ ሕዝብ ለእውነተኛ እርቅና አንድነት መንገዱን በጋራ እንድትጠርጉ ስንል ጥሪያችንን እናቀርባለን!  

 4) ለመላው ኢትዮጵያዊያን፡- ኢትዮጵያ በታሪኳ እንዲህ ዓይነት የጥፋት ዘመን አስተናግዳ እንደማታውቅ የታሪክ ገጾች ምስክር ናቸው፡፡ በጦርነት አዙሪት ትውልድና አገር እያወደመ ያለው ኦሕዴድ-ብልጽግና ወከልኩት ለሚለው ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ የመከራ ምንጭ ሆኖበታል፤ ለቀሪው ኢትዮጵያ ሕዝብ አደጋ ሆኗል፤ ይህ አገራዊ መናጋት የኢትዮጵያን ፍርሰት እያፋጠነው ነውና የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጠባብ ቡድንተኝነቱ ጥቅም ሲል ሀገር እያፈረሰ ያለውን አገዛዝን ለማስወገድ የምናደርገውን ትግል በአንድነት እንዲቀላቀለን ጥሪያችንን እናቀርባለን!    

  5) በውጭው ዓለም ለምትገኙ የአማራ ልጆችና የአማራ ትግል አጋሮቻችን፡- የገጠመን የሕልውና ጦርነት ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ጦርነቱ አካላዊ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲ፣ የሥነ-ልቦና፣ የሚዲያ፣ የመረጃ፣… ወዘተ ነው፡፡ በአማራ ሕዝብ ትግል ውስጥ የሀሳብና የፋይናንስ ምንጭ በመሆን የሚታገለው ዲያስፖራው ‹ባለንበት ሁኔታ ሁሉም አማራ የሕልውና ትግሉ አካል መሆን አለበት› በሚለው መርኾችን ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ እያቀረብን፤ እንደሕዝብ በዚህ የሕልውና ትግል ውስጥ ሁሉም አማራና አጋሮቻችን በመክሊቱ ተሳትፎ ሊኖረው ይገባል፤ ዲያስፖራ ወገናችን በጊዜና በቦታ ርቀት ሳትገደቡ ለምታደርጉት ተጋድሎ በትግሉ ሰማዕታት ጓዶቻችን ስም እያመሰገን፤ የትግሉን የዕድገት ደረጃዎች በመገምገም ተልዕኳችሁን ማሳደግ፣ ሚናችሁን ለይታችሁ ከሁኔታዎች ጋር በማጣጣም ትግላችሁን ማጠናከር ይጠበቅባችኋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ ላቀረበው የገቢ ማሰባሰቢያ ጥሪ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ትግሉን በገንዘብ እንድትደግፉ ጥሪችንን እናቀርባለን!!  

 በመጨረሻም የሕልውና ትግላችን ፍትሐዊ እና እውነተኛ በመሆኑ፣ በትግል ጉዟችን የማንጠራጠረው ሀቅ ቢኖር የጠላቶቻችንን አይቀሬ ሽንፈት ነው፡፡ የፋሽስቱ ዐቢይ አሕመድ አገዛዝ አይቀሬውን ውርደት፣ መራራውን የሽንፈት ጽዋ በቅርቡ ይጎነጨዋል፡፡ እስከዛው ታላላቆቻችን አርበኞች በተግባር እንዳስተማሩን በሞት ሸለቆ ሳይታለፍ ታሪክ መቀየር አይቻልምና አማራ በከበረ መስዋዕትነቱ ድሉን ያጸናል!! 

የማይሰበረው አማራ ለሕልውናው፣ ለክብሩና ለታሪኩ በጽናት መፋለሙን ይቀጥላል!! 

 የአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ 

ጎንደር-ኢትዮጵያ 

ሚያዚያ 11/2016

Filed in: Amharic