>

ግልጽ ደብዳቤ:- ያልተቀደሰ ጋብቻ መቅዘፍት ነው!

ግልጽ ደብዳቤ

ያልተቀደሰ ጋብቻ መቅዘፍት ነው! 

ራሳችሁን “የአብሮነት ኢትዮዽያ” በሚል የቡድን ስም የምትጠሩ ግለሰቦች በአቶ ልደቱ አያሌው  እጅ የተፈረመ ደብዳቤ ልካችሁልን ደርሶናል። የፊታችን ዻጉሜ 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በምታካሂዱት የበይነ መረብ ጉባኤ ላይ እንድንገኝም ጋብዛችሁናል። 

ሆኖም በዚህ ቡድን ውስጥ ከምትገኙ ግለሰቦች መካከል አንዳዶቻችሁ ከአገዛዙ ጋር ተቀናጅታችሁ በአማራ ሕዝብ ላይ በፈፀማችሁት የጅምላ ጭፍጨፋ ወንጀል፣ ከፊሎቻችሁ በአዲስ አበባ ኗሪ ብሎም በመላው ኢትዮዽያ ሕዝብ ላይ በፈፀማችሁት ለከት የለሽ ክህደት፣ ሌሎቻችሁ የወያኔ ፊታውራሪ በመሆን በፈፀማችኋቸው የዘር ማጥፋት፣ የጦር እና የሀገር ማፍረስ ወንጀሎች የምንፋረዳችሁ መሆኑን እናንተም ሆናችሁ የምንታገልለት ሕዝባችን እንዲያውቀው ስንል ይህንን ግልጽ ደብዳቤ ፃፍንላችሁ። በመሆኑም ከእናንተ ጋር የምንገናኘው በሕግ አደባባይ ከሳሽ እና ተከሳሽ ሆነን እንጂ በፖለቲካ ጉባኤ አባሪ ሆነን አይደለም። “ልዩነቶቻችን እንዳሉ ናቸው። ለዚህ ወደ ፊት የሽግግር ጊዜ ፍትሕ ይኖረናል። ዛሬ እኛ ባንታገለውም መንግስት በራሱ የውስጥ ችግር ሊወድቅ ስለሆነ ቀጥሎ ስለሚኖረው የሽግግር ሂደት ከወዲሁ እንምከር። ይህ ካልሆነ ግን ድሉ ይጠለፋል” ማለታችሁን በመገናኛ ብዙሃን ሰምተን ተገርመናል። ሟች እና ገዳይ ዛሬ አብረው እየሠሩ ስለነገ ፍትሕ ቢመክሩ ነገሩ ቂም ይዞ ጸሎት፣ ሳል ይዞ ስርቆት እንደ ማለት ነው። 

ተቋማችን የዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል እንደ መስታዎት የጠራ የትግል መስመር ግልጸኝነት ያለው፣ ወገን፣ ጠላት እና አጋሩን ለይቶ የሚያውቅ  ሃይል ነው። ስለዚህ የፖለቲካ ርጣት ላይ ለሚገኙ ወንጀለኞች መናጆ አይሆንም። በድምሩ ከላይ በገለጽነው ነሲብ አመክንዮ እና በሚከተሉት ዝርዝር ምክንያቶች ጥያቄያችሁን አልተቀበልነውም:- 

1- ግንኙነቱ ያልተቀደሰ ጋብቻ በመሆኑ 

በዚህ ቡድን ውስጥ የተሰባሰቡ የፖለቲካ ስብዕናዎች ለዘመናት በአጥፊ እና ጠፊ የተሰለፉ ከመሆናቸውም በላይ የክህደትን ክብረ ወሰን የሰበሩ በመሆናቸው ዛሬም ሊታመኑ አይችሉም። ምቹ ሁኔታን ሲያገኙ ተመልሰው ወደ መጠፋፋት መግባታቸው አይቀርም። በአንድ ሰሞን ደርግ እና መኢሶን ቢሻረኩም ተጠፋፍተዋል። ኦነግ እና ወያኔ በፍቅር እፍ ቢሉም የሽግግር ቻርተሩን ፅፈው ሳይጨርሱ ጦር ተማዘዋል። ከሰባት አመታት በፊት ብአዴን እና ኦሕዴድ በወያኔ የጣር ወቅት ቢመሳጠሩም ምስጢራቸው የትግሉን ፍሬ ከእውነተኛ ታጋዮቹ ማለትም ከአማራ እና ከኦሮሞ ወጣቶች ከመንጠቅ የዘለለ ሚና አልነበረውም። በፍጥነት ተኮራርፈዋል። አጥቂና ተጠቂ በመሆን የዛሬውን የጌታ እና ሎሌ ደረጃም ይዘዋል። “አብሮነት” በሚል ገበታ ዙሪያ እየተሰባሰበ ያለው ቡድንም ጀግኖች ደም ተራጭተው ያመጡትን ድል ወይን እየተራጨ ለመንጠቅ የሚጥር የሰነፍ ስብስብ ነው። በአስክሬን መሀል ተረማምደው ያመጡትን ድል በኢንተርኔት ለመጋራት የሚጥር ነው። 

ስብስቡ የሚያጋምደው ዘላቂ የፖለቲካ ካፒታል የለውም። ይልቁንም የሚያለያየው ይበልጣል። አገዛዙን ለማስወገድ ያለው ፍላጎት ብቻ አንድ አያደርገውም። ቢሯቸውን ዘግተው ከሀገር የወጡ፣ የፖለቲካ ርጣት ላይ የደረሱ እና ማኅበራዊ መሰረታቸውን የከዱ ግለሰቦች ቢሰባሰቡም ሆነ ባይሰባሰቡ አገዛዙ በጀግኖች ክንድ ተገፍትሮ መውደቁ አይቀርም። 

2- የትብብር ጥያቄውን ያቀረቡት በሕግ ሊጠየቁ የሚገባቸው ሰዎች በመሆናቸው

በዚህ ስብስባችሁ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች እሳት ቆስቁሰው ሕዝብን ከማገዶ በኋላ የሸሹ፣ አማራን በጅምላ ያስጨፈጨፉ፣ ያፈናቀሉ፣ ቤተ ከርስቲያን ያቃጠሉ፣ ካህን ያስገደሉ ናቸው። ከፊሎቹ ሰው ከእነ ነፍሱ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ወርውረው የገደሉ፣ የአማራን እናቶች ማህፀን በክኒን ያደረቁ ወንጀለኞች ናቸው። ታዲያ እነዚህ ወንጀለኞች ዘመን ሰጥቷቸው በሕግ ፊት ሳይቀርቡ ቢያልፉ እንኳን በእንግሊዝ በእነ ቻርልስ እና ኦሊቨር እንደ ተደረገው ለፍትሕ ስንል ከመቃብር አውጥተን ለፍርድ የምናቀርባቸው እንጂ የምንተባበራቸው አይደሉም። 

3- የሕዝባችንን ሞራል ለመጠበቅ 

ከእናንተ ጋር ብንሰለፍ ክህደት፣ የዘር ፍጅት ወንጀል እና የጦር ወንጀል በፈፀማችሁበት ሕዝባችን ሞራል ላይ እንደ መሳለቅ ይቆጠራል። ስለዚህ ለኅሊና ተጠየቅ ስንል አናደርገውም። ይልቁንም የበደላችሁትን ሕዝብ በይፋ ይቅርታ እንድትጠይቁት እናሳስባችኋለን። 

4- ያለነው የኅልውና ትግል ላይ በመሆኑ 

የሕዝባችንን በሕይዎት የመኖር መብት ለማረጋገጥ እየታገልን በመሆኑ የፖለቲካ ማመቻመች ለማድረግ ፋታ የለንም። በሕይዎት ለመኖር ባለን ውስን ጊዜ ራሳችንን እንከላከልበታል። 

5- ስብስቡ የሀገር ግንጠላ አጀንዳን ያነገበ በመሆኑ

በአንድ የበይነ መረብ ጨዋታችሁ ላይ የትግራይ ተወላጅ መሆኑን የገለፀ ተጨዋች እወክለዋለሁ የሚለውን ማኅበረሰብ ይዞ የመገንጠል አላማ እንዳለው ገልጿል። “የመገንጠል ጥያቄ በእንግሊዝ፣ በካናዳ፣ በስፔን የነበረ ነው። ያለ ነው” ሲል አቶ ልደቱ አያሌው ሀገር ማፍረስ ተገቢ መሆኑን ለጋዜጠኞች ሲያስረዳ ተሰምቷል። ይህ ትናንተ ከፈፀማችሁት በተጨማሪ ዛሬም የሀገር ማፍረስ ወንጀል ላይ መሰማራታችሁን የሚያረጋግጥ ነው። 

6- ከጀርባችሁ ከእናንተም የከፉ አጥፊዎች ያሉ በመሆናቸው

በዚሁ የስክሪን ጨዋታችሁ አቶ ጃዋር መሀመድ “ከጀርባችን በፎቶ የማይታዩ ሰዎች አሉ” ሲል ተደምጧል። ይህም ስብስቡ የሽፋን መሆኑን አረጋግጦልናል። 

ከዚህ በአሻገር በአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል ውስጥ ብሎም በእውነተኛ ኢትዮዽያውያን የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኙ ፖለቲከኞች ሁሉ ራሱን “የአብሮነት ኢትዮዽያ” በሚለው ቡድን ውስጥ እንዳይሳተፉ ስንል እናሳስባለን! የአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የድል ቀማኞችን በይፋ እንዲያወግዙ እንጠይቃለን።

የአብይ አሕመድ አገዛዝ በእውነታኛ ታጋዮች ክንድ ይወገዳል! የድል አጥቢያ አርበኝነት በዚህ ትውልድ አይደገምም! 

የዲሲ የጋራ ግብረ ኃይል

ነሐሴ 23 ቀን 2017 ዓ.ም. 

ዋሽንግተን ዲሲ

Filed in: Amharic