መውጫችን ስር ነቀል ለውጥና ማሸነፍ ብቻ ነው!
ነገሮች መስመር ሲይዙ፣ መልክ ሲያበጁ፣ ምስል መከሰት ሲጀምሩ፣ የአማራ ወጣት ከክንውኑ ጀርባ ርዕዩን አንግቦ ሲተም፤ በደሙ፣ በነፍሱ፣ በአካሉ፣ በወዙ፣ መከፈል ያለበትን ሁሉ እየከፈለ በዋጋ ሊተመን የማይችለውን የዘመኑን እንቡጥ ለወገኖቹ ነጻነት አሳልፎ እየሰጠ፣ በትግሉ አውድማ ላይ ነፍሱን እየዘራ፣ የቆሰሉና የተሰዉ ወንድሞቹን በየበረሀው በየሸጡ መራራ እንባውን እያፈሰሰ ‘እንዲህ ነው’ ሊባል በማይችል የቁጭት መንፈስ አፈር አልብሶ ወደፊት የሚተመው ድሉ እየቀረበ መምጣቱን ስለተገነዘበ ነው።
ለአማራ ልጅ የድል ብስራት መቃረብ ግንባሩን ሳያጥፍ ወደፊት በሚፈጥንበት በዚህ ወቅት፤ የልጆቹ ድካም ፍሬ ሲያፈራ የሚያየው አርሶ አደር ወደ ላይ አቅንቶ ቀኒቷን በሚናፍቅበት በዚህ ግዜ፤ አሸልበው የነበሩ ባንዳዎች ትግሉን ከእጁ ነጥቆ ሰቆቃውን ለማርዘም መርመስመስ መጀመራቸው ያሳዝናል።
የትግሉ ባለቤት መከራ በሚዘንብበት ወቅት፣ የእሱ የሚስቱና የልጆቹ ህይወት እንደቅጠል ይረግፍ በነበረበት ወቅት እንዲህና እንዲያ እያሉ ያለ ስሙ ስም ያወጡለት የነበሩ ሙሾ አውራጆች በደም ማንነታቸውን ሳያጸዱ፣ “ሰፋ ሰፋ አርጉልንና እንዳኛችሁ” ይሉን መጀመራቸው አይደንቀንም። ምክንያቱም አዝመራ ባለበት ሁሉ ምትሀት እንዳፈላው ኩብኩባ ለማውደም መቻኮል ባህሪያቸው ነው። በባህሪያቸው ወንበር ወንበር የሚሸትበት ቦታ ክብርና ስልጣን ይሸቀጥበታል ብለው በሚያስቡበት ስፍራ ሁሉ እየተገኙ ከባቢው ላይ በባለ እርስት መንፈስ መስፈር እርስ በርስ የዳቦ ስም እየተሰጣጡ ከፍታውን መቆጣጠር ዋንኛ ተግባራቸው ነው። አስረጅ ቢያስፈልግ ሰሞናችንን ማስተዋል በቂ ነው። እንደዘመናችን አጭልጎች ‘በአየ በሰማ’ ለመዝገን ጭብጣቸውን አስፍተው መጠባበቅ ያዋጣል ብለው ስላመኑ ያለስፍራቸው እየተገኙ ስልጣን ስልጣን ይጨዋወታሉ። በሚገርም ቅጽፈት ቆዳቸውን የሚቀይሩ ከዘመንጋ የሚሽከረከሩ እና ከነፈሰውጋ የሚነፍሱትን እብቆች ከማየት የከፋ ህመም የለም።
እንደ አንዳንዶች ዘርፈው ነጥቀው በልተውና ቀላውጠው ዞር ቢሉ ባልከፋ ነበር ። ነገር ግን እንዴት አድርጎ ማልያ እንደሚቀየር፣ እንዴት ተደርጎ ቆዳ እንደሚገፈፍ…እንዴት ተደርጎ ህሊና እንደሚሸጥ…እንዴት ተደርጎ አይን እንደሚቀቀል ስለተካኑበት ላንዴን ለመጨረሻ ጊዜ ሊፈጥሙን እንደ ተኩላ መንጋ ተቧድነው መምጣታቸው ምን ያክል እንደናቁን ማሳያ ነው። ከመች ከመቼ ካይንም ከልብም እርቀዋል ብለን በራሳችን ጉዳይ በተጠመድንበት በዚህ አንገብጋቢ ጊዜ ለዳግም ግልቢያ ዝግጁ ነን! ብለው በአደባባይ ሲሞከሻሹ ከማየት የከፋ ህመም ይኖርን? ማንነታችሁ በምድሪቱ ለሚኖር የአማራ ልጅ ሁሉ የተገለጠ ነውና ዳግም እራሱን ሚያሞኝላችሁ የለም።
የሀገሬ ገበሬ ፈረሱን አሳዩኝና ጌታውን ልንግራችሁ እንዲል፤ እኛም ስብስባችሁን ተመልክተን ጋላቢያችሁን ስላወቅን በመንገዳችን ላይ እንዳትቆሙ ብለን እንመክራለን…!
መውጫችን ስር ነቀል ለውጥና ማሸነፍ ብቻ ነው
✝️ Lina🦅 (@Unity_for_Amhar) On X