ሠርፀ ሚ
ሕጻን እንደተወለደ እትብቱ እዛው እተወለደበት ቀዬ ይቀበራል። የሰው ልጅ እግዚአብሄር በሕይወት ይኖር ዘንድ የወሰነለት ዘመን ሲያከትም አካሉ እዛው እትብቱ በተቀበረችበት አገር ያርፋል። ይህም ማለት ማንነቱ ከራሱ ተፈጥሮአዊ አፈር ጋር ዳግም ተዋሃደ ማለት ነው። አገር ሠፊ እና ተፈጥሯዊ ትርጉምን አዝላለች። መልካሙ አስተማርያችን ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ስለ አገር እንዲህ ጽፈው ነበር፣ “አገር በታሪክ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በልማድ፣ በተስፋ፣ በደስታና፣ በመከራ ተሳስሮ የሚኖር አንድ ወገን የሆነ ሕዝብ የሚኖርበት የዓለም ክፍል ነው። አገር ማለት አያት ቅድም አያት የተወለዱበት፣ አድገውም በጀንግነት ከውጭ ጥላት እየተከላከሉ ለሕዝብና ለመንግሥት የሚጠቅም ሥራ ሠርተው ዕድሜያቸው ሲደርስም ልጆቻቸውን ተክተው የተቀበሩበት ጉድጓድ ነው። በመወለድ እትብት፣ በመሞት አካል ከአፈሩ ጋር ስለሚዋሃድ የአገሩ አፈር ሕዝቡ በላዩ የሚኖርበት ማለት ነው። እግዚአብሄር ከምድርዋ ፍሬ ሕይወት እንዲገኝባት በማድረጉ አገር እያጠባች የምታሳድግ ፍቅርዋ በአጥንት በሥጋ ገብቶ የምይምለስ የሆነች እናት ማለት ነው። …..”
ዘመኑ የፈጠረው ባዕድ ፖለቲካ በተለይም ደግሞ የፈረንጁን ሙሉ ትምህርት ያልቀሰሙት የፖለቲካው አቀንቃኞች፣ ምሉዕ ባልሆነ፣ ባልተገራ አስተሳሰብ ውዲቱ አገር ኢትዮጵያን እዛሬው ምስቅልቅል ውስጥ ዳረጓት። ክፉ ልኅቃን ያበጃጁት የዘር ፖለቲካ ኢትዮጵያ በታሪክ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በልማድ፣ በተስፋ፣ በደስታና፣ በመከራ ተሳስሮ የሚኖር አንድ ወገን የሆነ ሕዝብ የሚኖርበት የዓለም ክፍል እንዳትሆን ሽብልቅ ሆነባት። የኢትዮጵያ ልጆች በጀንግነት የውጭ ጠላትን እየተከላከሉ ለሕዝብና ለመንግሥት የሚጠቅም ሥራ ሠርተው እንዳይኖሩ “የተማሩት” የነደፉት ወልጋዳ የፖለቲካ ሃሳብ ከንቱነትን አመርቅዞ ስደትን አበዛ። ማንም ሲወለድ እትቱ – ሲሞት አካሉ ከአፈሩ ጋር የሚዋሃድባትን የተፈጥሮ እናት አገሩን ትቶ ስደትን ምርጫው አየደርግም።
አገር ማንነት ነች፣ ስም ማንነት ነው፣ ጾታ ማንነት ነው፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ነገድ ማንነት ናቸው። ትምህርት፣ ሙያ፣ አቋም፣ ወዘተ፣ ተጨማሪ የማንነት መገለጫዎች ናችው። ስደት እነኚህን ማንነቶች ሁሉ አፈር ድሜ አልብሳ እማንነት ቀውስ (identity crisis) ውስጥ ትከታለች። ይህ ሆን ተብሎ በሙያተኞች የተነደፈ የሥነ–ልቦና ደባ ነው። ኃብታም አገሮች ትላልቅ እጆች አሉዋቸው። አንደኛው እጅ ደሃ አገሮችን በምጣኔ ኃብት እያዳሸቀ አለመረጋጋትን እያባባሰ ዜጎችን ማሰደድ ሲሆን ሌላኛው እጅ የተሰደዱትን በማያቋርጥ ጥርጣሬ ውስጥ ክቶ በማንነት ቀውስ ማሾቅ ነው። ሌሎቹ እጆች የዕዳ ባርያ፣ ተንበርካኪ፣ ሸቀጥ አድናቂ፣ ባህልና ወግን በራዥ፣ ምቾትን ወዳጅ፣ ወዘተ፣ የማድረግ ኃይል አላቸው።
በአንድም በሌላም ይሁን – ችግር ነው እክፉዋ ስደት ላይ የሚጥለው። ስደት ቀጣፊ፣ ዋሾ፣ ተጠራጣሪ፣ ብኩን፣ ፈሪ፣ ብኩን፣ ወዘተ፣ ታደርጋለች። በያን ዘመን የተማሩት የወረወሩት ድንጋይ ተከምሮ ወደ ማይፈለጥ ዓለትነት ተቀይሮ ትውልዱን ለተገለጠ የሥጋ ሥራ ዳረገ። ይህን ዓለት መፍለጡ ነው ትልቁና አስቸጋሪው የዚህ ትውልድ የቤት ሥራ። ይህን ዓለት ፈልጦ ወደ አማረ ቅርጽ ለመለወጥና ያለፈውን መከራ ለመቅረፍ አስተዋይ ሃሳብ (critical thinking) ወሳኝ ነው። ሃሳብ እውቀትን ትወልዳለች። አስተሳሰብ ከሌለ አለማወቅ ታይላለች። ለዘብተኝነት ሃሳብን ታመክናለች። ጽንፍ ሃሳብን ታስፈራራለች። ደሃ አገሮች እውቀትን መድፈር አቅቷቸው በወረደ ነገር ብቻ እንዲሻኮቱ የሚያደርጉት አበዳሪ ባለሃብቶች ናቸው።
ዓለም ሕይወትን ማስተናገድ እየከበዳት ነው። የመጨረሻው ቀን ማለት ይህ ነው። የክፋቱ ክምችት፣ የነውሩ ክምር ሲበዛ እግዚአብሄር ትዕግስቱ ያልቃል። የዘንድሮ ሰዎች የእግዚአብሄር ትዕግስት ሊያልቅ በተጠጋበት ዘመን የምንኖር ነን። “በዚያን ጊዜ ይላል ፍካሬ ኢየሱስ ወምክረ አበው፣ “በዚያን ጊዜ ሐሜት፣ ትዕቢት፣ ስድብ፣ ራስን መውደድና ማክበር፣ መማለጅ ወይንም ጉቦ ተቀብሎ ፍርድ ማጣመም፣ ገንዘብን መቀማት፣ ወንድምን መግደል፣ በሓሰት መምስከር፣ መስረቅ፣ ሃሰት መናገር፣ ድንበር መግፋት፣ ወሰን መግፋት፣ አጥር መስበር፣ ቤት መሰርሰር ይበዛል፣ ወንድም ወንድሙን ለገንዘብ ይለውጣል፣ ፍቅርም ከነሱ ትርቃለች…”።
ስደት ዝባዝንኬ ነች። ስደት ሊያሰማምሯት የማይቻል ድሪቶ ነች። ቢሆንም አንድ ነገር አለ። በስደት ከሚኖርበት – ብዙ ወርቅ ከሚታፈስበት አገር ይልቅ – ምንም ትሁን ምንም –እናት አገር ማርና ወተት ነች። ማንነት ከአልማዝና ከእንቁ ትበልጣለች። እግዚአብሄር ለእያንዳንዱ ግለሰብ የሚሰራው በጎ ሥራ አለ። “ሁሉም ለበጎ ነው” የሚባለው ለዚህ ነው። ማንም በእግዚአብሄ ነገር ጣልቃ አይግባ። መጠቋቆም፣ ምቀኝነት፣ ቅናት፣ ሃሜት፣ አሉባልታ፣ የሰው ስምን ማጥፋት፣ የመሳሰሉትን ክፋቶች ልንጸየፋቸው ይገባል። ስሜትን ቀስቃሽ (sensitive) የሆኑ ጉዳዮች ባይሰራጩና ባይራገቡ መልካም ነው። ፍርድ ቤት እኮ በዝግ ችሎት የሚፈርደው የሰዎችን ዓዕምሮ ለመጠበቅ፣ መጥፎ ድርጊትን በእጥፍ ላለማባዛት፣ ገመናን ለመሸፈንና የአገርን ክብር ከፍ ለማድረግ ነው። ያልተንገዋለለ፣ ያልተበጠረ፣ አዋቂዎች ያልመከሩበት ነገር ሁሉ ጎጂ ነው።
ወገኖቼ! ብሶት እየፈረጠመች ነው። እልህ እያየለች ነው። ቅናት እያደገች ነው፣ ዘረኝነት እየተባባሰ ነው። እነኚህ ፍላጻዎች የወጣቱን ዓዕምሮ ያውካሉ። ማመዛዘን የማትችል ክፋት የወረራት ዓዕምሮ ምንም ከመሥራት ወደ ኋላ አትልም። ክፋቶች ካልታቀቡ በቀር አልፎ ተርፎ “ሁሉን ለበጎ” አድራጊውን እግዚአብሄርን ያስቀይማል። ጦርነት የሁሉንም በር እያንኳኳ ነው። ሁሉም አስፈሪ ሆኗል! ምን ማድረግ ይገባናል? ብሎ የመመካከርያ ጊዜው አሁን ነው፣ ነገ አይደለም።
በርታ፣ ቀና በል ወንድሜ – በርቺ፣ ቀና በይ እህቴ – እግዚአብሄር ሁሉን ለበጎ ያደርገዋል!!

























