ሃይማኖትና ፖለቲካ : አብሮ ሲቦካ !!

ከድር ጠንክር : መርካቶ

 

ኑ ! ዓብይ አህመድ : ገነትን : ወይም  ጀነትን : ያወርሳችኋል : ተደመሩ !!

ቢያሻችሁ ብዙ ተባዙ ! ምድርን ሙሏት ! መንግሥተ ሰማያት የእናንተ ትሆናለችና !!

ወንጌለ መደመር: ምዕራፍ ቅጥፈት : ቁጥር አንድ ::

ተደማሪ ፕሮቴስታንቶች፤….. ተደማሪ ኦርቶዶክሶች፤…. ተደማሪ ጴንጤዎች፤ …. ተደማሪ ጠንቋዮች፤…. ተደማሪ ሙስሊሞች… ተደማሪ ፓስተሮች፤… ተደማሪ ጳጳሳት፤ ተደማሪ ሼኮች፤… ተደማሪ ሃጂዎች… ተደማሪ ቀሳውስት፤… ተደማሪ ዲያቆናት፤…. ተደማሪ ጋዜጠኞች፤…. ተደማሪ ወሬኞች፤…. ተደማሪ ገዳዮች፤….ተደማሪ ዘራፊዎች፤…ተደማሪ አዝማሪዎች፤…. ተደማሪ ጨፋሪዎች፤…… ተደማሪ ከሳሾች፤… ተደማሪ መስካሪዎች፤…. ተደማሪ ዳኞች፤…. ተደማሪ የድንቁርና ፈላስፎች፤…. ተደማሪ ሆዳም ምሁራን ተብዬዎች፤….ተደማሪ አሰፍሳፊዎች፤….. ተደማሪዲያስፖራ፤…….ተደማሪ ላሜቦራ፤…. ተደማሪ……ተደማሪ…….ተደማሪ…… ወዘተ.

ዕውቀትን ገድለው፤ ድንቁርናን የሚሰብኩየማሰብ ነፃነትን ገድበው፤ ዘረኝነትና ጎሠኝነትን ያነገሡ፤ ጥላቻን ዘርተው፤ በቀልን መረቱከአንድ ዓይነት የለት ድንጋይ ተጠርበው የተሠሩ የድንቁርና ጌቶች፤ ወደ እንጥርጦስ ከመውረዳቸው በፊት፤ በመቃብራቸው አፋፍ ላይ ሆነው፤ የመቃብራቸውን ስፋትና ጥልቀት እየለኩ፤ በቁማቸው ተዝካራቸውን ደግሰው እየበሉ ይጨፍራሉ ::

የወገኖቻችን ጩኸት ለእነሱ ሙዚቃቸው ነው:: የእናቶቻችን ዕንባ ለእነሱ የሚጨልጡት ውስኪያቸውነው :: የወገኖቻችን እሬሳ፤ ለእነሱ የሚበሉት ቁርጥ ሥጋ ነው:: የወገኖቻችን መፈናቀል ለእነሱ ጭፈራቸው ነው :: በጦርነት እንደ ቅጠል የሚረግፉት ወንድሞቻችን ዕህቶቻችን ሞት፤ ለእነሱ ፋሲካ እንደሚታረድ ፍሪዳ እንጂ ሰዎች አይደሉም :: በኑሮ ውድነት ችጋር የሚማግዷቸው ወገኖቻችን ለእነሱ ሰዎች ሳይሆኑ፤ እግራቸውን አንፈራጠው የሚሞቁት እሳት ማገዶዎች ናቸው ::

እኔ እምለው ! በሰዎች ላይ በሚፈጠር፤ የበደልግፍና ጭካኔ መጠንፍጅት ወንጀል ብዛትገነትን : ወይም ጀነትን : የሚያወርሰውየዓብይ ዓህመድ አምላክ የት ነው ያለው ?!

እኛ የማናውቅህ፤ ምናልባት አንተ እያጮለቅህ የምታየን፤ የዓብይ አህመድ ዓሊ አምላክ ሆይ!  

አንተ ማን ነህ ? ?!!
የት ነው ያለኸው ?!
ማን ትባላለህ ?!
ምን ታያለህ ?!
ምን ትሰማለህ ?!
ምን ትሠራለህ ?!
በእጅህ ምን ይዘሃል ?!
በአይምሮህ ምን ይመላለሳል ?!
ወንድማማችነትና ፍቅር፤ ሠላምና ፍትህ፤ ምነው ካንደበትህ አይፈልቁ ?!
ቂም ተረግዞ፤ የበቀል በትሩ በዝቶ፤ ህዝብ ሲታረድ ዝምታህ ምነው ነገሠ ?!
ፍትህ የምትለዋን ቃል ታውቃታለህ ?!
ፍርድህ ለመቼና ለእነማን ነው ?!  

ባላውቅህም: በሥነ ምግባር ተኮትኩቼና ታርሜ፤ ያደግሁ በመሆኔ፤ በጨዋ ደንብ የእግዜአብሔር ሠላምታ ላስቀድም ::

እንደምን አለህ ?!  

እንደምገምተው: አንተን አይርብህም፤ አይጠማህም፤ አይበርድህም፤ አይከፋህም፤ አትታመምም፤ አታዝንም፤ ሞት አንተ ደጃፍ ድርሽ አይልም ፤ ምን ቁርጥ አድርጎት ?!

እንዴት ነው አንተ ባለህበት ቦታ ምን ይወራል ? ምን ይሠራል ?  ምን ይበላል ? ምን ይጠጣል ? ምን ይለበሳል ? የት ይዋላል ? የት ይታደራል ?

እኛ ባለንባት፤ ኢትዮጵያ በምትባል አገር፤ እየተደረገ ያለውን ታውቃለህ ?! ታያለህ?!

ትሰማለህ ?!  

አልሰማህም ? አልነገሩህም ?!  ወሬ የሚያቀብልህ አሳባቂ ቢጤ የለህም ?!  ….. አልቀጠሩልህም ?!  ሌላው ሁሉ ቢቀር፤ « ያመነ የተጠመቀ ይድናል ሳይሆን »፤     « ያመነ የተደመረ ይድናል » የሚለውን የዓብይ አህመድ ወንጌን፤ ምዕራፉንና ቁጥሩን ጠቅሶ፤ የሚያነበንብ ፓስተር፤ ወይም የተደመረ ካድሬ ብቅ ብሎ ሹክ አላለህም ?!

ወይስ አንተም ቀደም ብረህ : አብረህ ተደምርሃል ??

አይ አለመታደል !!

አንተንም : በጎሣና በዘር ጠርፈው፤ በክልልህ እንድትኖር : አጠሩብህ ?!  

ከሰማያዊው ክልልህ ዝቅ ብለህ ብናገኝህ፤ ወዮልህ ! አቃቂ ፤ ቂሊንጦ፤ ወይም ዝዋይ ወህኒ ቤት ነው የምንከትህ፤ ብለው አስፈራሩህ ?!  

አላርፍ ካልክ ደግሞ « ኮሬ ኔጌኛን » ልከን እስከወዲያኛው ያሰናብትሃል ብለው ዛቱብህ ?!

ያለህበት ሰማየ ሰማያት ድረስ ድሮን ልከን: እንደ ቅጠል ባናረግፍፍ ወዮልህ ብለው  ጣታቸውን ቀሰሩብህ ?!

እነሱ ማንን ፈርተው ?!  ሁሉ በእጃቸው !! ባንኩም፤ ታንኩም፤ ድሮኑም ጥይቱም  የእንሱ :: ወታደሩ ኬኛ፤ ፖሊሱ ኬኛ፤ ፍርድ ቤቱ ኬኛ፤ ዳኛው ኬኛ: ቀበሌው ኬኛ፤ እየሱሲ ኬኛ፤ ዋቃኒስ ኬኙማ ካሉ ቆይተዋል ::

ከፈልግህ እንደቅጠል ያረገፍናቸውን፤ የትግራይ፤ የአማራና የኦሮሞ ወጣቶችን፤ እናትና አባት፤ አሮጊትና ሽማግሌዎች፤ አዛውንት፤ ቀሳውስትና መነኮሳትን ተመልከት አሉህ ?!

ምን ይኸ ብቻ ! ያለ እናትና አባት ያስቀሯቸውን ህፃናት፤ ልጆቻቸውን በጦርንነት  በመማገድ፤ ያለ ጧሪ ያስቀሯችውን አባትና እናቶች፤ አሮጊቶችና ሽማግሌዎችን፤ ቁልቁል ተመልከት አሉህ ?!

ለማመን ከፈለክ፤ በቦንብ ያፈረስናቸውን ትምህርት ቤቶች፤ በድሮን የደረመስናቸውን ሆስፒታሎች፤ በእሳት ያጋየናቸውን የገበሬዎች ቤቶችና ዕህል፤ የመዘበርናቸውን የልማት ተቋማት፤ ያፈረስናቸውን የድሃ ቤቶች፤ የእርሻ መሬታቸውን የነጠቅናቸውን ገበሬዎች፤ ከመኖርያ ቤታቸው አፈናቅለን ህጋዊ ድሆች ያደረግናቸውን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ዜጎች ተመልከት አሉህ ?!      

እናም: !  አንተም ፈርተህ፤ ላለማየት ዓይኖችህን ጨፈንክ፤ ላለመስማት ጆሮዎችህን ደፈንክ፤ በጥቅሉ ዝም ማለቱን፤ መረጥክ ::

እነሱ ላንተ ሁሉንም ደብቀው « ለዓብይ አህመድ ዓሊ መንግሥት፤ እየሱስ እረጅም ዕድሜ እንዲሰጠው ጠልዩ » ቢሉም፤ እኔ ሰዎች ሁሉ በየ ቤታቸው፤ በሥራ ቦታ፤ በየሰፈሩ፤ በየመንገዱ፤ ሆነው የሚሉህን ሳልደብቅ ልንገርህ ::

የዓብይ አህመድ ዓሊ አምላክ፤ አያይም ዐይኑ ታውሯል፤ አይሰማም ጆሮው ደንቁሯል፤ እጁ ብቻ ረጅም ነው፤ ሕፃናትን፤ አሮጊቶችና ሽማግሌዎችን፤ አዛውንትና መነኮሳትን፤  መንድሞቻችንና እህቶቻችንን፤ በቦምብ ይጨርሳል፤ በድሮን እያሰሰ ትምህርት ቤት ያፈርሳል፤ ሆስፒታል ይደረምሳል፤ ቤተክርስቲያንና መስጊድ፤ ገዳማት ሳይቀሩ በድሮንና በመትረየስ ያፈራርሳል ይሉሃል ::

እንግዲህ መልስህ ምን ይሆን ?!!  

አንተ ታውቃለህ ! እንዳልል፤ ማወቅህን ተጠራጠርኩ !!

ዓብይ አህመድ አሊ፤ ለእኔ ሥልጣን ስትል የሞተች ነብስ፤ ክርስቲያኑ ገነትን፤ እስላሙ ጀነትን ይወርሳሉብሎ ነግሯቸዋል ::  እነሱም ያውቃሉ : እኛም ሰምተናል ::  

ለመሆኑ የተዘጋጀላቸው፤ ኮንደምንየም ነው ወይስ ቪላ ቤት ?!  የተንጣለለ አዳራሽ፤ ወይስ ወደ አንተ ቀረብ እንዲል ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ?!  

ባባትህ ዕውነቱን ንገረኝ !

እኔ ያልገባኝ ነገር፤ ቀደም ብለው ገነት ወይም ጀነት የገቡትን፤ ጻድቃን፤ እንደ ዓብይ አህመድ አፈናቅለህ፤ ወደ ገሃነም፤ ወይም ጀሃነም፤ እንዲገቡ አድርገህ ነው ? የዓብይ አህመድ ታደሮችን ወንጀለኞችን በመንግሥተ ሠማያትህ ተቀብለህ ለማስተናገድ የወሰንከው ?!

« ጉድ ሳይሰሙ መስከረም አይጠባም » ስትል እሰማ ነበር እናቴ፤ አፈሩ ይቅለላትና ::  ጉዷን አልሰማች !  ዓብይ አህመድ የመኖሪያ ቤቷን አፍርሶ ያፈናቀላት ምድራዊ መከራዋ አልበቃ ብሎ፤ በድጋሚ የዓብይ አህመድ አምላክ፤ ነብሷን ካረፈችበት አፈናቅሎ ወደ ገሃነም አሽቀጥሮ ሊጥላት፤ መወሰኑን ስትሰማ፤ የምትለውን ለመስማት ጓጓሁ ::

ብጓጓ ምን ይፈረድብኛል ?! ልጇ ነኝ እኮ !!

በአካሉም ሆነ በህሊናው ዘቅጦ፤ የዕህል ጆንያ በመሆን፤ ሰብዕናውን አዋርዶ ለሆዱ ካደረ፤ አጉል ሰው ተብዬ  በቀር፤ ማን ነው ስለ እናቱ፤ ስለ ወገኑና ስለ አገሩ የማይጓጓና የማይጨነቅ ?!

እነሱ በሉና ሲጠጡ : እንዲያሸቱ ብቻ ተፈረደባችሁ ወገኖቼ : ይችን ስላቅ ለበስ ሃቅ፤ ባለ ሱቆች : በሱቆቻችሁ፤ ባለ ጋዜች :በጋዜጦቻችሁ፤ ባለ ድረ ገጾች : በድረ ገጾቻችሁ፤ ባለ ዩ ትዩቦች : በ ዩ ትዩቦቻችሁ፤ ቲክ ቶከሮች : በቲክቶችሁ፤ እግረኞች : በእግራችሁ እየሄዳችህ ለፋሲካ በዓል ጋብዙልኝ ::                                                                                                        

አደራ ብያለሁ ! አደራ እንዳትበሉ !!

አብሽር !!

የናንተው : ከድር ጠንክር !!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.