በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)፤
ምክንያተ ጽሕፈት፤ አንዲት መንፈሳዊ ወዳጄ የጌታችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለትን ምክንያት በማድረግ፤ “እኛ የሰው ልጆች ዋጋችን ስንት ነው? ልካችንስ ምን ድረስ ነው?!” በሚል ርእስ አንድ ጽሑፍ አካፍላኝ ነበር። እናም ይህ የወዳጄ ጥልቅ መንፈሳዊ ሐሳብን ያዘለ መጣጥፍ ይህን ጽሑፍ አዋልዷል።
“ከተፈጠርንበት ጥበብ ይልቅ የዳንበት ጥበብ ይበልጣል!!”
ሐሳቡን እናፍታታው ዘንድ ጥቂት አብረን እንዝለቅ. . .፤
ዋጋችን/ልካችን ምን ድረስ ነው? ምን ያህልስ ነው? ልካችንን/ዋጋችንን በቅጡ ያለማወቅ የሚፈጥረው የማንነት ዝብርቅርቆሽና የሕይወት ስንክሳር የትና እምን ድረስ ነው? የሚለው ጥያቄ ከፍጥረት ማግሥት ጀምሮ በርካታ ሊቃውንትን፣ የምድራችንን ፈላስፎችን በብርቱ ያነጋገረ፣ በብዙ ያመራመረ ርእሰ ጉዳይ ነው።
የሆነስ ሆነና ሰው የተባለውን ፍጥረት መንፈሳዊው አስተምህሮው እንዴት ይረዳዋል፤ እንዴትስ ይገልጸዋል? የሚለውን የሐሳብ ፈትል ይዘን- ሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጥበብ ይልቅ የዳነበትን መለኮታዊ ጥበብ፤ ዘላለማዊ ፍቅር የበለጠበትን እውነታ በጥቂቱ እንቃኝ።
በአጭር ቃል፤ ሰው በመንፈሳዊውም ሆነ በሳይንሱ እውቀት ትንታኔ የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ፣ የፍጥረት አለቃ፣ ምርጥ/የተመረጠ ነው። ይህ ሰው የተባለ ፍጥረት ደግሞ በፈጣሪው እጅግ የተወደደ፣ የተከበረ ነው።
በቤተክርስቲያናችን ሠለስቱ ምዕት/፫፻፲፰ ሊቃውንት በቅዳሴያቸው ስለዚህ በፈጣሪው ስለተወደደው ሰው ስለተባለው ፍጥረት ሲያመሰጥሩ፤
“አዳምን/ሰውን እግዚአብሔር ከምድር አፈር በውብ እጆቹ አበጃጀው፤ የሕይወትንም እስትንፋስ እፍ አለበት። ሰውን እጅግ ወደደው፤ ሳመውም።” ይሉናል።
እንዲሁም እንግሊዛዊው ተወዳጅ ደራሲ ሼክስፒር “ሐምሌት” በተባለው ድንቅ የተውኔት ሥራው፤
“ሰው ከመላእክት ይልቅ እጅግ የከበረ፣ የአምላኩ የፍቅር ማኅተም የታተመበት እንዴት ውብ፣ ድንቅ ፍጥረት ነው፣ ሐሳቡስ ምንኛ ምጡቅ፣ ረቂቅ ነው…፤” በማለት ይገልጸዋል።
ልበ-አምላክ የተባለ ንጉሥ ዳዊት፤
“ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።” እንዲል።
(መዝሙረ ዳዊት ፻፴፱፤፲፬)።
ይህ ውብና ድንቅ የሆነ የተፈጠረ፤ በአምላኩ እጅጉን የተወደደ ፍጥረት ሰው በበደሉና በኃጢአቱ ምክንያት ከክብሩ በተዋረደና ለሞት ፍርሃት ለሲኦል ባርነት ተላልፎ በተሰጠ ጊዜ እንኳን አምላክ ፈጽሞ አልተወውም። ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆኖ ሊያድነው፣ ሊቤዠው ወደደ፤ ፈቀደ እንጂ።
እናም፤ አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ!! ይህን ከሰው አእምሮ በላይ የሆነና ከማስተዋልም የሚያልፍ እግዚአብሔር ለሰው የገለጸውን ፍቅር የሰማይ ሰራዊት፣ መላእክቱ፤
“ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ ሃሌሉያ!” ሲሉ ይህን ፍቅር እጅጉን ተደነቁበት፣ በአዲስ ዜማ፣ በአዲስ ሰማያዊ ቅኔም አወደሱት። ሰማይ ሰማያት፣ ምድርና ሞላዋም በዚህ ታላቅ ፍ-ቅ-ር እጅጉን ተደመሙ፤ ተደነቁ።
ይህን አምላክ ሰው፣ ሰው አምላክ የሆነበትን የማዳን ፍቅሩን፤ ጥበቡን ኦርቶዶክሳውያን የሥነ-መለኮት ምሁራንና የቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት እንዲህ ሲሉ በአድናቆት ይገልጹታል፤
“እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ሰውን ያዳነበት ጥበቡ፤ ፍቅሩ ይበልጣል፣ እጅጉንም ይልቃል።”
ተወዳጆች ሆይ፥ ይህን ምሥጢር በደንብ ለመረዳት ከቤተልሔም የከብቶች ግርግም እስከ ቀራኒዮ ጎልጎታ ድረስ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን በመውደዱ የፈጸመውን የፍቅሩን፣ የማዳኑን ሥራ መመልከት፣ ማስተዋል ያስፈልገናል።
እግዚአብሔር ወልድ ከ፺፱ኙ በጎች ይልቅ የባዘነውን፣ የጠፋውን አንዱ በግ/የሰው ልጅ በዛው እንደጠፋ ይቀር ዘንድ ፍቅሩ አላስቻለውምና ሰውን ሊፈልገው ከሰማየ ሰማያት ወረደ። የቤተክርስቲያናችን ሊቅ፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በቅዳሴው፤
“ኃያል እግዚአብሔርን ፍቅር ከመንበሩ ሳበው እስከሞትም አደረሰው፤” በማለት የተወደድንበት አምላካዊ ፍቅር፤ የዳንበት መለኮታዊ ጥበብ ምን ያህል ዘላለማዊ፣ ሕያው፣ ታላቅ፣ ዕፁብ እና ድንቅ… መሆኑን ያስረዳናል።
በእውነትም፤ እግዚአብሔር እኛን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ እኛን የወደደበት ፍቅር፣ ሰውን ያዳነበት ጥበብ ይበልጣል፣ ይደንቃልም!!
በገዳማውያ አባቶቻችን ዘንድ እግዚአብሔር ሰውን የወደደበትን ይህን አባታዊ ፍቅር፤ የዳንበትን አምላካዊ ጥበብ የሚያዘክር፤ የሚያወድስ አንድ ታሪክ አለ።
አንድ መነኩሴ የሆኑ መናኝ አባት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ያስተማረውን፤ “አባታችን ሆይ!” የሚለውን ጸሎት ዘወትር በአንቃድዎ ሕሊና፣ በሰቂለ-ልቦና በተመስጦ ሆነው ይጸልያሉ።
ታዲያ እኚህ መነኮስ አባት ለረጅም ደቂቃዎች አባታችን ሆይ፣ አባታችን ሆይ፣ አባታችን ሆይ በማለት ሲጸልዩ የሰማቸው አንድ ወጣኒ መናኝ/መነኩሴ፤
“አባታችን ጸሎቱን ይዝለቁት እንጂ ‘አባታችን ሆይ!’ ብቻ እያሉ ቀሩ እኮ፤” ሲል በመገረም ይጠይቃቸዋል።
እኚህ አባትም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤
“ልጄ እንደ እኔ ያለውን ደካማና ኃጢአተኛ ባሪያውን የወደደበትን፣ ያፈቀረበትን የአምላኬን፣ የጌታዬን- የጌትነቱን ቸርነት፣ የአባትነት ፍቅሩን፤ እኛን ያዳነበትን አምላካዊ ጥበቡን መቼ ተናግሬው፣ መቼ አሰላስዬው በቅቶኝ ወደሌላው ልዝለቅ ብለህ ነው?!”
“ልጄ ይህ ከአእምሮ፣ ከስማተዋልም በላይ የሚያልፍ ሰውን ሁሉ የወደደበት የአምላኬ፣ የአባቴ ፍቅሩ፤ የዳንበት ታላቂቱ ጥበቡ ሁሌም አዲስ ሆኖ ቢመስጠኝ፣ ቢያስገርመኝ ይኸው ዘወትር አባታችን ሆይ፣ አባታችን ሆይ፣ አባታችን ሆይ ስለው እውላለኹ።”
“ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር እኛን የወደደበት ፍቅር፣ እኛን የሰው ልጆችን ያዳነበት ጥበብ ልክም፣ ወደርም የለውምና በዚህ ፍቅር ውስጥ ሆኜ ይህን ታላቅ፣ ቸር አባት ሁሌም ያለ ማቋረጥ አባታችን ሆይ፤ አባታችን ሆይ፤ አባታችን ሆይ እለዋለኹ …።” ሲሉ መለሱለት።
ታላቁ መጽሐፍ፤
“ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።” እንዲል።
(የዮሐንስ ወንጌል ፲፭፤፲፫)።
እናም በዚህች ታላቅ እለት እኛም እንደ አባቶቻችን እንዲህ እንላለን፣ እንዲህ እንመሰክራለን፤
“ከተፈጠርንበት ጥበብ ይልቅ የዳንበት ጥበብ ይበልጣል!!”
መልካም የስቅለትና የትንሣኤ በዓል!!
ሰላም!!
በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)፤





















