ዝምታና ፍራቻ የመቃብር መቆፈሪያ አካፋና ዶማ ናቸው !!

(አሥራደው ከካናዳ)

መንደርደሪያ :

1. « Les tyrans ne sont grands que parce que nous sommes à genoux ». Pierre Victurnien Vergniaud, célèbre avocat, homme politique et révolutionnaire français

« አምባ ገነኖች አደገኛ ወይም ትልቅ የሚሆኑት፤ እኛው እራሳችን ስለተንበረከክንላቸው ነው » ፔር ቪክቱሬን ቨርኝኦድ

2. « The silence of the good people is more dangerous than the brutality of the bad people » Martin Luther King, Jr.

« መልካም አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ዝምታ፤ ከመጥፎ ሰዎች ጭካኔ የባሰ አደገኛ ነው » ማርትቲን ሉተር ኪንግ

3. L’ignorance mène à la peur, la peur mène à la haine la haine conduit à la violence …. Voilà l’équation » Ibn Rochd

« የዕውቀት ማነስ ወደ ፍርሃት ይመራል፤ ፍርሃት ወደ ጥላቻ ይመራል፤ ጥላቻ የጭካኔ ዕልቂትን ያስከትላል…  ይኸው ነው ቀመሩ! » ኢብን ሮችድ

4. There is no flag large enough to cover the shame of killing innocent people.” – Howard Zinn

« የንጹሃን ሰዎች ግድያን ወይም ዕልቂት ሃፍረት፤ ሊሸፍን የሚችል ትልቅ ሰንደቅ ዓላማ አይኖርም » ሃዋርድ ዚን

5. “Old men declare war. But it is the youth that must fight and die.” – Herbert C. Hoover « በዕድሜ የገፋ ሰዎች ጦርነትን ያውጃሉ፤ በጦርነቱ እየተማገዱ የሚያልቁት ግን የአገሪቱ ወጣት ዜጎች ናቸው » ሄርበርት ሲ. ሁቨር

መግቢያ :

ዓብይ አህመድ አሊ፤ ወደፊት ለሚያደርገው የጦርነት እልቂት፤ እውቅና ለማግኘት፤ በኢትዮጵያ ምርጫ እንዲደረግ እያስገደደ ይገኛል:: በዚህ ምርጫ ኢትዮጵያውያን፤ ዓብይ አህመድ አሊ: ህዝብን በቦምብ፤ በድሮንና በጦር ጀቶች፤ ለመፍጀት የሚያስችለውን ፍቃድ፤ በይስሙላ ምርጫ ተብዬ ዕውቅና ለማግኘትና፤ የተመኘውን የንጉሠ ነገሥትነት ሥልጣን አረጋግጦ፤ አጤ በጉልበቱ በመሆን፤ የኢትዮጵያን ህዝብ፤ በጎሣና በዘር ከፋፍሎ እያባላ፤ ለረጅም ዘመን እግሩን አንፈራጦ ለመግዛት ወስኗል ::

በፊት በህወሃት(ወያኔ)፤ አሁን ደግሞ በኦህዴድ፤ የብልጽግና ተብዬ ዘመን፤ እንደ ዕንቁላል የፈለፈሏቸውን፤ ተለጣፊ የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞችና፤ አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ « ተወዳዳሪ » የሚል የዳቦ ስም ያወጣላቸውን ጨምሮ፤ ምርጫ የሚሉትን ተውኔት ወይም የትያትር ድራማ፤ ለመሥራት፤ እየተሯሯጡ ይገኛል ::

የተለጣፊ የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞች ምኞት፤ የዓብይ አህመድ አሊ ተቀላቢ ሆኖ፤ በፓርላማ ተብዬው ውስጥ ተጎልተው፤ ለዓብይ አህመድ ዘረኛና ጎሠኛ ዲስኩር፤ ለማጨብጨብና ለማንቀላፋት ብቻ ሲሆን ::

በተቃራኒው፤ አብይ አህመድ እንድታጅቡኝ እንጂ እንድትቃወሙኝ አልፈልግም ብሎ « ተወዳዳሪ ፓርቲዎች » የሚል ስም ያወጣላቸው፤ የጨረባ ምርጫ ተብዬውን ለማጀብ ብቻ የተጠሩ መሆናቸውን በሚገባ እያወቁት፤ በዚህ ምርጫ በመሳተፍ፤ ለዓብይ አህመድ፤ የዘርና የጎሣ፤ አምባ ገነን ሥርዓት ዕውቅና በመስጠት፤ የኢትዮጵያን ህዝብ፤ የመከራ፤ የመፈናቀል፤ የርሃብ፤ የጦርነት ዕልቂትና ስደትን፤ ለማራዘም ካልሆነ በቀር፤ ምንም ፋይዳ እንደለሌው እያወቁ በምርጫው ለመሳተፍ ወስነዋል::

 በበኩሌ፤ ዓብይ አህመድ ካወጣላቸው « ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች » ከሚል የዳቦ ስም በመውጣት፤ ተቃዋሚ የፖለትካ ፓርቲዎች : ሊሆኑ ይገባል እላቸዋለሁ ::

በሳይንሳዊ ፍልስፍና ምርምርና ጥናት ላይ በተመሠረተ፤ እራሳቸው በነደፉት የፖለቲካ ፍልስፍና በመመራት፤ ተወዳድሮ የህዝብን ይሁንታ፤ በአብላጫ ድምጽ አግኝተው በማሸነፍ፤ ሥልጣን በመረከብ፤ የነደፉትን የፖለቲካ ፕሮግራም፤ በተግባር በመተርጎም፤ አገርን ማስተዳደር የሚችሉ መሆናቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል ::

እራሳቸው በነደፉትና፤ በሥራ ላይ ለማዋል ባቀዱት የፖለቲካ ፍልስፍና መሠረት:

የሥነ መንግሥቱን፤ የምጣኔ ሃብቱን፤ የፍትህ ሥርዓቱን፤ የማህበረሰቡን፤ የትምህርቱን፤ የሠላምና ጸጥታ ማስከበሩን፤ የጦር ሃይሉን ሚናና ተግባር፤ የዲፕሎማሲውን፤ አገራዊ፤ ክፍለ ዓለማዊና፤ ዓለም አቀፋዊ፤ ግንኙነቶችና ሌሎች ያልጠቀስኳቸውን፤ ጉዳዮች ጨምሮ፤ በሃላፊነት ተቀብለው አገርን ማስተዳደር መቻል ይኖርባቸዋል ::

ያ ካልሆነ፤ « ተወዳዳሪ » የሚል ቡልኮ ተከናንበው፤ አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን፤ ዘረኛና በጎሣ ከፋፋይ የሆነን ገዢ  ቡድን፤ መልሶ በሥልጣን ላይ ለማስቀመጥ ከሆነ፤ ፍሬ ከርስኪ ከመሆኑም በላይ፤ የህዝብን መከራና ስቃይ ለማራዘም ተባባሪ በመሆናቸው፤ በታሪክ ፊት ተጠያቂ ከመሆን አያመልጡም ::

ምሳሌ :

በማራቶን የሩጫ ውድድር፤ ከተለያዩ አገራት፤ የተለያየ ዕድሜና ቁመና ያላቸው የሩጫ ተወዳዳሪዎች፤ የማራቶን እሩጫ፤ የሚባለውን የ42 ኪሎ ሜትር ርቀት፤ ተወዳድሮ ለማሸነፍ፤ ተመዝገበው ይሮጣሉ እንበል ::

ዓላማቸው ወይም የሩጫቸው የመጨረሻው ግብ፤ የ42 ኪሎ ሜትሩን ርቀት፤ ከሌላው ተወዳዳሪ  ፈጥኖ በመጨረስ፤ አሸናፊ መሆን ብቻ እንጂ፤

ከሌላው ተወዳዳሪ የተለየ፤ አዲስ የፈጠራም ይሁን የድርጊት ለውጥ አያመጡም :: ምክንያቱም የውድድሩ ዓላማና ግቡ በአዘጋጆቹ ቀድሞ ተወስኖ አልቋል ::

ዓብይ አህመድ « ተወዳዳሪ ፓርቲዎች » የሚል የዳቦ ስም ያወጣላቸው፤ የፖለቲካ ስብስቦች፤ ሩጫውን ህጋዊ ለማስመሰል ፤አብረውት የሚሮጡ፤ የዓብይ አህመድ የዘርና የጎሣ ፖለቲካ አጃቢዎች ሲሆኑ፤ በመጨረሻም፤ የዓብይ አህመድን አምባ ገነናዊ አገዛዝ፤ ፈርመው ከማጽደቅ ውጪ፤ ሌላ የሚያደርጉት ምንም ዓይነት ምርጫ የላቸውም ::

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ድርጅቶች ከሆኑ ግን፤ ከዓብይ አህመድ የዘርና የጎሣ ፖለቲካ ውጪ፤ የራሳቸው የሆነ፤ ሥልጣን ለመያዝ የሚያስችላቸው፤ የፖለቲካ ፕሮግራምና የተግባር መርህ ሊኖራቸው ይገባል ::

ስማቸውም ብይ ህመድን የዘርና የጎሣ ፖለቲካ የሚቃወሙ፤ የራሳቸው የሆነ የሚመሩበትየፖለቲካ ፕሮግራም፤ አቅታጫና ግብ ያላቸው እንጂ ፤ ተመሳሳይ የሆነ የዘርና የጎሣ ሥርዓት፤ መልሶ ለማስፈን፤ የሚወዳደሩ ሊሆኑ አይገባም ::

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ድርጅቶች ከሆኑ ግን፤ ከዓብይ አህመድ የዘርና የጎሣ ፖለቲካ ውጪ፤ እራሳቸው ሥልጣን ለመያዝ የሚያስችላቸው፤ የፖለቲካ መርህና ግብ ያላቸው በመሆን፤ የህዝብ ባለ አደራነታቸውን በማረጋገጥ፤ ህዝቡን ከአምባ ገነን፤ የዓብይ አህመድ የዘርና የጎሣ ከፋፍለህ ግዛው ሥርዓ በማላቀቅ፤ የነፃነት አየርን እንዲተነፍስ ሊያደርጉት ይገባል :: ከበረቱም ይችላሉ !!

ተቃዋሚ የፖለትካ ፓርቲዎች ወይም ድርጅቶች

ተቃዋሚ የፖለትካ ፓርቲ ወይም ድርጅት ማለት፤ አሁን በሥልጣን ላይ ካለው : የገዢው ፓርቲ ወይም ድርጀት፤ የተለየና በተሻለ መልኩ፤ የአገርንና የህዝብን ደህንነትና ጥቅም ለማስከበር፤ የራሱ የሆነ የፖለቲካ ንድፈ ሃሳብና፤ የተግባር ዕቅድና ግብ ይዞ፤ በመወዳረር ለሥልጣን በመብቃት፤ አገር ለማስተዳደር ወይም ለመምራት የሥልጣን በትሩን መያዝ መቻል ሲሆን ::

ለዚህም :

ሥነ መንግሥቱን  (ፖለቲካውን)
ምጣኔ ሃብቱን  (ኢኮኖሜውን )
ህግና የህግ ሥርዓቱን : የህግ ሥርዓቱ የህጎች ሁሉ የበላይ ሆኖ፤ ከማንኛውም የፖለትካ ድርጅት ተጽዕኖ ነፃ በሆነ መልኩ፤ ማንኛውም ዜጋ፤ መንግሥትን ጨምሮ፤ ከህግ በላይ የማይሆንበት፤ ዳኞች በነፃነት የሚፈርዱበት፤ ዜጎች በህግ ፊት ቀርበው፤ እኩል የሚዳኙበት አካል እንዲሆን ማድረግ ::
የህዝብ መገኛና ማዕከላትን :  ቴሌቪዥን፤ ሬዲዮ፤ መጽሄቶች፤ ጋዜጦች……ወዘተ. ከህዝብ ኪስ በተሰበሰበ ግብር፤ የሚተዳደሩ እንደመሆናቸው መጠን፤ የህዝብ ዓይንና ጆሮ በመሆን፤ የመንግሥትን የሥልጣን ገደብ የሚቆጣጠሩ :: መንግሥታዊ ጥቃትና ጥፋት ሲፈጸም፤ ህዝብ እንዲያውቀው የሚያደርጉ :: መንግሥታዊ ምዝበራ ሲፈጸም የሚያጋልጡ :: የፍርድ ሂደቱ ሲዛባ፤ የሚያስጠነቅቁ :: የአምባ ገነኖች የጥላቻ ዲስኩር ማሰራጫ ከመሆን የሚቆጠቡ፤……ወዘተ. መሆን አለባቸው::
ዘወትር የንሥር ዓይን የተካኑ፤ የውሻ አፍንጫ የታደሉና፤ የህዝብን ትኩሳትና ቅዝቃዜ የሚለኩ የሙቀት መለኪያ መሣርያ በመሆን፤ ለአገር ልዕልና : ለህዝብ ጥቅምና ደህንነት ዘብ በመቆም : ሠላም፤ ነፃነት፤ እኩልነትና ፤ ወንማማችነትን እንዲከበርና እንዲጠነክር የራሳቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው::
ማህረሰባዊውን :

ለዕድገትና ለሥልጣኔ፤ ህዝዊ ትስስርና ትብብርን በማጠናከር ፤ ያለፈ ታሪካችንን ሳይፍቁ፤ ሳይፈገፍጉና፤ ሳይደልዙ፤ ከሚያለያዩን ጉዳዮች ይልቅ፤ በሚያቀራርቡ ዕሴቶቻን ላይ በማተኮር፤ ባለፈ ታሪካችን ቂም በመቋጠር፤ ለበቀል ምክንያት በመፍጠር፤ ሁልጊዜ አፍርሶ ገንቢ ከመሆን ይልቅ፤ ባለው ላይ በቀጣይነት በመገንባት: የወደፊት አቅጣጫን የሚያመላክት፤ የአብሮነት እቅድ በመንደፍ፤ ሰዎች በሠላምና በፍቅር፤ እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደፊት እንዲገሰግሱ ማድረግ ::

የትምህርት ፍልስፍናውን :

ቀደም ብሎ በህወሃት (ወያኔ) ቀጥሎም በኦህዴድ የዓብይ የብልጽግና ፖለትካ የሚተገበረውን፤ ትውልድ ገዳይና አገር አምካኝ የሆነ ፤የትምህርት ሥርዓት በማስወገድ፤ ነባራዊ ሁኔታዎችን በሚገባ በማጤን፤ በሳይንሳዊ ፍልስፍና ምርምርና ጥናት ላይ ተመርኩዞ፤ የወደፊት የትምህርት አቅጣጫ በመንደፍ፤ አዲሱ ትውልድ ከመዋዕለ ህፃናት ጀምሮ፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፤ በምህንድስና፤ በኢንጂነሪ፤ በህክምና በእስፖርትና የአካል ብቃት፤…. ወዘተ. ተኮትኩቶ የሚያድግባቸውን የትምህርት መስኮች በመተለም: በሥራ ላይ ማዋል ::

– መዋዕለ ሕፃናት

– የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ት/ ቤቶች

– የሙያና የቴክኒክ ማሰልጠኛ ማዕከላት

– የመምህራን ማሰልጠኛ ማዕከላት

– የተለያቱ ዩኒቨርሲቲዎችን

– የሳይንስና የቴክኖሎጂ ማዕከላት

– የእስፖርትና የአካል ብቃት ማሰልጠኛ ማዕከላት

– የእርሻና የአዝርዕት ምርምርና ጥናት ማዕከላት

– የቋንቋ፤ የባህልና ሙዚቃ ጥናት ማዕከላት

_ የዓለም አቀፍ ግንኙነት : የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጥናት ተቋማት

– የህክምና ሳይንስ ምርምር ዩኒቨርስቲዎችና ተጓዳኝ ተቋማት

– የምርምርና የፈጠራ ችሎታ ማዳበሪያ ጥናት ማዕከላት…….ወዘተ.

በማስፋፋት፤ አሁን ያለውና መጪው ትውልድ፤ የዕውቀት ባለቤት ሆኖ፤ ሥራ አፍቃሪና ሥራ ፈጣሪ ትውልድ ሆኖእንዲያድግ በማድረግ፤ ከግለኝነት ይልቅ አብሮ የማደግ ባህልን በማስቀደም፤ እራሱንና አገሩን እንዲያሳድግ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ::

ሥራና ሥራ አጥነትን : መንግሥታዊና፤ የግል የሥራ መስኮችን እንዲስፋፉ በማድረግ፤ የሥራ ፈጠራን በማሳደግ፤ የወጣቱን የሥራ አጥነት ችግር፤ በተቻለ ፍጥነት በመቀነስ፤ የስደትን ምንጮች ማድረቅና ፤ አገራችን ኢትዮጵያ የወጣት ዜጎቿ  ዕውቀት፤ ሃይልና ጉልበት ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ ::

መኖርያ ቤትና ኗሪ : ያለ መኖሪያ ቤት፤ የአገር ባለቤትነት ስለማይኖር፤ ዜጎች እንዳቅማቸው የሚኖሩበት ቤት፤ አቅማቸው የሚፈቅድ ሠርተው፤ የማይችሉ ተከረይተው እንዲኖሩ የሚያስችል፤ የአጭር፤ የመካከለኛና የሩቅ ጊዜ ዕቅድ አዘጋጅቶ፤ በሥራ ላይ በማዋል፤ የመኖሪያ ቤትን ችግር፤ ማስወገድ ባይቻል እንኳ፤ በተቻለ አቅም ለማቃለል መሞከር ::

ንግድና ነጋዴው: በንቅዘት (በሙስና) የተጨማለቁ የገዢው ክፍል ካድሬዎች፤ የነጋዴውን ጉሮሮ ከማነቅ እንዲቆጠቡ፤ ህግና ሥርዓት በማስፈን፤ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ :: ነጋዴውም ወገኖቹን እንዳይበዘብዝ፤ የህግ ጠለላና ቁጥጥር እየተደረገ፤ ነግዶ እራሱንና ወገኖቹን እንዲያግዝ ማድረግ ::

ንቅዘት ወይም ሙስና፤ በነጮቹ አጠራር ( Corraption)አገራችንን ጨምሮ አብዛኞቹ  የአፍሪካ አገራት የተዘፈቁበት አስከፊ ምግባር በመሆኑ፤ በአገራችን ቀደም ብሎ በህወሃት (በወያኔና) አሁን ደግሞ በዓብይ አህመድ የአምባ ገነን አገዛዝ ዘመን : እንደ ወረርሽኝ በሽታ የተስፋፋ በመሆኑ፤ የህግ የበላይነትን በማስፈን : ሠርቆ በላ፤ ነጥቆ በላና፤ አውርቶ በላ፤ ሙጃዎችን በመንቀል፤ የሞራልና የሥነ መግባር ባህላችንን መልሶ ማደስ ::  

ሠራተኛውና ሥራ : ሠራተኛው የሚያገኘው ደሞዝ (የደም ወዝ)፤ የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም የሚያስችል፤ ልጆቹን ለመመገብለማልበስና ለማስተማር፤ የሚያበቃ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር፤ እንደ አቅሙ ጥሪት በመቋጠር፤ ከቤት ኪራይ በመውጣት፤ ቤት ለመሥራት ወይም ለመግዛት፤ የሚያስችል ዕድል እንዲኖረው ማድረግ ::  

ገበሬዎችና ግብርና : ገበሬዎችን የመሬት ባለቤት፤ ያደረጋቸውን የትግል ትሩፋት ነጥቆ፤ መሬትን ለድንበር ዘለል ከበርቴና፤ ለአረብ አገር ፔትሮ ዶላር ነገሥታት፤ መቸብቸቡን :በአፋጣኝ በማቆም: ገበሬው አርሶ፤ እራሱንና ቤተሰቦቹን የሚያስተዳድርበት፤ ፍትሃዊ የመሬት ክፍፍል ማድረግ ::

ዲፕሎማሲውን :  

*አገራዊ፤  

*ክፍለ ዓለማዊና

*የዓለም አቀፋዊነትን፤ ፍልስፍናና ፈር በመከተል፤ የአገር ድንበር፤ ጥቅምና ክብር አስከብሮ፤ የሌሎችንም ጥቅምና ክብር ሳይጋፉ፤ ተከባብሮ የመኖር የጥንት ባህላችንን መልሶ ማስቀጠል  :: ….ወዘተ.

ማሳረጊያ :

« የመጀመሪያው የወዶ ገብነት፤ ወይም የፈቃደኛ አገልጋይነት ምንጭ ፤ ልምድ ሲሆን » ሁለተኛው የፈቃደኛ አገልጋይነት ምክንያ ደነግሞ፤ « ከውልደታችን ጀምሮ፤ በመላው የዕድገታችን ሂደት ውስጥ፤ በወዶ ገብነት፤ ወይም በፈቃደኛ አገልጋይነት፤ እየተገራን በማደግ ፤ ፈቃደኛ አገልጋይነትን ወደን በመቀበል፤ ተላምደንና ተላብሰነው በመቆየታችን ነው ::

እንግዲህ በውዴታ፤ እራሳችንን ዝቅ አድርገን በማቅረብ፤ የአምባ ገነን ፈቃደኛ አገልጋዮች በመሆን፤ ዓብይ አህመድን የመሰለ፤ የአይምሮ ሰንካላ፤ የአስተሳሰ ደካማና፤ በዝቅተኝነት በሽታ ዘወትር የሚሰቃይ፤ የሞራል ብቃቱ ከዜሮ በታች  የሆነ ሰው፤ የኢትዮጵያን ህዝብ እየሰደበ፤ እያመናጨቀ፤ እየናቀና እያዋረደ፤ ልግዛችሁ ሲለን እንዴት እሺ በማለት ወዶ ገብ፤ ወይም ፈቃደኛ አገልጋዮች እንሆናለን ??!!

አምባ ገነኑ ዓብይ አህመድ፤ እንደፈለገ እንዲፈነጭብን ያደረግነው፤ እኛው በገዛ እጃችን፤ ከኢትዮጵያዊነት ማማችን ወርደን ዝቅ በማለት፤ « ወዶ ገብ ወይም ፈቃደኛ አገልጋዮች » በመሆናችን ስለሆነ፤ ከዚህ ውርደታችን ለመገላገል ያለን አማራጭ፤ በአንድላይ በመነሳት፤ እምቢ !ለአምባገነን አገልጋይና አሽከሮች አንሆንም በማለት፤ ለጋራ ነፃነታችን ዝምታና ፍራቻን በማስወገድ : ለመብታችንበአንድንነት ዘብ በመቆም፤ ስንታገል ብቻ ነው ::

ጎበዝ ! ዝምታና ፍራቻ የመቃብር መቆፈሪያ አካፋና ዶማ በመሆናቸው :ሞት አይታደጉንም !!

ከአንዴም ሁለቴ የጣሊያንን ወራሪ ጦር መክተው፤ ድል የነሱ፤ የጀግኖች የልጅ ልጆች ሆነን፤ እንዴት የዓብይ አህመድ፤ ወዶ ገብ ወይም ፈቃደኛ አገልጋዮች እንሆናለን ??!!

ለተሻለ አስተዳደራዊ ሥርዓት ብለን፤ የቀ.ኃ.ሥ. ፊውዳላዊ የዘውድ አገዛዝን፤ ታግለን ያስወገድን ዜጎች፤ እንዴት የዓብይ አህመድ፤ ወዶ ገብ ወይም ፈቃደኛ አገልጋዮች እንሆናለን ??!!

የደርግ ወታደራዊ አገዛዝን፤ ገፍትረን የጣልን፤ የፍትህ ታጋዮች፤ እንዴት የዓብይ አህመድ፤ ወዶ ገብ ወይም ፈቃደኛ አገልጋዮች እንሆናለን ??!!

የህወሃት (ወያኔን) የጥላቻ፤ የዘርና የጎሣ ልፋይ ቡድን በህዝባዊ ትግል ያስወገድን ሰዎች፤ እንዴት የዓብይ አህመድ፤ ወዶ ገብ ወይም ፈቃደኛ አገልጋዮች እንሆናለን ??!!

የገዛ አገሩን ለአሜሪካ ሲሰልል የነበረ፤ ዘረኛና ጎሠኛ ለሆነ፤ በውሸትና በክህደት ለተዘፈቀ፤ የአገራችንን ሃብት እየዘረፈና እያዘረፈ ወገኖቻችንን ለሚያስርብ፤ ባሰፈነው የንቅዘት (የሙስና) ሥርዓት ህዝብ የሚያሰቃይ፤ ህዝብን እያፈናቀለ ለአረብ አገራት ቱጃሮች መሬታቸውን ለሚሸጥ፤ ጦርነት አውጆ: ት/ ቤት: ሆስፒታል፤ መንገዶችና ድልድዮችን የሚያፈርስ፤ የገበሬዎች ቤትና ዕህል የሚያቃቅጥል፤ ወገኖቻችንን በድሮን፤ በታንክና በጀት እየደበደበ በደም እጆቹን ብቻ ሳይሆን፤ አከላቱን እየታጠበ ለሚገኝ፤ ዓብይ አህመድ ለሚባል አምባ ገነን ፤ እንዴት « ወዶ ገብ ወይም ፈቃደኛ አገልጋዮች » እንሆናለን ??!!

ቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም.     (25/05/2026)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.