ኦሕ-Dead ምን ላይ ነው…? በአዲስ አበባ አይግረማችሁ!

ሙሉዓለም ገብረመድህን

ክፍል ፩

ኦሕዴድ ብልጽግና ወደሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ፣ ቡድኑ በተግባራዊ እንቅስቃሴዎቹ ስምንት የወረራ፣ የጥቃት፣ የውድመት፣ የቀውስ፣ ዓመታትን እንዳሳለፈ የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡ በእነዚህ የጥፋት እንቅስቃሴዎቹ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ስጋት ሆኗል፡፡

አገር የማዳን ዓላማ የነበረውን የጥቅምት 2013 ጦርነት ከዐይን ጥቅሻ በፈጠነ ክህደቱ ወደቀጠናዊ ቀውስ የቀየረበትን ሁኔታ እያሰቡ ይከተሉኝ…

የኦሕዴድን ኢምፓየር ለመገንባት በዕቅድና በዓላማ በአማራ ሕዝብ ላይ ጦርነት ከመክፈት ጀምሮ ሕግና ፖሊሲን፤ ተቋማትንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ኃይሎችን ጭምር ለዓላማው ማስፈጸሚያ ሲጠቀም ታይቷል፡፡

ባለፉት ስምንት ዓመታት ዐቢይ አሕመድ መራሹ አገዛዝ ስጋትነቱን በግልጽ ካሳየባቸው ጉዳዮች አንደኛው፤ ‹ከሁሉም አጎራባች ክልሎች የመሬት ቅርምትና ግዛት ማስፋፋትን› ዓላማ አድርጎ መስራቱ ነው፡፡

አራት ኪሎን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ከኦሮሞ ክልል ጋር ድንበር የሚጋሩ ሁሉንም ክልሎችና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጭምር የመጨፍለቅ ዓላማውን ለማሳካት ቀውስን፣ ማጭበርበርንና ማደናገርን ማስፈጸሚያው አድርጎት ታይቷል፡፡

መሬት ላይ ባሉ ጥሬ ሀቆች የተነሳ፦ ሌሎች የማንነት ቡድኖች የኦሮሞን ፖለቲካ በስጋት እያዩት ነው። ዛሬ መላው የኢትዮጵያ ብሄረሰብ በኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች እምነት የሌላቸው ሆነዋል።

አማራው ላይ ተጀምሮ አማራው ላይ የሚያበቃ ጭፍጨፋም ሆነ ማፈናቀል እንደሌለ ብዙዎቹ ከገባቸው ቆይቷል።

የኦሕዴድ ተስፋፊነት፣ ዋጭና ሰልቃጭ ፖለቲካ ለህዳጣኑ የህልውና አደጋ እንደሆነ በየራሳቸው ሁኔታ ተረድተዋል።

ጥቂት ማሳያዎች 

❶. ሶማሌ ራሱን ሲከላከል ነው የኖረው። ገና ድሬዳዋ እና ሞያሌ ላይ ቀጣይ ፍልሚያዎች አሉበት። ከአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የወሰን መጋራቱ ውስጥ ከ400 በላይ ቀበሌዎች የወሰን ውዝግብ ረመጥ አለ።

❷. ሲዳማ፣ በምስራቅ ሲዳማ በኩል ከጉጅ የሚነሳ ወራሪ ኃይል ከ10 በላይ ቀበሌ በጉልበት ተይዞበታል። ሐዋሳ ዳር ዐይኑን ተክሎ ‘Bishaan Gurraacha’ በሚል የዳቦ ሥም ከተማ ሰይሟል። የሐዋሳ “ፍቅር ሀይቅ”ን “ጥቁር ውሃ” በሚል ስያሜ ለመንጠቅ ጊዜ ነው የሚጠብቅለት። ሲዳማ ሻሸመኔ የታሪካዊ ግዛቴ አካል ነበረች ብሎ ሲተዝት፣ ኦህዴድ አሻግሮ ሐዋሳን ሊነጥቀው በሩ ላይ ቆሟል።

❸. አፋር በነሱ ተስፋፊነት ተፈትኗል። አርብቶ አደሩ ጥይት የቀለብ ያህል የሚሸምተው ተጨባጩ ስጋት ስለገባው ነው። በተለይም አዋሽ መስመር ዋናው የወረራ ስጋት ቀጠና ሆኖበታል።

❹. ጋምቤላ በኢንቨስትመንት ሥም የመሬት ወረራ እየተፈፀመበት ነው። ኢሬቻ ጭምር ተከብሮበታል። ጋምቤላዎች ቢጨንቃቸው የባሮ ወንዝ አዞዎቻቸውን ስያሜ በኦሮሞ ፖለቲከኞች ስም እስከመጥራት ደርሰዋል። ህጻናትን እያደነ የሚበላውን አዞ ‘ሽመልስ’ የሚል ስያሜ ያወጡት፣ ጋምቤላዎች የደረሱበትን የስጋት ስሜት ከነሱ ውጭ የሚረዳው ያለ አይመስልም።

❺ ቤኒሻንጉል በ”ነፍጠኛ መጣብህ” ማስፈራሪያ ካማሽንና አሶሳ ዞኖቹን እየተነጠቀ ነው። ካማሽን በወረራ፣ አሶሳን በቢሮክራሲ ሲያስረክብ፣ መተከልን በኢንቨስትመንት ሥም ተነጥቋል። መደበኛው ታጣቂ ጭምር ዘልቆ ገብቶበታል።

ከአምስት የተሰነጠቀው ደቡብ

➽ ከፋና ሸክቾ በመኖርና ባለመኖር መካከል ስጋት እንደዋጣቸው አሉ።

➽ጉራጌ በሶዶ አስታኮ፣ ሰባት ቤትን ለመሰነጣጠቅ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። ወለኔም በለው ክስታኔ የባልካናይዜሽኑ ፕሮጀክት አካል ናቸው። ሱቅ አብቅሎ የሚያድረው አንዱ ጉራጌ በዘየ ልዩነት የልዩነት ማንነት ሲፈለፈልበት እያደረ ነው።

➽ የነጭ ሳር ፓርክ ውስጥ የሰፈረውና ቀጣይ ወረራን ያለመው ኦነጋዊ ኃይል ለኮሬና ቡርጅ ቀርቶ ለወላይታ፣ ጋሞ፣ ደራሼ ፈተና ሆኖ በመታየት ላይ ነው።

➽ ሐደሬ በፍጹማዊ የመዋጥ ስጋት ውስጥ ነው። በከተሜነት የፈካ ማንነቱ በተረኛው ኃይል መዋቅራዊ ጥቅለላ መደብዘዝ ውስጥ ገብቷል።

መቼም የአማራውን ጉዳይ መዘርዘር አይጠበቅብኝም።

አንድ የማይታለፍ ነገር፦

አማራው ላይ ከሚፈጽሙበት የዘር ማጽዳት ወንጀል በተጨማሪ በክልሉ ያሉትን ልዩ ዞኖች በቀጣይ ራሳቸውን ችለው “ክልል” እንዲሆኑ የካርታ ዝግጅትን ጨምሮ የሪሶርስ፣ የፖለቲካ፣ የፕሮፖጋንዳ፣ … ድጋፎች እየተመቻቹላቸው ነው። (ገራሚው ተረክ ድጋፉ ከወያኔም ከኦሕዴድም በየራሳቸው ኔትወርክ የሚሰጥ መሆኑ ነው)

ከዚህ ቀደም የአመጽና የቀውስ መነሻ በማድረግ አማራውን በውስጥ ጉዳዮቹ እንወጥረዋለን ብለው አቅደው የሰሩበት ሲሆን፤ ፋኖ ወደለየለት ትጥቅ ትግል ከገባ ወዲህ ደግሞ ልዩ ዞኖቹ ክልሉን ከውስጥ እንዲያፈርሱ በልዩ ሁኔታ ድጋፍ እየተቸራቸው ነው።

“እምብርታችን ነች” የሚሏትን አዲስ አበባን ከበባ ውስጥ ስለማስገባታቸው “እርግጠኞች” ከሆኑ በኋላ አሁን ደግሞ እንዋጣት እያሉ ነው።

ይህ መዋቅራዊ ወረራ ከትጥቅ ትግሉ ጋር በከተሞች አመጽ ያዋለደ ቀን፣ መዳናዋን የከበባትን የከተማ አናርኪስት ፈትተን እንለቀዋለን ነው-ዕቅዳቸው። ዐቢይ “መንግሥታችን ተነካ ብለው … ” ሲል የገለፃቸው እነዚህን አናርኪስቶች ነው።

ሆኖም ግን እነዚህ ሰዎች ያልገባቸው ወይንም አምነው መቀበል ያልፈለጉት ነገር የምስራቁና የምዕራቡ ኦሮሞ በአንድ የመቆም የታሪክ ኑባሬ የሌለው መሆኑን ነው።

በዚህ ምክንያት የኦሮሞ ፖለቲካ ኢትዮጵያን የመዋጥ ጉዞው ቅድሚያ ራሳቸውን ሊበላቸው እንደሚችል አልገባቸውም/ማመን አልፈለጉም።

በየአቅጣጫው ፈተው የለቀቁት ኃይል አንድ ላይ መቆም የማይችል ተጠፋፊ ኃይል ነው። እውነታው በየትኛውም ሁኔታ ‘ኦሮሞ ኦሮሞን እንደዚህ ዘመን ገድሎት የማያውቅ’ መሆኑ ነው።

በሌላ በኩል የፖለቲካ አስኳል (core group) አደረጃጀታቸው ሃይማኖታዊ ቅርፅ እየያዘ መጥቷል። ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በ conventional war ደረጃ ሊፈጸም የማይችሉ ጥፋቶች እርስ በርሳቸው ሳይቀር ተፈጽሟል።

የሸዋ ኦሮሞ እየተለየ በሃይማኖታዊ ማንነቱ ተገድሏል። (ማረድ : አስከሬን መቆራረጥ ማቃጠል …የተፈጸመባቸው) አርሲ-ዶዶላ፣ ባሌ-ሮቤ፣ ሐረርጌ:.. በዲሞግራፊ ደረጃ [ከሃይማኖት አንፃር] ምን አይነት የሥነ-ሕዝብ አሰፋፈር እንዳላቸው ያጤኗል።

በመስመር መሀል ማንበብ ለሚችል ሰው፥ ከመቼውም ጊዜ በላይ የኦሮሞ ፖለቲካ ተከፋፍሏል። የወለጋን ሕዝብ ጭራቅ አድርጎ የማሳሉ የነ ሽመልስ አብዲሳ ሴራ የወለጋ ልሂቃን የማይሽር ቅራኔ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። ዛሬ ወለጋ ውስጥ “ፋኖ ሰላም ስጠኝ” የሚል ኦሮሞ ቢፈጠር ሁኔታው የኦህዴድ ውጤት ነው።

በሌላ በኩል፣ በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ አንጀኞችም ሆኑ ዋናው ኃይል ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ማህበራዊ መሠረት ፍለጋ እየኳተኑ ይገኛል።

ያ-ሁሉ የሰው ልጅ እርድ የአሰላለፉ ምልክቶች ናቸው። ጊዜ ጠብቀው ማዕከላዊ መንግሥት የተዳከመ ሲመስላቸው ብቅ የሚሉ ሰለፊ ጀሃዲስቶች መፈልፈያቸው እዚያው መንደር ነው።

ይሄ ፍፁም አደጋ ያዘለ አሰላለፍ መጀመሪያ የኦሮሞ ፖለቲካን ይበላዋል፤ እየበላውም ነው። ቀጥሎ ኢትዮጵያን ብሎም ምስራቅ አፍሪቃን በይበልጥ የአፍሪካ ቀንድን የሽብር ቀጣና ያደርገዋል።

እናም፦ ኦሕዴድ፣ ከቤተ-ኢትዮጵያ ይልቅ፣ ኦሮሙማ መደበቂያ ምሽጉ መዋያና ማደሪያው መሆኑ ሊያከትም ግድ ይላል!

ትላንት ያልነበረውን ጥያቄ አሁን እየወለደ፤ ዛሬ የሌለውን ጥያቄ ለነገ እያማጠ ከመሄድ መቆም የሚችለው ከአራት ኪሎ ሲነቀል ብቻ ነው።

ትላንት ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም እንፈልጋለን፤ ዛሬ ‘አዲስ አበባን ልዋጥ’ ፣ … ይህ አባዜው ካልቆመ ኢትዮጵያ ወደ ፍርሰት ቀጣናውንም ወደ ሽብር ማዕከልነት ይከተዋል፡፡

በአዲስ አበባ አይግረማችሁ በኪሳቸው ይዘውት የሚዞሩት ካርታ ከኬንያ ቀይባሕር የሚደርስ ነው…

ክፍል ፪ ይቀጥላል …

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.