>
5:14 pm - Tuesday April 30, 8086

የሃብታሙ ስቃይ እና የህዝቡ እንቅልፍ [ሄኖክ የሺጥላ]

Habtamu Ayalew Andinetሃብታሙ ሲታመም ፥ ሃብታሙ ሲሰቃይ ፥ ሃብታሙ ለህዝብ ሲሞት ፥ ህዝብ የሃብታሙን ስቃይ ከቦ ተኝቷል ። እንግሊዞች ቴዎድሮስን መቅደላ ላይ ሲከቡ ፥ እንግሊዞችን ከቦ ሁኔታውን ያይ የነበረው ህዝብ ትዝ አለኝ። እዚህ ጋ እንግሊዞችን መርቶ ቴዎድሮስን ስላስከበበው ህዝብ ዛሬም ማውራት አልፈልግም!
ተመስገን ደሳለኝን አስሮ የሚያሰቃየው ፥ የቀስቶን ጥፍር ነቅሎ በህመም ጣር ውስጥ የጣለው ፥ አንዷለመን የከሰሰው ፥ ወይም እስክንድር ላይ የፈረደው ፍርድ ቤት አይደለም እኔን የሚገርመኝ ፥ እኔን የሚገርመኝ እስር ቤቱን ፥ ፍርድ ቤቱን ፥ ሃብታሙ የተኛበትን ሆስፒታሉን ከቦ የተኛው ህዝብ እንጂ! እኔን የሚገርመኘን ተቀጥረው ህዝባቸውን የሚቀጠቅጡት ወታደሮች አይደሉም ፥ ወይም በዘረኝነት ልክፍት ነብሳቸው ደም ጎርሶ ህፃናትን የሚገሉት ልማታዊ ሰይጣኖች አደሉም ፥ እኔን እጅግ የሚገርመኝ ለነዚህ ሰዎች ተቀጥሮ ስራ ለመስራት ጠዋት ፊቱን ታጥቦ ከቤቱ የሚወጣው ህዝብ ፥ እኔን የሚደንቀኝ እየተናነቀው የወያኔ አባል ሆኖ አድርግ የሚሉትን የሚያደርገው ኢ-ወያኔ ነኝ ባዩ ወያኔ ህዝብ !
Habtamu Ayalew- Andinet Partyአዎ ሃብታሙ አያሌው ውጭ ወጥቶ የመታከም ፍቃዱን ሲከለከል ፥ ሌሎች የመስራትም ሆነ መንግስታዊ ተግባራትን የመከወን እምቢታ ውስጥ ለመግባት ፍቃደኛ አይደሉም ። የሚገርመው 90 ሚሊዮን ህዝብ ጥቂት ጠባቦችን ከቦ ከውስጥ ወደ ውጭ መሞትን መቀበሉ ነው። የሚገርመው የሃብታሙ መታመም አይደለም ፥ የሚገርመው የሃብታሙን መታመም እየተናገሩ ሀብታሙን መሆን ግን የማይፈልጉት ሚሊዮኖች ምንነት እንጂ! ሃብታሙ በጠና ታሟል ፥ የታመመው ግን የህዝብን ፥ የሃገርን ፥ የትውልድን ነቀርሳ ነቅሎ ሊጥል ሲታገል ነው ። ሃብታሙን ያመመው የኛ በሽታ ነው!
ዛሬ ዜናው ሃብታሙ ኮማ ውስጥ እንደሆነ ይናገራል ። ግን ሃብታሙ ኮማ ውስጥ የገባው ዛሬ ነው እንዴ ? በዚህ ህዝብ ዝምታ ፥ በስርአቱ ርካሽነት ፥ በሃገርም ሞት ፥ ነብሱ አዝኖ ፥ መንፈሱ ተረብሾ ፥ ጮኾ ፥ ተናግሮ ፥ ታስሮ ፥ተገርፎ ፥ ተሰቃይቶ ፥ ሽንት ላይ ተኝቶ ፥ ሰውነቱ በቅማል ተበልቶ ፥ ሰዋዊ ክብሩን ለማስመለስ ፥ ሰዋዊ ምቾቱን አጥቶ ፥ ራሱን ሆኖ ፥ ሳይንበረከክ ከታሰረበት ሲወጣ ፥ ያ የሞተለት ፥ የታሰረለት ፥ የቆሰለለት ፥ ሽንት ላይ የተኛለት ፥ በወታደር ጫማ የተረገጠለት ህዝብ ፥ ምንም እንዳልተፈጠረ ፋሲካን ሊያከብር በግ ሊገዛ ሲጋፋ ፥ ለመለስ ደረት ሲመታ ፥ ምርጫ( በግድም ቢሆን) ሊመርጥ ተሰልፎ ሲወጣ ሲያይ ፥ ሃብታሙ ኮማ ውስጥ የገባው ያኔ ነው ! ሃብታሙ እኮ በስርአቱ ሳይሆን ስርአቱን ከቦ በደል በሚሞቀው ህዝብ ውሳኔ ኮማ ውስጥ ከገባ ቆየ!

Filed in: Amharic