>

ዶ/ር አብይ አህመድ ለህዝብ እና ለመንግስት ብቸኛው አማራጭ!! (ሄኖክ ተሾመ - ቦስተን)

 “እውነት የማውቀው አብይ ጠቅላይ ሚንስትር ሊሆን ነው??” እኔ
“የምነግርህ 90% ያለቀ ጉዳይ ነው።” ወዳጄ …………
ታዲያ ለምን ብዬ ዝም ልበል???
ደስታዬንስ ለምን ልገድበው????

እድል ገጥሞኝ ያወቅሁት አብይ የላቀ ስብእናን የተላበሰ ግለሰብ ነው። እጅግ በጣም ጥልቅ እና አንደበተ ርዕቱ ነው። ለጠባብ አስተሳሰብ የማይመች ምናበ ሰፊ ነው። የአብይን ቢሮ ለተመለከተ ሰው አስተሳሰቡን ለማወቅ ግዜ አይወስድበትም። እኔ እንኳን በሆነ ብሔር ፓርቲ ውስጥ ታቅፎ እንደሚሰራ ለማወቅ ግዜ ወስዶብኛል። እንዴትስ ማወቅ እችል ነበር? አብይ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ዝቅ ብሎ ስለ ጎሳ እና መንደር ሲያወራ ለማዳመጥ ማሰብ ከዝንብ ማር የመጠበቅ ያህል እሩቅ ነው። ይባስ ብሎ ያላየንውን እና ያልዳሰስነውን እሩቁን የህዋ ሳይንስ ሲገልፀው አፍ ያስከፍታል። የአብይ ህልም ትልቅ ነው ፣ ቁጭት የሚያንገበግበው የእውነት አዋቂና ምሁር ነው። ከአንደበቱም “ሁሉ እያለን ለምን ተራብን? ፣ ለምን ደሀ ሆንን? ፣ ለምን ድንቁርና ነገሰብን? ፣ ……” የሚሉትን አድምጦ ምክንያቶቹን እና መፍትሄውን ሲገልፀው ያደመጠ ሰው ፣ ምን አለ ኢትዮጵያን እንደዚህ ያለ ሰው ቢመራት? ካላለ ፣ የሌላ ሀገር ዜጋ ነው ማለት ነው። በልቡ ለራሱ ሀገር ተመኝቶታል። ታዲያ እኔም ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ ለራሴ ተመኝቸው ነበር እንዲህ ብዬ ” ምናለ የትምህርት ሚንስትር ሀላፊ ቢሆን?” ኤዲያ! የምኞት ትንሽ ከተመኙ አይቀር በደንብ ነበር እንጂ ፣ ብቻ ያሁኑ ይሁን እንጂ ሁለተኛ ድንክ አልመኝም። አይለመደኝም። በደንብ እመኛለሁ። ደሞ ለምኞት!! እናም አሁን ምኞቴ ሞልቶ ሊፈስ ቀርቧል መሠለኝ ፣ ፈጣሪ በእፍኜ የጠየኩትን በቁና ሊሰፍርልኝ ግዜው ደርሶ እንደሁ እንጃ ልቤ ድው ፣ ድው ይላል። እንዲህ የተመኘሁትን ፣ ያወዳደስኩትን ፣ የማውቀውን ፣ የነካሁትን ያየሁትን አብይን ለምን ብዬ የጎሳ አጉሊ መነፅር አድርጌ አየዋለሁ?? አላደርገውም። የትላንትና ህልሜን ሲነጋ አስፈተዋለሁ እንጂ ፣ ሲፈታ ምን ይሆን? ብዬ ፈርቼው ዛሬን ሳልተኛ አላድርም። ባይሆን ህልሜ ሲፈታ መጥፎ እንዳይሆን ፈጣሪዬን እማፀናለሁ። ስለዚህ ዛሬ በክልል እና በጎሳ በታጠረ የፓለቲካ ግቢ ውስጥ ያለው አብይ ፣ በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ወለል ብሎ በተከፈተለት የፊት ለፊት በር እንዲወጣ እና ለት በለት የሚያስጨንቀኝን ፣ በነገዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን በምናቤ የማየውን ፣ ሁሉ እንደጉም አብንኖ እንዲያጠፋልኝ እጠብቀዋለሁ።
ለምን ብቸኛው አማራጭ??
ለህዝ ፦ ከተቃዋሚዎች አንዱ ወደ ስልጣን የሚመጣ ከሆነ የመምጫ መንገዱ ደም እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው። አብይ በደም ሳነዘፈቅ ለመሻገር ድልድይ መሆን ይችላል። የህዝብ ደም የለውጥ መንገድ መሆኑ ይብቃን!!
ለመንግስት፦ ሰላምን አስፍኖ ነገሮችን ለማሰብ እና ለማስተካከል ካሰበ ፣ ከአብይ የተሻለ ተናግሮ የሚያሳምን ፣ በህዝብ አመኔታ እና ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችል ከፓርቲው ውስጥ ማግኘት የሚችል አይመስለኝም። አይችልምም።

Filed in: Amharic