>

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከመቀሌ ወደ ቃሊቲ ተዘዋውረዋል ተባለ (ዘመድኩን በቀለ)

~ በነገራችን ላይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መቐለ ነበር እንዴ የታሰሩት ?

~ መቐለ ~ ባዶሽድሽተ ~ ቃሊቲ ~ ሎንዶን

~ እንጊሊዝ መረጃ ሰጠች ፣ መረጃውን እነ አጅሬ ሻአቢያ አጎልብተው ከህወሓት ጋር መከሩበት ፣ አላሙዲን ከየመኑ ሟች የቀድሞ ፕሬዘዳንት ሳላህ ጋር ተደራደረ ፣ ገንዘብ ለየመን ተሰጠ ፣ የግል አውሮፕላን ደግሞ ለህወሓት አላሙዲን አዘጋጀ ፣ አቀረበም ፣ የእግዜር በጉ አቶ አንዳርጋቸው ሀገር ሰላም ብሎ ሸከተፍ ፣ ሸከተፍ እያለ አስመራ ገብቶ ወደ እንጊሊዝ ለመብረር የኤርትራ አውሮፕላንን ተሳፍሮ ወደ የመን መንገድ ጀመረ ።የመን ሰንዓም ደረሰ ፣ ሰንዓላይ የህወሓት ወታደሮች የአላሙዲንን አውሮፕላን ይዘው ይጠብቃሉ ። የየመን ወታደሮች አንዳርጋቸውን አስወርደው ለህወሓት አሳልፈው ሰጡ ። ይኸው ነው ። ይላሉ አንዳንድ ሐሜተኞች ።

~ ይኽ ሁሉ ሲሆን ግን እግዚአብሔር ደግሞ ከሰማይ ሆኖ ሁሉንም ሴራና ግፍ ያይ ይመለከትም ነበር ። ይኽ በሆነ በጥቂት ዓመታት ውስጥ እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት ወጥታ ውጥንቅጥ ውስጥ ወደቀች ። ኤርትራም ያው መከራ ላይ ናት ። የየመኑ ፕሬዘዳንት እንደ ጋዳፊ እዚያው የመን ውስጥ ተገድለው አስከሬናቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ክብር ተነፍጎ ተጎተተ ። ህውሓትም አንዳርጋቸው ከተያዘ ዕለት ጀምሮ ጠላት አብዝታ ታማሚ ሆነች ። አልጋም ላይ ዋለች ። የአሁኑ ጣዕረ ሞት ከብዙ አይነት ህመም የመጣ ቢሆንም ያባባሰባት ግን ከአንዳርጋቸው መያዝ በኋላ ነው ይባላል ።

~ ጋሽ አላሙዲም በሰሩት ግፍ እግዚአብሔር ቀን ጠብቆ ብድራቱን ከፈላቸው ። ያስረገዟትን የትግራዋይዋን አርቲስት ደመ ግቡዋን ማኅደር አሰፋን ሳይንከባከቡ ፣ በቅርቡ የሚወለደውንም ልጃቸውንም ሳያዩ ወደ ወኅኒ ተጣሉ ። ሀብት ንብረታቸውም ታገደ ። ይኸው ይባስ ብለው አሁንማ አዲስ አበባዎችም ሰሞኑን ሼኩ ሳይሞቱ በህይወት እያሉ እስከዛሬ ድረስ አጥረው የሙጃ ማብቀያ አድርገው ለሰንበት የሚሆን ቄጤማ እያመረቱ የሚሸጡበትን አጥረው ያስቀመጧቸውን መሬቶቻቸውን ሰሞኑን ወረሱባቸው አሉ ። ድሮስ ደሀን ማን ይደዋል? ማንም ።

ለማንኛውም የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚንስቴር የነበሩት አቶ ቶኒ ብሌይር ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ገብተው የቀድሞውን ተጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን በይፋ ፣ የህወሓት ባለሥልጣናትን ደግሞ በዝግ ሳሎን አግኝተው በብዙ ተወያዩ ፤ በውይይቱም ወቅት ሁለቱ ተወያዮቹ ስለምንና በምን ጉዳይ እንደተነጋገሩ ግን እሱ መድኃኔዓለም ይወቅ ።

~ በቄሮ እና ፋኖ ትግል ፤ የአማሪካዋ #HR128ም ተጨምራ ተአምር በሚያሰኝ መልኩ ባልታሰበ እና ባልተጠበቀ ሁኔታ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኅሊና እስረኞችን አገዛዙ ሳይወድ በግድ አንድ በአንድ ፣ ጥቂት በጥቂትም በችርቻሮም ጭምር ቁጥ ቁጥ ቢልም በመፈታት ላይ መሆናቸውንም እያየን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው ።

~ በዶር መረራ ጉዲና የተጀመረው የመፈታት ዜና በእነ እስክንድር ነጋ ፣ አንዱዓለም አራጌ ፣ አበበ ቀስቶ ፣ የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴና አቶ በቀለ ገርባን በመፍታት ቀጠለና ፤ በመቀጠልም የወልቃይት ኮሚቴዎችን በመፍታት በተለይም ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን እና ንግሥት ይርጋን በመፍታት በትንሹም ቢሆን እያስደሰቱን ቀጠሉ ።

~ አሁንም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የኅሊና እስረኞች ባሉበት ሀገር አስከ አሁን የተፈቱት በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ሳይሆኑ ሚድያው የሚያውቃቸው ዜጎች ብቻ ናቸውም ተብሏል።

~ እነ ዳንኤል ብርሃነ የመሰሉ የአገዛዙ የሥጋ ዘመዶች እንደልባቸው መከላከያውንም ሆነ የክልል ፕሬዝዳንቶችን ከፍ ዝቅ አድርገው በፌስቡክ እንደልብ በሚሳደቡበትና ዝንባቸው ከላያቸው ላይ እሽሽ በማይባልባት ሀገር ፤ እነ ዮናታን ተስፋዬ የመሰሉ ብሔር አልባ ኢትዮጵያዊ ወጣት በፌስቡክ ገጹ የህዝቡን ትግል ስለደገፈ ብቻ 6 ዓመት እንዲፈረድበት ሆኗል ። ዮናታን እስከ አሁንም ድረስ አልተፈታም ።

~ አሁን ከሚጠበቁት ተፈቺዎች መካከል የዋልድባ አባቶችና ዮናታን ተስፋዬ ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌና ሌሎችም በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከማጎሪያው ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

~ ሰሞኑን በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢንግሊዝ ኤንባሲና የኢትዮጵያው መንግሥት በአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ ትንሽ ሙግት ቢጤ ላይ እንደሆኑ ውስጥ አዋቂዎች ሲያወሩ የተሰማውም በዚህ ሳምንት ነበር ። መንግሥት አንዳርጋቸውን እንደፈታሁት ወዲያው ወደ መኖሪያው ኢንግሊዝ ሳይውል ሳያድር ይሒድልኝ ሲል ፤ ኤምባሲው ደግሞ አይ ! እንደዚያማ አይደለም እኛ እንቀበለዋለን ፣ የጤና ምርመራም እናደርግለታለን ፣ ከዚያ በኋላ ነው የሚሔደው ብለው አቋም በመያዛቸው ሳይስማሙ በእንጥልጥል ቀርተዋልም ነው የሚሉት እነዚህ የውስጥ አዋቂ ምንጮች ።

~ ዶር ቴዎድሮስ አድኃኖም አንዳርጋቸውን በተመለከተ የታሰረበትን ሥፍራ ባይገልፁም አቶ አንዳርጋቸው በግሩም ሁኔታ እንደተያዙ ፣ እንዲያውም ላፕቶፕ ተሰጥቷቸው መጽሐፍ እየጻፉ እንደሆነ ፣ የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድንም እንዳስጎበኟቸውና በልማቱም አቶ አንዳርጋቸው እንደተደነቁና እንደተገረሙ ለአሜሪካ ድምጽ ሲናገሩም መደመጣቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ መሆኑም ይታወቃል ።

~ ረዘም ላለ ጊዜ አቶ አንዳርጋቸው የት እንደታሰሩ ሳይታወቅ ቆይቶ ዛሬ በዛሬው ዕለት በዕለ አቡነ አረጋዊ ታሳሪውን ከመቐለ አምጥተው ቃሊቲ ማስገባታቸው ተሰምቷል ። ቀጥለው ባሉት ቀናት ምንአልባትም አቶ አንዳርጋቸው በብሪቲሽ አየር መንገድ አውሮፕላን ተሳፍረው ለንደን አደባባይ ሳይታዩ አይቀርም ተብሎ ይጠበቃል።

~ ፍቱ ! ፍቱ ! ፍቱ ! በችርቻሮ ሳይሆን ታዲያ በጅምላ ፣ ነጠላ ዜማ ሳይሆን ሙሉ አልበሙን ልቀቁልን ።

Filed in: Amharic