>
5:13 pm - Wednesday April 19, 6856

ከዚህ አዙሪት መውጣት ግድ ይላል !!! (መሳይ መኮንን)

ሂሳቡ ቀላል ነው። ዶ/ር አብይ አህመድን የኦህዴድ ሊቀመንበር አድርጎ መሰየም። አቶ ለማ መገርሳ ምክትል ሊቀመንበር እንዲሆኑ ማድረግ። ቀጥሎ ዶ/ር አብይ ወደ ኢህአዲግ ሊቀመንበርነት ያመራሉ። አቶ ለማ እዚያው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሆነው ይቀጥላሉ። በመጨረሻም ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ። የኦህዴዶች ሂሳብ ይህ ነው። በ27 ዓመታት ውስጥ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ቦታ የተነፈገው ኦህዴድ ተረኛ ነኝ ብሎ ተነስቷል። ህወሀት ይቀበለዋል? ብአዴን እንዴት ያየዋል? ደኢህዴንስ?

ወታደራዊ መንግስት ስልጣኑን ተረክቧል። ሀገር የምትመራው በሳሞራ የኑስ ሆኗል። ሲቪሉ አስተዳደር ስለሀገሪቱ መግለጫ እንኳን የማይሰጥ፡ ሁለመናው በጄነራሎቹ የሚዘወር፡ የሚመራ እንዲሆን ተደርጓል። በአፍሪካ ታሪክ ደም ሳይፈስ በተካሄደው የመጀመሪያው መፈንቅለ መንግስት ህወሀት ከቀድሞ የበለጠ ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮታል። የይስሙላ ፌደራል ስርዓቱ ፈርሷል። ይህ አዋጅ ለ6 ወራት የሚዘልቅ ነው ተብሏል። ከእንግዲህ የህወሀት ህልውና በጄነራሎቹ መዳፍ ውስጥ በመሆኑ አዋጁ በ6ወራት የሚቆም አይደለም። ህወሀት በተጀመረው ህዝባዊ ትግል ተፈንቅሎ ካልተወገደ በቀር ጄነራሎቹ ስልጣኑን ለሲቪል አመራር ይሰጣሉ ለማለት ይከብዳል።

ህወሀቶች የዶ/ር አብይ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መምጣት ሊያሰጋቸው የሚችል አይደለም። ምርጫቸው ግን አይደለም። እንደሚሰማው የህወሀት የመጀመሪያ ምርጫ ከደኢህዴን ነው። አሁንም ደኢህዴን ፈረስ ሆኖ ቢጋልቡ ደስታቸው ወደር የለውም። ካልሆነም ከብአዴን አቶ ደመቀ መኮንን እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። ወዶ ገብ አገልጋይ የሆነው ደመቀ በህወሀት ደጋፊዎች ዘንድም የሚጠላ አይደለም። ከኦህዴድ ከሆነም ለህውሀት የማይጎረብጡ፡ የጎረሱትን ብቻ የሚተፉ ሰዎች አሉ። አቶ አባዱላና አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፡ ከሁለት አንዳቸው ቢሆኑ ለህወሀት አደጋ የለውም። ከሃይለማርያም ባልተናነሰ እንደፈረስ ሊጋልቧቸው እንደሚችሉ ህወሀቶች ያውቁበታል።

ደህንነቱና መከላከያውን እስከተቆጣጠሩ ድረስ ህወሀቶች ስልጣን አልባው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር ላይ ማንም ቢቀመጥ ማን ብዙም ላያስጨንቃቸው ይችላል። አሁን ደግሞ አስቸኳይ አዋጅ በተሰኘ የብዕር ስም በተካሄደው ሰላማዊ መፈንቅለ መንግስት የፈደራል ስርዓቱን አፍርሰው በጄነራሎቹ የሚመራ መንግስት አቋቁመዋል። በዚህ ወቅት ነው ኦህዴዶች ወንበሯ ትገባናለች፡ ጊዜው የእኛ ነው ብለው የተነሱት።

በእርግጥ ዶ/ር አብይ እንደአቶ ሃይለማርያ አፋሽ አጎንባሽ ላይሆኑ ይችላሉ። የጎረሱትን ብቻ የሚናገሩ እንደማይሆኑ መገመት አይከብድም። ለራሳቸው ክብር ያላቸው፡ ባርነትን የሚጠየፉ፡ ሰው ሆኖ መቆም የሚችሉ እንደሆኑ አያያዛቸው ይመሰክራል። ህወሀቶች ከኦሮሞ ህዝብ የመጣባቸውን ማዕበል የሚመክትላቸው ከሆነ ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ ይቀበሉታል። ደህንነቱ፡ መከላከያው፡ ኢኮኖሚው በእጃቸው ውስጥ እስክቆዩ ድረስ ቤተመንግስት የሚገባው ሰው ከየትም ቢመጣ ለጊዜው አይገፉትም። ኦህዴዶች አከባቢ የሚባለው ወንበሩን ከተቆጣጠርን በሂደት እውነተኛ ስልጣን እንዲሆን እናደርጋለን። ደህንነቱና መከላከያውን የሚያዝ የሚቆጣጠር ጠቅላይ ሚኒስትር ለማድረግ እንችላለን፡ ጊዜ ይሰጠን የሚል ነው። ይህ የሚሆነው በህወሀት መቃብር ላይ ብቻ ነው። የህወሀቶች ህልውና ህዝብ አይደለም። ቆመው የሚራመዱት ህዝባዊ ድጋፍ ይዘው እንዳልሆነ ያውቁታል። የሚተነፍሱት በወታደሩ ነው። ነፍሳቸው የቆየው በደህንነቱ ነው። እነሱን ያጡ ዕለት ጨዋታው ያበቃል።

ኦህዴዶች የሚያሰሉት ቀመር ቀላል ነው። እንደህወሀት ጄነራሎች በሴራ የተጎነጎነ፡ መሬት ላይ የወረደ ቀመር አይደለም። የህዝብ ድጋፍን ጉልበት ያደረገ፡ በቅንነት ላይ የቆመ የፖለቲካ ስሌት ይዘው ነው ብቅ ያሉት። በእርግጥ የህዝብ ድጋፍ ወሳኝ ነው። ግን ብቻውን በቂ አይደለም። ከ40ዓመታት በላይ የሴራ ፖለቲካ ደማቸው ውስጥ ሲንተከተክ የቆየ፡ በወረቀት ላይ ከሰፈረ ንድፈ ሀሳብ ይልቅ መሬት ላይ ወርዶ በተግባር በተፈተነ የፖለቲካ ውስልትና የተካኑትን ህወሀቶችን ከጨዋታው ለማስወጣት በእነሱ ቋንቋ መናገር፡ በሚገባቸው የሴራ ፖለቲካ መግጠም ጭምር የሚጠይቅ ውስብስብ ትግል እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል።

ዋናው ጥያቄ ይህ አይደለም። ይህ ሁሉ ግርግር ለኢትዮጵያ ህዝብ ምኑ ነው? ምን ይፈይድለታል? ዶ/ር አብይ ቢሆን ሲራጅ ፈርጌሳ፡ ደምቀም ይሁን ደብረጺዮን ምን ትርጉም አለው? ይህ ወሬ አየሩን ይዞታል። ሰማዩን ሞልቶታል። ስርነቀል ለውጥ ለተጠማው የኢትዮጵያ ህዝብ በኢህ አዴግ መንደር በተከፈተ የግለሰቦች የቦታ ሽሚያ ውድ ጊዜውን እንዲያጠፋ ወጥመድ የተዘጋጀለት ይመስላል። አከሌ ይሁን፡ እንትና ቢሆን የሚል ወሬ በአጀንዳ መልክ ቀርቦ ከዋናው ትግል የህዝቡን ትኩረት ለመውሰድ እየተሞከረ ነው። ኦህዴዶች ወንበሯን ብቻ አይተው፡ ጊዜ ከሰጣችሁን ደህንነቱንና መከላከያውን ጭምር እንረከባለን በምትል የማትመስል የተስፋ ቃል ህዝቡን ከትግል ስሜት እያስወጡት እንደሆነ መታዘብ ይቻላል። ኦህዴዶች ሊያውቁት የሚገባው ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሀት የሚባል ጸረ ኢትዮጵያ ቡድን በህይወት እያለ ለማንም የሚሰጠው ሽራፊ ጊዜ የለም።

እነለማና ዶ/ር አብይ ያገኙትን የህዝብ ድጋፍ የሚመነዝሩት የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ወንበር ከደኢህዴን በመንጠቅ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ሲያነሳም በጣም ከፍ አድርጎ ነው። ሲጥል ደግሞ አይጣል ነው። ከመሬት አርቆ መቅበርን ያውቅበታል። እነለማ ህወሀት እያለ ስልጣኑን በእጃችን ማስገባት እንችላለን የሚል ቅዠት ውስጥ ከገቡ በቶሎ መውጣት አለባቸው። ህዝብ የጀመረው ትግል ይህን ለኢትዮጵያ ጠንቅ የሆነውን ማፊያ ስርዓት ከነግሳንግሱ ለማስወገድ ነው። ከዚህ ያነሰ ትግል አለተጀመረም። ህወሀትን በሌላ ቅርጽና ይዘት ዳግም ሊያይ የሚፈቅድ አይደለም የኢትዮጵያ ህዝብ።

አዎን! ከዚህ አዙሪት መውጣት ግድ ይላል። ኦህዴዶች እንድናዳምቅላቸው ለፈለጉት ‘ዘመቻ ጠቃላይ ሚኒስትር ወንበር’ ትኩረት ልንነፍገው ይገባል። የአሜሪካው ኮንግረስማን እንዳሉት ለህወሀት ጨዋታው አብቅቷል። ታዋቂው እንግሊዛዊ ጸሀፊ ሰሞኑን እንደጻፉትም ህወሀት እያበቃለት ነው። ይህን ተገዝግዞ ያለቀለትን ስርዓት የሚጠጋግን፡ እስትንፋሱን የሚያራዝም ማንኛውም አይነት አካሄድ እድል ሊሰጠው አይገባም። ከኢትዮጵያ የሚበልጥ ምንም ነገር የለም። አቶ ለማ መገርሳ በአንድ ወቅት እንዳሉትም ”የእኛ ጉዳይ ከኢትዮጵያ አይበልጥም”።

Filed in: Amharic