>

መቼም እንድ ድንቁርና እንደልብ የሚያናግርና ድፍረት የሚሰጥ የእውቀት ጾመኝነት የለም ! ! !

 

አቻምየለህ ታምሩ

ኢትዮጵያ ውስጥ ካልተማረው ማይምነት የተማረም ማይምነት ይበዛል። ዶክተርና ፕሮፌሰር እየተባለ እነ ተስፋዬ ገብረዓብ ያሰራጩትን ፈጠራ በስፋት ያስተጋባል። ተስፋዬ ፈልስሞ እንካችሁ የሚለው ሸቀጥ «ምንጭህ ከምን?» ብሎ የሚጠይቅ ስለሌለ ሁሉም እንዳወረደው እየተቀበለ የተስፋዬን ፈጠራ እውቀት እያደረገው ይገኛል። ተስፋዬ የወያኔ ፕሮጀክቶች የሆኑትን «የቡርቃ ዝምታን» እና «ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድን» የጻፈው በዚህ መልክ በበሬ ወለደ ነበር። ለነገሩ ሳይመረምር የሚያስተጋባ ካድሬ የሆነ ዶክተርና ፕሮፌሰር ተቀባይ ስላለው ለምን ይጨነቃል።

ዛሬ ጧት አንዳንድ ወሬ ደጋሚዎች አብይ አህመድ የኦህዴድ ሊቀመንበር መሆኑን ተከትሎ ግዑዙ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተገፍቶ በለቀቀ ወንበር ላይ ሊቀመጥ ይችላል በሚል ስሌት ከመሬት ተነስተው «ኢትዮጵያ የኦሮሞ ጠቅላይ ሚንስትር ኖሯት አያውቅም» በማለት አብይ አህመድን የመጀመሪያው ኦሮሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር [ከሾሙት ማለቴ ነው] አድርገው ያወራሉ። ይገርማል! መቼም እንድ ድንቁርና እንደልብ የሚያናግርና ድፍረት የሚሰጥ የእውቀት ጾመኝነት የለም።

ኢትዮጵያ ከልጅ እያሱ ዘመን ጀምሮ እስከ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ድረስ፤ አልፎም በዘመነ ደርግ የአገዛዝ አመታት ሁሉ የኦሮሞ ተወላጆች የሆኑ ጠቅላይ ሚንስትሮች ነበሯት።

የመጀመሪያው የኦሮሞ ተወላጅ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ልጅ እያሱ እህታቸውን [ ስኂን ሚካኤል] አጋብተው ጠቅላይ ሚንስትር አድርገው የሾሟቸው ቢትወደድ ኃይለ ጊዮርጊስ ወልደ ሚካኤል ናቸው።

ሁለተኛው የኦሮሞ ተወላጅ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር የታላቁ ጀግና የራስ ጎበና ዳጨ የልጅ ልጅ ራስ አበባ አረጋይ ሲሆኑ ራስ አበበ አረጋይ ጠቅላይ ሚንስትር ቢትወደድ መኮነን እንዳልካቸው በ1947 ዓ. ም. ከሞቱ በኋላ ከ1947 እስከ 1953 ዓ.ም. ድረስ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው አገልግለዋል። በ1953 ዓ.ም. መንግሥቱ ንዋይ ስለገደላቸው የጀግናው አርበኛ ራስ አበባ አረጋይ የጠቅላይ ሚንስትርነት ቦታ በጊዜያዊነት በራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ ተይዞ ቆይቶ በኋላ ላይ በጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተ ወልድ ተተክተዋል። የትኛውም አውሮፓዊ ትምህርት ቤት ያልሄዱት ራስ አበበ አረጋይ ጠቅላይ ሚንስትር በነበሩበት ወቅት ስላሳዩት የተለየ የአመራር ብቃት የራስ አበበ ካቢኔ ሚንስትር የነበሩ ብዙ አጋሮቻቸው መስክረውላቸዋል።

ኢትዮጵያ በደርግ ዘመን መጨረሻ የነበሯት ሌላኛው የኦሮሞ ተወላጅ ጠቅላይ ሚንስትር የአምቦ ልጅው ተስፋዬ ዲንቃ ናቸው። ጠቅላይ ሚንስትር ተስፋዬ ዲንቃ ባለፈው አመት ከዚህ አለም በሞተ የተለዩ ሲሆን የሕይወት ዘመን ትውስታቸውን «Ethiopia During The Derg Years» በሚል በጻፉት ዳጎስ ያለ መጽሐፍ አስፍረዋል።

በተረፈ ሳይመረምሩ ሀሳብ የሌለበት ወሬ ይዘው «ኢትዮጵያ የኦሮሞ ጠቅላይ ሚንስትር ኖሯት አያውቁም » ለሚሉ ወሬ ደጋሚዎች «ከመጠምጠም መማር ይቅደም» ፤ «ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት» የሚለውን የአያቶቻችን ጥልቅ ምክር በመለገስ ልሰናበት!

Filed in: Amharic