>
6:36 pm - Friday October 22, 2021

የቲም ለማ ቤተ-መንግስት በር ላይ መድረስ፣ ተስፋችንና ስጋታችን (ዳንኤል ተፈራ)

ዕንደ ባለፉት ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያችን ፖለቲካ የጅምናስቲክ ስፖርተኛ የሆነበት ጊዜ የለም፡፡ ለ27 ዓመታት በጉልበት ሲጨፈልቅ የነበረው ስርዓት ጡንቻው በወጣቶች አመፅ የላላበት፣ የዛለበት ጊዜም ነበር፡፡

በነዚህ ሁለት ዓመታት ሌላው የፖለቲካ ክስተት የኦህዴድ ጥርስ ማብቀል ነው፡፡ ለአቅመ መናከስ መድረስ ቀላል አልነበረም፡፡ ኦህዴድ (አዲሱ ኦህዴድ ይላሉ እነ ደረጀ ገረፋ ቱሉ እነ ለማ የሚመሩትን) የአስፈፃሚነት ካባውን ቀዳዶ በመጣል እኔም የኢትዮጵያን ፖለቲካ በአዲስ መንገድ መውሰድ እችላለሁ በማለት በመለስ ራዕይ ላይ አመፀ፡፡ ኦህዴድ ወደ አራት ኪሎ የሚያደርገውን ጉዞ የጀመረው ህወሃት ቡጢ ሲሰነዝር እሱም እየሰነዘረ እና የታላቁ መሪ ራዕይ የሚባለውን ወረቀት ቀድዶ እየጣለ ነው፡፡

ይህንን የኦህዴድ ጉዞ ደግሞ ተስፋ በተሞሉ ቃላት እያሽሞነሞኑ ጀሮ የሚነጥቁ ትንታግ አመሮችንም ፈጥሯል፡፡ እነ ኦቦ ለማ፣ አዲሱ አረጋ እና ዶ/ር አብይ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ይሄ ቲም ክንዱን ያፈረጠመው በቄሮ ንቅናቄ ነው፡፡ ከዚያም ከፍ በማለት እነ ለማ የብአዴንን ድጋፍ እና የአማራውን ህዝብ ልብ የሚያገኙበትን አንዳንድ እርምጃዎች ወስደዋል፡፡ ከእምቦጭ አረም ነቀላ እስከ ፖለቲካ መደጋገፍ የደረሰ ነው፡፡

በዚያኛው ገፅ ብአዴንን ስንመለከተው ራሱን ከህወሃት የበላይነት ለማላቀቅ በኦህዴድ ላይ መንፈሳዊ ቅናት ሳያድርበት አልቀረም፡፡ ነገርግን በቲም መልክ የመደራጀት ዕድል ያገኘ አይመስለኝም፡፡ ገሚሶቹ የህወሃት ፍቅር ገና የወጣላቸው አይመስልም፡፡ ወይም መንበርከኩ ሳይጥማቸው አልቀረም፡፡ እንደ አለምነው መኮንን ያሉት ደግሞ የሚመሩትን ህዝብ በመስደብ አለቆቻቸውን ለማስደሰት ሞክረዋል፡፡ በዚያ ላይ አሮጌ ታጋይ የብአዴን ዝሆኖች ጥላ ገና አለቀቃቸውም፡፡ ቢሆንም ግን እነ ገዱና ንጉሱ የሚያደርጉትን አንገት ቀና የማድረግ ትግል ማድነቅ የተገባ ነው፡፡ ማጀገን ክፋት የለውም፡፡

ከላይ በስሱ እንዳወሳሁት ፖለቲካው ለ2 ዓመት በማይገመት ሁናቴ ሂዶ ሲያበቃ ኃይለማሪም ደሳለኝ ቤተ-መንግስቱን ተረከቡኝ አሉ፡፡ ደግ አደረጉ ብያለሁ፡፡ ቀጣዩ አነጋጋሪ አጀንዳም ማን ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል የሚለው ሆነ፡፡ ጥያቄውን ብዙዎቹ ማንሳታቸው ተገቢ ነው፡፡ አንዳንዴ የሀገር ዕጣ ፈንታ በመሪ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ አንዱ ወፈፌ ተቀምጦ አገር ሊያወፍፍ ይችላል፡፡

ኦህዴድ የጅማውን ሰው ዶ/ር አብይ አህመድን አቀረበ፡፡ በሳምንታት ውስጥ ይሰበሰባል ተብሎ የሚገመተው የኢህአዴግ ም/ቤት ከአራቱ የግንባሩ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት አንዱን ይሰይማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኃይለማርያም በቃኝ ካለ በሁዋላ ስለቀጣዩ የፖለቲካ ዕጣ ፈንታ ብዙ ሀሳብ ተሰነዘረ፡፡ የግለሰብ መለዋወጥ ሳይሆን የሚያስፈልገው የስርዓት ለውጥ ነው የሚሉ አሉ፡፡ እውነት ነው፡፡ ነገርግን የስርዓቱን ለውጥ በምን መስመር እናስኪደው የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ነው፡፡ የሽግግር መንግስት ይቋቋምና በዚህ ሀገር ዕጣ ፈንታ ላይ የሚያገባቸው ሁሉ ይምከሩ የሚሉም አሉ፡፡ እንደ እኔ የግል አስተያየት ግን ኢህአዴግም ቢሆኑ የለውጥ ሀይል እስከሆኑ ድረስ ለዶ/ር አብይ እድል ቢሰጠው ጥሩ ነው ባይ ነኝ፡፡ ለምን ይህንን አልኩ….. እቀጥላለሁ

አሁንም ስጋታችን ጠሚው ከኦህዴድም ሆነ ብአዴን የጭቆና አገዛዙ ጥቂት ማሻሻያዎችን አድርጎ ላለመቀጠሉ ምን ማስተማመኛ አለ የሚለው ነው፡፡ ይሄ ስጋት እንደቀላል የሚታይ ባይሆንም አሁን ህዝቡ የደረሰበትን መብቱን የመጠየቅ ሳሆን የመውሰድ ደረጃ ላይ ስለሆነ ማንም እንደፈለገ ቡጢ መሰንዘር አይችልም፡፡ ለዶ/ር አብ ዕድል ይሰጠው ስል እነዚህን ሰዎች በቅርብ ባላውቅም ለባለፉት ሁለት አመታት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ራዕይና ተስፋ አለን ስላሉ በተግባር መፈተሽ አለብን ከሚል መነሻ ነው፡፡ እነዶ/ር አብይ ጥያቄያችንን በሙሉ ይመልሳሉ የሚል የሞኝ ተስፋም የለኝም፡፡ ነገርግን ቢያንስ ወደ ለውጥ የሚወስደንን መቀለጃ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ላይ ተስፋ እጥልባቸዋለሁ፡፡ ነፃውን ፕሬስና የሲቪክ ተቋማትን የመስቀያ ገመድ ዘው አይመጡም ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከተቃዋሚዎች ጋር የሚደረገውን ውይይት ድንበር ተሻግረው ያስቀጥላሉ ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በምርጫ ከተሸነፉ ስልጣን ይለቃሉ ብየ ተስፋ አደርጋለሁ ወዘተረወፈ፡፡

ስለዚህ ለቲም ለማ ዕድል ይሰጠው እላለሁ፡፡ ዘላቂው መፍትሄ ግን ህዝቡ የጎበጠውን ለማቅናት የሚያደርገውን ትግል መቀጠል ነው፡፡ ምርጫውም ኮሮጆውም የህዝቡ ከሆነ ስጋት ሊኖር አይችልም፡፡ ይህንን ማሳካትም የሚመጣው ጠ/ሚ ፈተና ይሆናል፡፡

Filed in: Amharic