>

ዶ/ር ዐብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ የምመርጥበት አስር ምክንያቶች፤ (ውብሸት ሙላት)

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሥልጣን የመለቀቅ ጥያቄ ስላቀረቡ በቅርቡ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚመረጥ ይጠበቃል፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መመረጥን ያህል ፈታኝ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ በአንድ በኩል ብሔርን መሠረት ያደረገ ፍላጎት አለ፤ በሌላ በኩል የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ እና የአፍሪካ ቀንድ ፍላጎትና ሁኔታ ደግሞ ሌላው፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ የሚመረጠው ሰው ከመከላከያ ሠራዊቱና ከደኅንነት ተቋሙ አሁን ያለበት ሁኔታ እና ከእነዚህ ተቋማት ጋር ተባብሮ የመሥራት ነገር አለ፡፡ የባሰው ደግሞ፣የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቀ አንድን አዲስ የሚመረጥ ጠቅላይ ሚኒስትር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አገር እንዲመራ መሰየም ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ችሎታንም ብቃትንም በመደበኛ የአስተዳደር ብሒል እንጂ መደበኛ ባልሆነ የአሰቸኳይ ጊዜ ሕግ እንዲመራ መሰየም ፈተናውን ያበዛዋል፡፡

እነዚህና ሌሎች ችግሮች ቢኖሩም አሁን በአመራርነት ከምናውቃቸው የኢሕአዴግ ሹመኞች ውስጥ እና ኢሕአዴግ በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በሚከተሉት አስር ምክንያቶች ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ የግል ምርጫየ ነው፡፡ ምክንያቶቹ ጥናት ላይ የተመሠረቱ ሳይሆን ዶ/ር ዐቢይን በተመለከተ ባለኝ የሩቅም ቢሆን ግንዛቤና መረጃ ነው፡፡

1. የመሪነት ፍላጎት ያለው በመሆኑ፤

እሱን የሚያውቁት ሰዎች እንደነገሩኝ፣ከበፊት ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ፍላጎት እንደነበራቸው የግል የሚያውቁት ሰዎች ነግረውኛል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕልም ከነበረው የራሱ እቅዶች፣የለውጥ ፍላጎቶች፣ማሻሻያዎች ይኖሩታል ማለት ነው፡፡ መሪ የሚሆን ሰው የራሱ አሻራ ትቶ የሚያልፍ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የራሱ የመሪነት ሐሳብ ያለው ሰው ነው አገር መምራት ያለበት፡፡ እንደ ንግሥት ዘውዲቱ በድንገት መሪ ማድረግ ውጤቱ እንደ አቶ ኃይለማርያም ምንም የሚታወስ ለውጥ ሳይኖረው መውረድ ነው፡፡ ስለዚህ፣ዶ/ር ዐቢይ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆን እመርጣለሁ፡፡

2. መሪ ለሕገ መንግሥታዊነትና ለሕገ የበላይነት ቁርጠኛ መሆን ያለበት ስለመሆኑ፤

እስከዛሬ ከሠራባቸው መሥሪያ ቤቶች መረዳት እንደሚቻለው ተቋም መገንባትና ሥርዓት ማስያዝ ከሚወዷቸው ተግባራቸው ውስጥ ናቸው፡፡ ሥርዓት የሌለው፣የተዝረከረከ ነገር አይወዱም፡፡ ንባብ ይወዳሉ፡፡ በሥርዓትና በደንብ የመመራትም የመምራትም ጥብቅ ፍላጎት እንዳለቸው አስመስክረዋል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥታዊነትና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሚጠቅም ዝንባሌ ነው፡፡ በአገራችን የጠፋውን ሕገመንግስታዊነትና የሕግ የበላይነት የማስፈን ችግር ለመቅረፍ ይሠራሉ፤ ዝናባሌያቸውም ለዚሁ የሚያግዛቸው ነው ብዬ አስባለው፡፡ ስለሆነም፣ዶ/ር ዐቢይ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆን እመርጣለሁ፡፡

3. ቀጣዩ መሪ ማርክሲስታዊ ዝባዝንኬን በሳይንሳዊና ሕጋዊ አሠራር መለወጥ የሚጠበቅበት ስለመሆኑ፤

ላለፉት 27 ዓመታት በአገራችን ላይ የተንሰራፋው ፖለቲካዊ አመራር ከሕግና ከሳይንስ ይልቅ መያዣና መጨበጫ የሌለው ሶሻሊስታዊ የሆኑ የችግር አረዳድና የመፍትሔ አሠጣጥ ብቻ ናቸው፡፡ መንግሥት የሚመራበትም የሚመራበትም (ላልቶ ይነበብ) መርሕ የማይገመት፣ተለዋዋጭ ለቁጥጥር የማይመች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቦናፓርቲዝም፣ ጥገኛ ዝቅጠት፣ጠባብነት፣ትምክህተኛነት፣ኪራይ ሰብሳነት፣ጥልቅ ተሃድሶ፣….ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ አመራሩንም ሕዝቡን የሚያደናግሩ ናቸው፡፡ ወጥ አይደሉም፡፡ ተጠያቂነትም ለማስፈን አይመቹም፡፡

እነዚህን አሰልቺ እንቶፈንቶዎች ሳይንሳዊና ሕጋዊ ወደሆኑ አሠራር የመቀየር ችሎታ ይኖራቸዋል ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ፡፡ ለሳይንስ ትምህርት ካላቸው ቀረቤታና እስካሁንም እያሳዩት ካለው አሠራር ይህን ዓይነት እንቶ ፈንቷዊ አሠራር እንደሚለውጡ ስለማምን ዶ/ር ዐቢይ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ እመርጣለሁ፡፡

4. ቀጣዩ መሪ ከዚያ ትውልድ የተለዬ መሆን ያለበት ስለመሆኑ፤

ዶ/ር ዐቢይ ወጣት የሚባሉ/ጎልማሳ ናቸው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ የ1960ቹ ትውልድ አይደሉም፡፡ አሁን ካለው ሕዝብ ከ75 በመቶ በላይ ከ1960ቹ ትውልድ በኋላ የመጣ ነው፡፡ ዓለም በ1960ቹ ትውልድ በመረጡት የአመራር ሥልት መመራት ካቆመች ቆይታለች፡፡ በመሆኑም ለዘመናት የሰለቸንን አንድ ዓይነት የአመራር ስልት ይቀይሩታል የሚል እምነት ስላለኝ፣በራሱ ከዚያ ትውልድ የአመራር ዘይቤ መገላገልም ትልቅ ለውጥ በመሆኑ ዶ/ር ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ እመርጣለሁ፡፡

5. ቀጣዩ መሪ አንድነትን በማምጣት ረገድ ተጽእኖ ፈጣሪ መሆን ያለበት ስለመሆኑ፤

ከብሔር እንጻር የኦሮማና የአማራ ቅልቅል፣ ከሃይማኖት ደግሞ የአባታቸው፣የእናታቸው እና የእሳቸው የተለያዩ መሆናቸው እንዲሁም ከቋንቋ ችሎታም አንጻር ቢታይ ኦሮምኛ፣አማርኛና ትግርኛ መቻላቻው ትልቅ ኃብት ነው፡፡ እዚህ ላይ የልጅ ኢያሱን የብሔር እና የሃይማኖት ታሪክና ሁኔታን ያስታውሷል፡፡ የልጅ ኢያሱን በአብዝኋኛው ብሔርና በሙስሊሞችም ዘንድ የነበረውን ተቀባይነት ለማለት ነው፡፡ በተሻለ ሁኔታ አገርን አንድ አድርጎ ለመምራት እና ተቀባይነት ለማግኘት ብሎም ለአገር አንድነት ጥሩ የብሔርና የሃይማኖት ዳራ አላቸው ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም፣ዶ/ር ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ አመርጣለሁ፡፡

6. ቀጣዩ መሪ አገር ለመምራት የተሻለ ዕውቀትና ልምድ ቢኖረው ተመራጭ መሆኑ፤

ዶ/ር ዐቢይ የመከላከያ ሠራዊት አባል (ሌተናል ኮሌኔል ነበር)፣ብሔራዊ የደህንነትና የመረጃ መረብ መሥራች፣ሚኒስትር፣በክልል በተለያዩ ሃላፊነት ሠርተዋል፡፡ አንድ የመጀመሪያ ድግሪ፣ሦስት የማስተርስ ድግሪዎች እና የዶክትሬት ድግሪ አላቸው፡፡ የመከላከያ፣የሳይበር ደህንነት፣የሚኒስትርነት፣የክልል የቢሮ ኃላፊ ልምድ አላቸው፡፡ በትምህርት ዝግጁትም ብዙ ነገሮች መገንዘብ ያስችላቸዋል፡፡ በተለይ ዶክትሬት ድግሪያቸው ሰላምና ደኅንነት ላይ መሥራታቸው እንዲሁ ጠቃሚ ሃብት ነው፡፡

የአፍሪካ ቀንድን ጂኦ-ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ እና የደኅነነት ሁኔታ እንዲሁም አገራዊውን የደኅንነት ሁኔታና በተለይም አስቸጋሪ እየሆነ የመጣውን የሳይበር ደኅንነት ፈተና በተሻለ መንገድ መረዳት ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ በመሆኑም፣ዶ/ር ዐቢይ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ አመርጣለሁ፡፡

7. ቀጣዩ መሪ አገራዊ መግባባትን መፍጠር የሚችል መሆን እንዳለበት፤

ከብሔርና ከሃይማኖት ልዩነት ባለፈ የተለያዩ ሐሳብ ያላቸውን ግለሰቦችና ቡድኖችን ማራቅ፣ ማሳደድ፣ ማሰር፣ ማሸበር፣ ጠላት ማድረግ ወዘተ የአገራችን የተዘወተረ ልማድ ሆኗል፡፡ በተለይ ከ1966 በኋላ ወይ ወዳጅ ወይ ጠላት እንጂ ገለልተኛ የሚባልን ቡድን ማጥፋት ተለምዷል፡፡ በሐሳብ የተለዬን ሰው ማጥቃት ባህል ሆኗል፡፡ ለማ መገርሳና ቡድናቸው ይህንን ሰብረው አሳይተውናል፡፡ ዶ/ር ዐቢይም የዚሁ ቡድን አባል መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ እስካሁን ለአገራችን እንቅፋት የሆነውን የፖለቲካ አተያይና አመራር ሊያስቀሩ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ በመሆኑም፣ዶ/ር ዐቢይ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ እመርጣለሁ፡፡

8.እንደ መሪ ንግግር አዋቂና ተናጋሪ መሆን አስፈላጊነቱ፤

እስካሁን ባየነው ዶ/ር ዐቢይ የተዋጣላቸው ተናጋሪ ናቸው፡፡ በተለይ ስለኢትዮጵያዊነት ያደረጓቸው ንግግሮች የሕዝብን ቀልብ የሚስቡና የሳቡ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜም እያነበቡ አይናገርም፣በቃላቸው እንጂ፡፡ መሪ ደግሞ የተጻፈለትን ብቻ ማንበብ የለበትም፡፡ በተቻለ መጠን መናገር እንጂ ማንበብ የመሪ ባሕርይ አይደለም፡፡ በመሆኑም፣ዶ/ር ዐቢይ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ እመርጣለሁ፡፡

9. ቀጣዩ መሪ ከኦሮሞ መሆኑ የፍትሕ ጉዳይ ስለመሆኑ፤

ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ብቃት ወሳኝ መስፈርት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ባለፈም የዴሞክራሲና የፍትሕም ጉዳይ ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት ሲጠይቀውም የነበረ ሥልጣን ነው፡፡ ትክክልም ነው፡፡ ይህንን ሥልጣን ከሌላ ብሔር ለሆነ ሰው መሥጠትም ምናልባትም በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለውን የአለመረጋጋት አዙሪት ሊጨምረውና ሊያባብሰው ይችል ይሆናል፡፡ በመሆኑም፣አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለዚህ ቦታ ከሚመጥኑትም ውክልናና ቅቡልነትም ሊኖራቸው ከሚችሉ የኦሕደዴ መሪዎች አንዱ ናቸው፡፡ በመሆኑም፣ዶ/ር ዐቢይ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ እመርጣለሁ፡፡

10. ቀጣዩ መሪ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ውስብስብ ችግር በቅንነትም በብልጠትም በፍጥነትም መፍታት የሚችል መሆን እንዳለበት፤

አሁን ኢትዮጵያን ወጥረው የያዟት በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የሚነሱ ችግሮች እንዲሁም ወደእነዚህ ክልሎች የሚደረጉት ሥርዓት የለሽ የፌደራል ጣልቃ ገብነቶች አሉ፡፡ የኦሮምኛ ተጨማሪ የፌደራል የሥራ ቋንቋነት፣የኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ የሚኖረው የልዩ ጥቅም አጀንዳ አለ፡፡ በኦሮሚያና በኢትዮ-ሶማሌ ክልሎች መካከል ያለው ችግር አለ፡፡ የብሔራዊ መግባባት ችግር አለ፡፡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በጊዜው ባለመጠናቀቃቸው እያስከተለ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር አለ፡፡ መረን የለቀቀ የሙስና ችግርም እንዲሁ፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱ የተበለሻሸ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች በተወሰነ መልኩ እንኳን ለመቅረፍ ቢያንስ በራሱ በእነዚህ ችግሮች ውስጥ ያልተተበተበ ሰው ሊሆን ይገባል፡፡ ወይም ደግሞ፣በአንጻራዊነት ያለበት ችግር ዝቅ ያለ መሆን አለበት፡፡ ችግሮቹን በቅንልቦና እና ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ እንዲሁም ሕዝቡም ድጋፍ እያደረገለት ሊፈታ የሚችል መሪ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ላይ ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል፡፡

ከእዚህ አንጻር እና ከምናውቃቸው የኢሕአዴግ ሹመኞች ውስጥ ዶ/ር ዐቢይ የተሻሉ ናቸው የሚል የግል ምልከታ አለኝ፡፡ በመሆኑም ዶ/ር ዐቢይ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ እመርጣለሁ፡፡

Filed in: Amharic