>
5:16 pm - Monday May 23, 8535

የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ! (ስዩም ተሾመ)

የለውጥ አይቀሬነት እና የህወሓት አይቀየሬነት 
ባለፉት ሦስት አመታት በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ብዛት ያላቸው ተከታታይ ፅሁፎችን አውጥቼያለሁ። ታዲያ በዚህ ወቅት በተደጋጋሚ የማነሳቸውና ሁሌም በተግባር የሚረጋገጡ ሁለት ነገሮች አሉ። እነሱም፡- የለውጥ አይቀሬነት እና የህወሓት አይቀየሬነት ናቸው።

በእርግጥ ለውጥ የማይቀየር የተፈጥሮ ሕግ ነው። “የማይለወጥ ነገር ቢኖር ለውጥ ብቻ ነው!” የሚባለው ለዚህ ነው። በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች ዜጎች የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ በተደጋጋሚ በማንሳት ላይም ይገኛሉ። የሕዝቡ ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ የሚያገኘው በፖለቲካዊ ስርዓቱ እና በመንግስት አስተዳደር ላይ ሥር-ነቀል ለውጥና መሻሻል ማምጣት ሲቻል ነው። በአንፃሩ የህወሓት አመራሮችና ደጋፊዎች ፀረ-ለውጥ የሆነ አቋምና አመለካከት አላቸው። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ስርዓቱ ላይ ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ አይሹም።

በቀላሉ ባለፉት ሦስት አመታት የኢትዮጲያ ፖለቲካ የመጣበት፥ ያለፈበትን መንገድ በጥሞና ካየነው የለውጥን አይቀሬነት እና የህወሓትን አይቀየሬነት በግልፅ መገንዘብ ይቻላል። በ2006 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በተለይ በአምቦና ጊንጪ ከተሞች ከፍተኛ አመፅና ብጥብጥ ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል። የ2007 ትምህርት ዘመን ከመጀመሩ በፊት የኢህአዴግ መንግስት በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚገኙ መምህራን ጋር ውይይት አድርጎ ነበር። በወቅቱ የነበሩ ከ900 በላይ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ከከፍተኛ የኦህዴድ አመራሮች ተወያይተዋል።

እኔ በግሌ የኦሮሞ ሕዝብ በባለቤትነት መክሮበት ያላፀደቀው ማስተር ፕላን በፍፁም ተግባራዊ መደረግ እንደሌለበት ተናግሬ ነበር። ነገር ግን፣ በ2008 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ማስተር ፕላኑ ዳግም ተግባራዊ ተደረገ። ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ መላው ኦሮሚያን አዳረሰ። በአመቱ መጨረሻ ላይ ማስተር ፕላኑ በክልሉ መስተዳደር ውድቅ ተደረገ። ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ግን በዚያ አላበቃም። ከዚያ ይልቅ፣ ወደ አማራ ክልል ተስፋፋ። አስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታወጀ፥ ተራዘመና ተነሳ። ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ዳግም ቀጠለ።

የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ በኦሮሞ ተወላጆችን በመግደልና በማፈናቀል የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄ በእጅ-አዙር ለማፈንና ለማዳፈን ጥረት ተደረገ። በተቃራኒው የሌሎች ብሔር ተወላጆች ለኦሮሞ ሕዝብ ድጋፍና አጋርነታቸውን እንዲገልፁ አደረጋቸው። ዳግም የአስቸኳይ ግዜ ለማወጅ ተሞክሮ ውድቅ ሲሆን “ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት” በሚል በተዘዋዋሪ ሌላ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታወጀ። ምክር ቤቱ የታለመለትን ግብ መምታት ሲሳነው ለሦስተኛ ግዜ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታወጀ። በተመሳሳይ ይህ አዋጅ የታለመለትን ግብ አይመታም። ምክንያቱም የአቸኳይ ግዜ አዋጁ መሰረታዊ ዓላማ የሕዝቡን የለውጥና መሻሻል ጥያቄ በኃይል ማፈንና ማዳፈን ነው።

የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የኢትዮጲያ ሕዝብ መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እስካልተረጋገጠ ድረስ ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ይቀጥላል። በመግቢያው ላይ እንደተገለፀው የዜጎች መብትና ነፃነት፣ እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት እስካልተቻለ ድረስ ፖለቲካዊ ግጭትና አለመረጋጋት ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሰ ይሄዳል። ይህ የለውጥ ንቅናቄ የማይቀየር የፖለቲካ ህግ ነው።

ከዚህ አንፃር፣ በጣም አስገራሚና አጠያያቂ ነገር የህወሓቶች ፀረ-ለውጥ የሆነ አቋምና አመለካከት አይቀየሬነት ነው። ባለፉት ሦስት አመታት ውስጥ ብቻ የሀገራችን ፖለቲካ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሲቀያየር እንደ ኩሬ ውሃ ባሉበት ቆመው የቀሩት ህወሓቶች ብቻ ናቸው። አይተ አባይ ወልዱ ሆነ አባይ ፀሃየ፣ ስዩም መስፍን ሆነ አዜብ መስፍን፣ ደብረፂዮን ሆነ ሞንጆሪኖ፣ ትግራይ ኦንላየን ሆነ አይጋ ፎረም፣ ዳንኤል ብርሃነ ሆነ ፍፁም ብርሃነ፣ ሚሚ ስብሃቱ ሆነች ሰናይት መብርሃቱ፣ … በአጠቃላይ ሁሉም የህወሓት አመራሮችና ደጋፊዎች ከሦስት አመት በፊት ሲያንፀባርቁት ከነበረው ሃሳብና አመለካከት ትንሽ እንኳን ፈቀቅ አላሉም።

“የተበላሸ ነገር ካለ እያስተካከልን…” አቶ አባይ ፀሃየ

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ካደረጉት ውስጥ አቶ አባይ ፀሃየ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ናቸው። እኚህ ግለሰብ “ልክ እናስገባችኋለን” በማለት የተናገሯትን ነገር ከህፃናት እስከ አዋቂዎች ደጋግመው ሰምተዋታል። በሁሉም ልብ ውስጥ የቁጭት፥ ንቀትና ጥቃት ስሜት ፈጥራለች። በመጨረሻም ለማስተር ፕላኑ ውድቅ መሆን ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች።

በተለምዶ “የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም” ይባላል። አሁን ካለው የፖለቲካዊ ሁኔታ አንፃር ደግሞ የፖለቲከኞች የአፍ ወለምታ የማይተሸ ብቻ ሳይሆን የሚሸሹትን ነገር ይዞ ይመጣል። አቶ አባይ ፀሃየ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን ያለ ሕዝቡ ፍቃድና ይሁኝታ በግድ ተግባራዊ እንዲያደርጉ “ልክ እናስገባችኋለን” በማለት የዛቱባቸው የክልሉ ኃላፊዎች በስተመጨረሻ ማስተር ፕላኑን ራሳቸው ውድቅ አድርገውታል። ከዚያ በኋላ እኚህ ሰው በግብዝነት የተሞላ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም። ምክንያቱም እንዲህ ያለ በትምክህተኝነት የተሞላ ንግግር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ በብዙ እጥፍ ያመዝናል። አቶ ኣባይ ፀሃየ ግን ዛሬም ድረስ በግብዝነትና ትምክህተኝነት ከመናገር አልተቆጠቡም። ለምሳሌ ሰሞኑን በወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ዙሪያ በትግሪኛ ከተናገሩት ውስጥ ተወስዶ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በአማርኛ ተተርጉሞ ከተለቀቀው ፅሁፍ ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡-

“ኢትዮጵያ ዉስጥ ከእንግዲህ የኣንድ ብሄር የበላይነት ኣክትሞለታል። የኣማራ ትምክህት በሃይል እገዛለሁ ቢል፣ የኦሮሞ ጠባብ በሃይል እገዛለሁ ቢል በፍጹም ተፈጻሚነት የለውም፡፡ … ኣንድ ኣድርጌ ጨፍልቄ እገዛለሁ የሚል ህልመኛ ቢመጣ እስከ ሞት እንዋጋዋለን እንጂ ኣይታሰብም። ቁርጡን ይወቅ! ግፋ ቢል ሃገሪቱ ወደ መበታተን ያደርሳት እንደሆነ እንጂ ኢትዮጵያ ዳግም የገዢዎች መፈንጫ ልትሆን ኣትችልም። መገነጣጠል ድግሞ ኣማራጭ ሊሆን ኣይችልም፣ ተያይዘን መጥፋት ነው የሚሆነው። የሁላችን እጣ ፈንታ ኣንድና ኣንድ ነች… የተበላሸ ነገር ካለ እያስተካከልን በጋራ እድገት ላይ መስራት። ከዛ በዘለለ ተያይዞ ጥፋት ነው።” አቶ አባይ ፀሃየ በትግሪኛ ከተናገሩት ውስጥ ተቀንጭቦ የተወሰደ

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ አቶ አባይ ፀሃየ የአማራን ሕዝብ በትምክህተኝነት፣ የኦሮሞን ሕዝብ በጠባብነት ከመፈረጅ አልወጡም። ይህ የህወሓቶች ቆሞ-ቀር የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ዓይነተኛ ማሳያ ነው። የአማራን ሕዝብ የመብትና ነፃነት ጥያቄ በትምክህት ከመፈረጅ የባሰ ትምክህተኝነት፣ የኦሮሞን ሕዝብ የመብትና ነፃነት ጥያቄ በጠባብነት ከመፈረጅ የበለጠ ጠባብነት ከቶ ከወደየት ይገኛል። ሰው እንዴት 45 አመት ሙሉ በአንድ ሃሳብና አመለካከት ላይ ተገትሮ ይቀራል?

አቶ አባይ የህወሓትን የበላይነት ለማስወገድ የሚደረገው ትግል በሀገሪቱ ላይ “መገነጣጠል ብቻ ተያይዞ መጥፋት ያስከትላል” ብለዋል። በተቃራኒው የዜጎች ሕይወትና ንብረት እየጠፋ የህወሓትን የበላይነት ለማስቀጠል ሲባል በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች በሚሸረበው ሸርና አሻጥር ነው። የኢትዮጲያ አንድነት አደጋ ላይ የሚወድቀው በእሳቸው የሚመራው ኪራይ ሰብሳቢና ዘራፊ ቡድን የፖለቲካ ስልጣን ይዞ እንዲቀጥል ሲፈቀድለት ነው።

እኝህ ሰውዬ ወይ የራሳቸውን ሥራና ተግባር መገንዘብ ተስኗቸዋል ወይም ‘የኢትዮጲያ ሕዝብ ሥራና ተግባራቸውን አይገነዘብም’ ብለው አስበዋል። አንድም የስኳር ፋብሪካ ገንብቶ ሳያስረክብ ከደሃ ሕዝብ ላይ የተሰበሰበ 77 ቢሊዮን ብር ቀርጥፎ የበላው እርሳቸው የሚመሩት ኮርፖሬሽን አይደለም እንዴ? “አንድ ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ከውጪ ሀገር በመግዛት በጅቡቲ በኩል ላስገባ ነው” እያለ በኬኒያ በኩል 45ሺህ ኩንታል ስኳር ወደ ውጪ የሚልከው ይሄው ድርጅት አይደለም አንዴ?

ከተገዛውም፥ ከተመረተውም እየዘረፉ “የተበላሸ ነገር ካለ እያስተካከልን በጋራ እድገት ላይ መስራት አለብን” የሚባለው የትኛው የአዕምሮ ክፍል ሲታመም፣ የትኛው የሰውነት አካል ሲጎድል ነው? እንዲህ በዘረፋ ላይ የተሰማራ የፖለቲካ ቡድን ከስልጣን ቢወገድ የኢትዮጲያ ሕዝብ ከዘራፊዎች ተገላገለ እንጂ ሌላ ምን ሊቀርበት ነው? አዎ… በእርግጥ አቶ አባይ ፀሃየ እንዳሉት “የሁላችን እጣ ፈንታ ኣንድና ኣንድ ነች… ዘራፊዎችን በማስወገድ ራሳችንን ከዘረፋ መታደግ፣ አሊያም ሀገርና ሕዝብን ዘርፈን ተያይዘን መጥፋት ነው። “የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” ይሉሃል ይሄ ነው።

Filed in: Amharic