>

የአብይ አበይት ፈተናዎች  (ኦባን ሞሀመድ)   

ዶ/ር አብይ የሚጠብቋቸው ፈተናዎች በርካታ ናቸው። ቢሮውን ከሚያስረክቧቸው ከአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የተረከቧት ኢትዮጵያ እጅግ የተወሳሰበች አገርን መሆኗ የተወሳሰበች አሜሪካን ከተረከቡት አብራሃም ሊንከን ጋር ያመሳስላቸዋል።  ከዋነኞቹ አንዱ ግን ክልሎች ለማእከላዊ መንግስት ያላቸው ተገዥነት ነው። ይህም ደግሞ ከወዲሁ የአንዳንድ ክልሎች ተወላጆች የሚሰንዝሯቸው ብሔራዊ አብሮነትን በሚገዳደሩት አስተያየቶች እየተገለጠ ይታያል። ይሁንና እነዚህን ችግሮች ሊንከን በፈቱበት መንገድ ሊፈቱ አይችሉም። ችግሮቹ ተመሳሳይ ዘመኑ ግን የተለያየ ነው። አብራሃም ሊንከን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ በደቡቡ የአገራቸው ክፍል የባርነትን ኢኮኖሚ እና ስርአት አላስወግድም ካሉ እና መገንጠልን እንደ አማራጭ አስቀምጠው ከታጠቁ ሃይሎች ጋር በመዋጋት ፈደረሽኑን ማዳን ነበረባቸው፡፡ ትልቅ ዋጋ ያስከፈለ ነገርግን አሜሪካን ያዳነ ጦርነት ነበር። ያሁኒቷ ኢትዮጵያ ውስጥ አብይ ይህን ማድረግ አይችሉም። ግን የራሳቸው መንገድ መፈለግ ይኖርባቸዋል። መለስ ዜናዊ በተለያዪ ጊዜዎች እናት ፓርቲያቸውን በአዳዲስ ፍልስፍና እና አካሄድ እንደታደጉ ይነገርላቸዋል። አብይ አደጋ ላይ ያለውን ግንባር በአዲስ ፍልስፍና እና አዲስ አቅጣጫ ካልመሩት ፓርቲው የተጋረጠበት ችግር ብሔራዊ እንደምታው ከፍተኛ ይሆናል። ፓርቲያቸው ጠቃሚነቱ ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገ አብይ አዲስ ፍልስፍና ይዘው መቅረብ አለባቸው፡፡ የኢህአዲግ ውድቀት ይዞት የሚመጣው ችግር ቀላል አይሆንም፡፡ አንድም አራትም ስለሆነ የደበረው ሕዝብ ይዞ ነው የሚነካው።                                                                                                                     የተሸረሸረውን የብሄር ብሄረሰቦች ግኑኙነት ለማስተካከል አዲስ እና አስተማማኝ አቅጣጫ ማቅረብ አለባቸው፡፡ “ከማስተካከል መገነጣጠል” የሚል አስተሳሰብ ያላቸውን ወደ “ከመገነጣጠል ማስተካከል” የሚል አተያይ ሊያመጧቸው ይገባል። በተለይ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ቀላል አይሆንም፡፡                                                                   ሌላው የሚጠብቃቸው ሃላፊነት እስካሁን አራቱን ፓርቲዎች ሲያናቁር የኖረው የብሔራዊ የሃይል አወቃቀር ነው። በዚህ ደረጃ ላይ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት የኖረው ሕወሃት ወልዶ ያሳደጋቸው ፓርቲዎች አገርን የማስተዳደር ብቃታቸው ባልተናነሰ ሁኔታ ማደጉን በፍቅርና በማባበል እያሳመኑ ማረጋጋት እና ተጽእኖው እያነሰ ይሄድ ዘንድ ግድ መሆኑ ታሪካዊ ሂደት እንጂ ክፋት አለመሆኑን እያስገነዘቡ አዲስ ብሔራዊ የሃይል አሰላለፍ ማስጀመር ይኖርባቸዋል፡፡ ያንድ ቀን ስራ አይደለም፡፡ ከዚህ በኋላ የህወሃት ሚና እና ተሳትፎ እንደነበረው የሚሆን አይመስልም፡፡ ይህን እውነታ መቀበል እና አስተካክሎ ለመሄድ (በተለይም ተጋሩ የጥላቻ ኢላማ በሆኑበት ሁኔታ ቀላል አይሆንም) ለዚህም ነው ከሁሉም በፊት የብሄር ብሄረሰቦች ግንኙነት ላይ መሰራት ያለበት። መልካም ግኑኙነት ግጭትን እና የመገነጣጠልን አደጋ ያስወግዳል፡፡ አብይን ዜጎች መስማት ይፈልጋሉ። ምን ይናገሩ ይሆን?                                                    አብይ ያላቸው ስብእናና አመጣጣቸው የምእራባውያንኑን አመኔታ ሊያስገኝላቸው ይችላል፡፡ ያ ደግሞ ኢኮኖሚውን እንዲፍታታ የሚያደርግ አቅም ከፈጠረላቸው አስተድስደራቸው የተዋጣለት ይሆናል፡፡                                                                               መጭው የ2012 ምርጫ ወሳኝ ምእራፍ ነው። አስተዳደራቸው እዛ ከደረሰ። የተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ ክንዳቸው ይበረታ ይሆን? ምህዳሩን ያሰፉት ይሆን? አሁንም ፓርቲያቸውን የ100% ወንበር ባለቤት ሊያደርገው የሚችል ስራ በቀሪዎቹ 27 ወራት መስራት ይችላሉ? ወይስ ሕዝቡ ሌሎች ፓርቲዎችን ቢመርጥ ቦታውን ይለቃሉ?                                                                           ዋናውና የነገር ማሰሪያው ግን በቀጣዮቹ ወራት ህዝቡን ከጎናቸው የማሰለፍ አቅማቸው ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡ ብዙዎች ኢህአዴግን ማየትም መስማትም አይፈልጉም፡፡ ከፓርቲው መልካም ነገር ሊጠብቁ የማይችሉበት ሁኔታ ላይ ደርሰዋል፡፡ አብይ ይህን ይለውጡ ይሆን ወይስ ተቀባይነታቸውን ይለውጠዋል? አብረን እናየዋለን፡፡
Filed in: Amharic