>

ዲፕሎማሲውን በታላቅ አስተውሎትና ብልሀት ያስጓዙ ዘመናቸውን የቀደሙ ንጉሰ ነገስት (ጌታቸው ኃይሌ)

አንደኛ የአፄ ቴዎድሮስ እስረኞች መቅደላ ላይ ሲማቅቁ ልጅ ምኒልክና አጃቢዎቻቸው ምንም ሳይነካቸው አመለጡ።
ሁለተኛ፤ የወሎ ገዢ ልዕልት ወርቄም ልጇ ስለታሰረባት፥ ምኒልክና አጃቢዎቻቸው በእሷ ግዛት ሲያልፉ፥ ይዛ ለልጇ መድን ለአፄ ቴዎድሮስ አሳልፋ ትሰጣቸዋለች ተብሎ ተፈርቶ ነበር። ግን ወሬው እውነት ይሁን አይሁን ሳይታወቅ፥ ያመለጡት ልጇን ገደል ሲሰዱት በማየት ለራሳቸው ፈርተው መሆኑን አስወሩ። ወርቄ በዚህ ተናድዳ፥ እነምኒልክን ዘብ ሰጥታ፥ ሸኘቻቸው።
ሦስተኛ፤ ሸዋ ሲገቡ ግዛቱ ይገባኛል በሚል ሹም ተይዛ ደረሱ። እሱን በጥቂት ሠራዊት ማሸነፍ ትልቅ ዕውቀተ ያስፈልጋል።
አራተኛ፤ አፄ ዮሐንስ ነግሠው ምኒልክን ገብር ሲሏቸው፥ መኳንንቶቻቸው “እንዋጋለን እንጂ ለአፄ ዮሐንስ አንገብርም፤ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ከተባሉ በኋላ፥ ንጉሠ ሸዋ መባልዎን አንቀበልም፤ ውርደት ነው” ሲሉ፥ እንግሊዞች ለአፄ ዮሐንስ የሰጧቸው መሣሪያ ምን ያህልና ምን ዓይነት እንደሆን ስለሚያውቁ፥ ለጊዜው መገበርን መረጡ፤ ድንጋይ ተሸክመው ይቅርታ ጠየቁ። አፄ ምኒልክ ሊያሸንፉት የማይችሉትን፥ ለማሸነፍ ጊዜና ዘዴ ይፈልጉለታል እንጂ፥ ጦር አይገጥሙትም።
አምስተኛ፤ አፄ ዮሐንስ በንዴት በሱዳን ደርቡሾች ላይ ሲዘምቱ፥ አፄ ምኒልክ ከደርቡሾች ጋር በእንግሊዞች ላይ የጋራ ግምባር ፈጠሩ። እንግሊዞች ሪር አድሚራል ሂወትን ልከው አፄ ዮሐንስን እንደቀለዱባቸው፥ ሬነል ሮድን ልከው አፄ ምኒልክን ሊቀልዱባቸው ቢሞክሩ አልተሳካላቸውም። አምባሳደር ሬነል ሮድ አፄ ምኒልክ እንደቀለዱበት ያወቀው ወደመጣበት ከተመለሰ በኋላ ነው። ግን እዚያው ባለበት ጊዜ የውል ውይይት ሳይጀምሩ ከማን ጋር እንደሚዋዋል በምልክት ሲያስጠነቅቁት፥ “ጣሊያን ምጽዋን እንድትይዝ ለምን ጋበዛችኋት?” አሉት። ሲሰማ ክው አለ። ምንም ከማያውቅ የዋህ ሰው 3 ጋር የሚነጋገር መስሎት ነበር። የመጣው ኢትዮጵያ ከሱዳን ደርቡሾች ጋር እንዳትስማማ ቃል እንዲገቡለት ነበር። የማይከበር ቃል ያለው እንግሊዝ አገር ብቻ መስሎታል። “ግዴለህም፥ ደርቡሾች የሃይማኖታችን ጠላቶች ናቸው። እኛ እንደናንተ ክርስቲያኖች ነን” ሲሉትና በሰማው ሲደሰት፥ የደርቡሽ መልእክተኞች ከጓዳ ሆነው ይስቁ ነበር። እንግሊዝና ፈረንሳይ በኮሎኒ ሽሚያ ጊዜ በማህላቸው ግጭት እንዳይነሣ ሁለቱ ሀገሮች መስማማታቸውን ንጉሡ ስለሚያውቁ፥ የሱዳኖቹ መልእክተኞች ከመመለሳቸው በፊት የሰጧቸው ምክር፥ “በምሥራቅ (ከግብጽ) እንግሊዞች ሲመጡባችሁ፥ የፈረንሳይ ባንዲራ ሰቅላችሁ ጠብቋቸው። በምዕራብ (በፋሹዳ) ፈረንሳዮቹ ሲመጡባችሁ የእንግሊዝ ባንዲራ እያውለበለባችሁ ተቀበሏቸው” የሚል ነበር። ሰይጣን መስቀል ሲያይ እንደሚበረግግ ይበረግጋሉ ማለታቸው ነው።
 የተንኮታኮተችውን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ሌሎቹ ሲሳናቸው አፄ ምኒልክን የቀናቸውም በዚሁ በዘዴኛነታቸው ነው።
Filed in: Amharic