>

ስለአድዋ ጦርነት ምን ተባለ? (ጳውሎስ ኞኞ እንደጻፈው)

“…ውጊያው  እስቲጀመር እንጠብቃለን፡፡ …እህቴ ሆይ ይህ ደብዳቤ ሲደርስሽ በሕይወት እንደሌለው ቁጠሪው፡፡ በሕይወት የምትቀሪው አንቺ እህቴ ለታዘዝኩት ስራ በክብር መሞቴንና በክብር መሞት ደግሞ ለሰው ልጅ አስፈላጊ መሆኑን መስክሪ፡፡ …” ካፒቴን ካኖቫቲ
“… በእንደዚህ አይነት ጭንቅ ጊዜ መልካም ምኞቴን ልገልጽልህ እወዳለሁ፡፡ … ጥቂት ሰዓት ከሚያስኬድ ርቀት ላይ ራሶች ተሰልፈዋል፡፡ ባንድነት ወደ እኛ ይጓዛሉ፡፡ ባታሊዮናችንም እንድናፈገፍግ ብቻ ይነግረናል፡፡ የዚህም ውጤት መጨረሻው ምን እንደሚሆን ይገባሃል፡፡ ጦሩ እየገፋ እስቲመጣ ብቻ እንጠብቃለን፡፡ … ለታዘዝነው ትዕዛዝ ህይወታችነን እንሰዋለን፡፡ የእኛ ነገር ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፡፡ አሁን ሁሉን ነገር ትቼ የማስበው ለተከበረው ሽማግሌ አባቴ እና ለተከበረችው እናቴ ነው፡፡ አንድ የምለምንህ ነገር አለኝ፡፡ ቤተሰቦቼን ምንም ነገር ቢያገኛቸው እንድትረዳልኝ አደራ እልሃለው፡፡ …”
 መቶ አለቃ ሚሴና
“ሃያ ሺህ ያህል ወታደሮች ያሉበት የኤሮፓ ጦር በአፍሪካ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ፡፡ በእኔ እምነት መሰረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ አድዋ ያለ ጦርነት የለም፡፡ በእልቂቱ በኩል 25,000 ሰዎች በአንዲት ጀምበር የሞቱበት እና የቆሰሉበት ነው፡፡ ፖለቲካ እና ታሪክ አበቃ፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ታላቅ የተወላጆች ኃይል መነሳቱ ታወቀ፡፡ የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ፡፡ ጥቁር በነጮች ላይ ሲያምፅ እና ሲያሸንፍ የመጀመሪያው መሆኑ ነው፡፡ አበሾች አደገኛ ህዝቦች መሆናቸውን ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተፅፎላቸዋል፡፡ የእኛ አለም ገና ቶር እና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ አበሾች የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበሉ ናቸው፡፡ …አሁን የሁሉንም ፍላጎት አድዋ ዘጋው፡፡…” ቤርክሌይ፡፡
“…በጥጋባቸው አድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ፡፡ እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረኳቸው ብዬ ደስ አይለኝም…”
  እምዬ ዳግማዊ ምኒልክ
Filed in: Amharic