>
2:19 am - Wednesday February 1, 2023

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የአማካሪነት ቦታ እንዲሰጣቸው ተወሰነ

 “ኦህዴድ ቃል የገባውን ፈፅሞልኛል፤ በተደረገልኝ ሁሉ ደስተኛ ነኝ”

አለማየሁ አንበሴ

ሰሞኑን 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት መኪና ከኦህዴድ የተበረከተላቸው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ ወርሃዊ ደመወዝ የሚያገኙበት የአማካሪነት ቦታ እንዲሰጣቸው መወሰኑም ታውቋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ የካቲት 14፣ በኦህዴድ ጽ/ቤት ተገኝተው፣ ኒሳን 2018 ሞዴል መኪና የተረከቡት ዶ/ር ነጋሶ፤ “ኦህዴድ ቃል የገባውን ሁሉ ፈፅሞልኛል፤ የደሞዝ ጉዳይም ሆነ የህክምና ጉዳይ እየተመቻቸልኝ ነው፣ በተደረገልኝ ሁሉ ደስተኛ ነኝ” ሲሉ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
“በአማካሪነት የምሰራበትን ቦታ ነግረውኛል፤ እርግጠኛ ስሆን የተመደብኩበትን እገልፃለሁ” ያሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ “የደመወዜ መጠንም የሚታወቀው ይህን የአማካሪነት ስራ ስጀምር ነው” ብለዋል፡፡
መኪናው ሙሉ ለሙሉ በስጦታ እንደተበረከተላቸውና የሊብሬ መረጃውም ከሰሞኑ እንደሚሰጣቸው ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት ዶ/ር ነጋሶ፤ “ሾፌር ለመቅጠር የሚያስችለኝ ገንዘብ ሳገኝ ሾፌር እቀጥራለሁ፤ ለጊዜው ግን ራሴው አሽከረክራለሁ” ብለዋል፡፡
“በኦህዴድ በኩል ለተደረገልኝ ሁሉ አመሰግናለሁ” ያሉት ዶ/ሩ፤ “የፌደራሉን መንግስት ግን አሁንም በህግ የተሰጡኝን መብቶቼንና ጥቅማ ጥቅሞቼን እንዲያከበርልኝ መጠየቄን እቀጥላለሁ” ብለዋል፡፡

Filed in: Amharic