>

የት አባቱ ንስና! (በፈቃዱ ሞረዳ)

አንደኛ፡-
ልክ ሦስት ወር ሆነዉ መሰለኝ፡፡ በአንዱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገር ዉስጥ ከሚገኘዉ የቀድሞዉ ቱጃር የአሁኑ ስደተኛ ዘመዴ ጋር ተደዋዉለን ‹‹ መንግሥት››ን እንቦጭቅ ነበር፡፡
እናም እንዲህ አለኝ፡፡ ‹‹ ኃይለማሪያምን አዉርደን አብይን እንተካለን›› ሲለኝ ፣ ‹‹ እንዴት ሊሆን ይችላል?›› ወደሚል ጥያቄ ሳልገባ፣ ‹‹ለማ አይሻልም? ›› አልኩት፡፡
‹‹ለማ ኦሮሚያ ላይ መቆየት አለበት›› አለኝ::
የዘመዴ ሐሳብ የራሱ ተራ ምኞት ቢመስለኝም ከአባእንትና ጋር ቀረቤታ እንዳላቸዉ ስላማዉቅ ‹‹ አንድ ነገር ሊኖር ይችላል›› ብዬ ተዉኩት፡፡ ዘመዴ ነጋዴ እንጂ የፖለቲካ ሰዉ አለመሆኑ ልብ ይባልልኝ፡፡

ሁለተኛ፡

ይኼኛዉ ደግሞ አሜሪካ የሚኖር ስደተኛ ነዉ፡፡ እርሱም በአንድ ወቅት ከገዥዎቻችን ጋር ጠንካራ የቢዝነስ ግንኙነት የነበረዉ ሰዉ ነዉ፡፡ ከተወሰኑ ባለጊዜዎች ጋር ተደባብረዉ ነዉ ሀገሩን ጥሎላቸዉ ካቻአምና ወዲህ የመጣዉ፡፡ አሁንም ግን ከቀድሞዎቹ ወዳጆቹ ጋር ይገናኛል፡፡ ወሬም ያገኛል፡፡ አንዳንዴ ትርፍ ወሬ ሲያገኝ ለእኔም ያካፍለኛል፡፡
ያን ሰሞን ደወለና ‹‹ የሚቀጥለዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን እንደሚሆን ታዉቃለህ?›› አለኝ ፡፡ ማወቅ እንደማልችል ነገርኩት፡፡ ‹‹ ደመቀ መኮንን ይሆናል ብለዉኛል›› አለኝ፡፡ ምንጮቹ የሕወሓት ሰዎች ናቸዉና ‹‹ ሊሆን ይችላል›› አልኩኝ፡፡
አሁን ሁለቱም ኢሕአዴጎች የየድርጅቶቻቸዉ ሊቀመንበር ሆነዋል፡፡ ለኢሕአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆነዉ ከሁለቱ አንዱ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል፡፡ የደቡብ ዕጬም ሳይዘነጋ፡፡
የትኛዉ ወዳጄ መረጃ ይሆን ትክክል? የካቲት 24 (March 3) አሉ ሹመቱ?

በሳቅ ድባብ ሥር ሆኜ ሳስብ ኢሕአዴግ እንደዘንድሮ የሕዝብ ፓርቲ ሆኖ የሚያዉቅ አይመስለኝም፡፡ የተጨበጨበላቸዉ የተቃዋሚ ፓርቲ ኣባላትና ደጋፊዎች፣ ቀንደኛ አክቲቪስቶች…ሁሉ ‹‹ እገሌ ሊቀመንበር ቢሆንህ ይሻልሃል ›› እያሉ በምክር ሲያጨናንቁት ሳይ፡፡ የሰዎችን የፍቅርና የድጋፍ መብት እናከብራለን፡፡
ግን የኢሕአዴግ ሰዎች ኢሕአዴግ ናቸዉ፡፡
ኢሕአዴግ ደግሞ በሺህ ወገኖቼ ደም ገፅታዉን ኩሎ፣ በአደባባይ በገደላቸዉና ሰዉሮ ባጠፋቸዉ ወገኖቼ አስከሬን ላይ ተቀምጦ የሚያቅራራ ሰይጣን ነዉ፡፡ እኔ ደግሞ ከሰይጣን ዉልም እርቅም የለኝም፡፡ የት አባቱ ንስና!

Filed in: Amharic