>
5:18 pm - Saturday June 14, 6313

የህወሓት የበላይነት በውዴታ አልያም በግዴታ ያበቃለታል (ስዩም ተሾመ)

ከሦስት አመት በፊት በአዲስ አበባ የሚገኘው የጀርመን ኢምባሲ ባወጣው ክፍት የሥራ ማስታወቂያ ላይ ከጀርመንኛ፥ እንግሊዘኛ እና አማርኛ በተለየ የትግሪኛ ቋንቋ ለብቻው ቅድመ ሁኔታ ስለተደረገበት ምክንያት ማብራሪያ እንዲሰጡኝ ለአምባሳደሩ ደብዳቤ ፅፌ ነበር። የሥራ ማስታወቂያውን፣ የእኔን ደብዳቤና የኢምባሲውን ምላሽ ከታች ባለው ምስል ላይ መመልከት ይቻላል።

ከላይ በምስሉ ላይ እንደሚታየው፣ ከሦስት አመት በፊት “አራት ቋንቋዎች መስፈርት በሆኑበት የሥራ ማስታወቂያ ላይ የትግሪኛ ቋንቋ ለብቻው ለምን ቅድመ ሁኔታ ይሆናል?” ብሎ መጠየቅ በአብዛኞቹ የትግራይ ልሂቃን ዘንድ ከምክኒያታዊነት ይልቅ “ዘረኝነት” ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘ የገጠመኝን አስቸጋሪ ሁኔታ እና የእኔን አመለካከት “እኔና የጀርመኑ ኢምባሲ የሥራ ማስታወቂያ” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ (Pdf) ላይ በዝርዝር ገልጬያለሁ።
በተመሳሳይ ከሁለት አመት በፊት ደግሞ ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል “የትግራይ/ህወሓት የበላይነት የለም” የሚል አስተያየት ሰጥተው ነበር። እንደ እሳቸው አገላለፅ፣ በፌዴራሊዝም ስርዓቱ መሰረት እያንዳንዱ ክልል ራሱን-በራሱ የማስተዳደር ስልጣን ስላለው የትግራይም ሆነ የሌላ ብሔር የበላይነት ሊኖር አይችልም፡-

“/የትግራይ የበላይነት/ የሚባለው አንዳንዱ የተዛባ አመለካከት ነው፣ አንዳንዱ ደግሞ ፈጠራ ነው። ከፌዴራል ጀምረህ የስርአቱን አወቃቀር ነው የምታየው፡፡ /አወቃቀሩ ካልፈቀደ/ “የበላይነት“ የሚፈልግም ካለ ስሜት ብቻ ፤ “የበላይነት አለ“ የሚልም የራሱ ግምት ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ …/በኢህአዴግ/ አንዱ በደንብ የገምገምነው እሱን ነው፤ “የትግራይ የበላይነት“ የሚባል የለም ነው፡፡ ህወሓት ኦሮሚያን ወይም አማራ ክልልን ሊያስተዳድር አይችልም፡፡ ስርአቱ አይፈቅድም።” ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (hornaffairs)

ከላይ የተጠቀሰውን አስተያየት መነሻ በማድረግና አንዳንድ የጥናት ስራዎችን በማጣቀስ “አዎ…የትግራይ/ህወሓት የበላይነት አለ” የሚል ፅሁፍ አውጥቼ ነበር። ከዚያ በመቀጠል ደግሞ “የህወሓት የበላይነት በውዴታ ወይም በግዴታ ያበቃል”፣ “በሕገ-መንግስቱ የህወሓት የበላይነት እንጂ የሕግ የበላይነት የለም”፣ “የህወሓት የበላይነት የሚረጋገጠው በፍርሃትና ሽብር ነው” እና ሌሎች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ፅሁፎችን አውጥቼያለሁ። ነገር ግን፣ ልክ እንደ አምና እና ካቻምና አሁንም ለህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ጎልቶ የሚታየው ከፅሁፎቹ ይዘት ይልቅ የእኔ “ዘረኝነት” ነው።

ህወሓቶች ወደ ቀልባቸው የተመለሱት በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ በተካሄደው የኢህአዴግ ስብሰባ ላይ ነው። በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ በተካሄደው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ “የህወሓት/የትግራይ የበላይነት አለ” የሚለው ሃሳብ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል። ከዚህ ስብሰባ አፈትልኮ በወጣው ሰነድ መሰረት፣ ከሁለት አመት በፊት “የህወሓት/የትግራይ የበላይነት የሚባለው ነገር የተዛባ አመለካከት ወይም ፈጠራ ነው” ሲሉ የነበሩት ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል በትግራይ/ህወሓት የስልጣን የበላይነት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዙሪያ በቀጣይ መወያየት እንዳለባቸው ለኢህአዴግ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሃሳብ አቅርበዋል።

በመጨረሻም 17 ቀናት በፈጀው የኢህአዴግ ስብሰባ የኦህዴድና ብአዴን አመራሮች ስለ ህወሓት የበላይነትና ኪራይ ሰብሳቢነት የሚያሳዩ እልፍ መረጃዎች እና ማስረጃዎች መቅረባቸው ውስጥ አዋቂዎች ገልፀዋል። ውስጥ አዋቂዎቹ አያይዘው አንደገለፁት፣ የህወሓት አዲሱ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል የትግራይ/ህወሓት የበላይነት መኖሩን አምኖ ተቀብሏል። በተለይ ከሌሎች የህወሓት ሥራ አስፈራሚ አባላት አንፃር “ለዘብተኛ” የሚባል አቋም ያለው አንድ ክፍተኛ የህወሓት አመራር “የህወሓት የበላይነት በውዴታ ወይም በግዴታ ያበቃል” በማለት ቃል-በቃል ተናግሯል። እንደ እሱ አገላለፅ፣ የህወሓት የበላይነት በውዴታ የሚያበቃ ከሆነ ልሂቃኑ ጥቅማቸውን ለማስከበር መደራደር ይችላሉ። በግዴታ የሚያበቃ ከሆነ ግን ጥቅማቸውን ሙሉ በሙሉ ሊያሳጣቸው እንደሚችል በግልፅ ተናግሯል።

የኢህአዴግ ስብሰባ በዶ/ር ደብረፂዮን የሚመራው አዲሱ የህወሓት አመራር የትግራይ/የህወሓት የበላይነት እንዳለ አምኖ ተቀብሏል። ችግሩንም ለመፍታት ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት ተስማምቷል። በዚህ መሰረት በመከላከያና ደህንነት ተቋማት ውስጥ ያለውን የህወሓት የበላይነት ለማስወገድ በአፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ የሚመራ ልዩ ኮሚቴ መዋቀሩ ተገልጿል። አቶ አባዱላ ገመዳ ወደ አፈ-ጉባኤነት የተመለሱበት “ሚስጥር”፣ እንዲሁም በሀገር መከላከያ ውስጥ እየተደረገ ያለው የስልጣን ሽግሽግ ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይገመታል።

ታዋቂው የስነ-ልቦና ምሁር “Sigmund Freud” በስልጣን ላይ የነበሩ ባለግዜዎች ከእነሱ የተለየ ሃሳብና አመለካከት የሚያንፀባርቁ መፅሃፍትን ሰብስበው ሲያቃጥሉ በተመለከተ ግዜ “ተሻሽለናል! ድሮ ድሮ ደራሲውን እናቃጥል ነበር፣ ዘንድሮ ግን መፅሃፍቱን ማቃጠል ጀምረናል። በጣም ተሻሽለናል!” የሚል ሽሙጥ ተናግሯል ይባላል። በተመሳሳይ ይህ ሽሙጥ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች አሁን ያሉበትን ሁኔታ በደንብ ይገልፃል። በህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ዘንድ “የህወሓት/የትግራይ የበላይነት” የሚባለው ነገር ካቻምና “ዘረኝነት” ነበር፣ አምና “የተዛባ አመለካከት” ተብሎ፣ ዘንድሮ “ተጨባጭ እውነት” ሆነ።

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ “የህወሓት/የትግራይ የበላይነት” የባለው ነገር ከሦስት አመት በፊት በትግራይ ሕዝብ ላይ የተሰነዘረ የዘረኝነት ጥላቻ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። ዘንድሮ ግን በህወሓት/ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ የውይይት አጀንዳ ከመሆን ጀምሮ ተቀባይነት ያለው ነባራዊ እውነታ ለመሆን በቃ። በእርግጥ “የህወሓት የበላይነት” በተጨባጭ ያለና የነበረ ነገር ነው። ይህን በተጨባጭ የሚስተዋልን ነገር “የተዛባ አመለካከት” እና “የፈጠራ ወሬ ወይም ውሸት ነው” ሲሉ የነበሩ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ዘንድሮ አምነው ተቀብለዋል። በዚህ መሰረት፣ እስካሁን ድረስ በተዛባ አመለካከት እየተመሩ የፈጠራ ወሬ ሲያወሩ እንደነበር በራሳቸው ላይ መስክረዋል።

ህወሓቶች ትላንት ላይ “የህወሓት/የትግራይ የበላይነት አለ” ስንላቸው ሲክዱ እንዳልነበር ዛሬ ላይ እውነት መሆኑን ተቀብለዋል። ዛሬም ሆነ ነገ ህወሓቶች ይህን እውነት ተቀብለው በአስቸኳይ ምላሽ መስጠት ከተሳናቸው ኢህአዴግ ይፈርሳል። ምክንያቱም በአባላት ቁጥር፣ በምክር ቤት መቀመጫ ሆነ በሚወክሉት ሕዝብ ብዛት አብላጭ ድምፅ ያላቸው ኦህዴድ እና ብአዴን ከህወሓት ጋር በአብሮነት መቀጠል አይችሉም

Filed in: Amharic