እግዚአብሔር በጥበቡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንቂ አጋር የሚሆኑትን ላከለት፣ኮሎኔል ደመቀ፣ፍቅሬ ቶሎሳ(ፕ/ሮ)፣ሰለሞን ደሬሳ፣ከዚያም ለማ መገርሳ፣ዓቢይ(ዶ/ር)፣ሬሳ የመሰለው የኢትዮጵያ ሕዝብ አጋር ሲያገኝ ተንቀሳቀሠ፣ትንፋሽ ተነፈሰ፣ያለነው እዚህ ላይ ነው።
የጻእረ ሞት እንቅስቃሴና የንቃት እንቅስቃሴና ሊመሳሰሉ ይችላሉ፤ግን ሁለቱን ማሳሳት(ንቃትን እንደ ጻእረ ሞት ወይም ጻእረ ሞትን እንደ ንቃት መቀበል) በጣም አደገኛ ነው፣ንቃት የሕያውነት ብሥራት ነው፣ጻእረ ሞት የሞት ብሥራት ነው፣ኢትዮጵያ ዛሬ በሁለት ብሥራቶች መሀከል ነች፣መግደል የሞት አጋፋሪ ነው፣መግደል የሕይወት ጸር ነው፣ንቃት የአዲስ ሕይወት የነጻነት ክህሎት፣የሀሣቦች ፍጭት፣የልማትና የእድገት ውድድር፣የዜግነት ኅብረት መሠረት ነው፣ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበት መንታ መንገድ አንዱ ጻእረ ሞትን ያሳያል፣በምርጫችን እንሞታለን ወይም በምርጫችን እንለመልማለን።…………
፠፠
የሐበሻ ወግ ቅፅ 2 ቁ 67 የካቲት 2010 ገጽ 13 የተቀነጨበ