ከ122 አመታት በፊት
የንጉሠ ነገሥት ምኒሊክ ጦር ብዙ ብቻ ሳይሆን ድፍን ኢትዮጵያን የወከለ ነበር፡፡
ስለዚህ…
አበሻን እገዛለሁ ብሎ ሰፍ ያለውን ጣልያን ጉድ ያፈሉት ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡
ያልተቆጠሩትን ብንተው በአንዲት ቀን ጦርነት የወደቁት 7000 ሰዎች….ከደቡብ ተመሙ ከሰሜን፣ ከምስራቅ ሆ ብለው መጡ ከምእራብ…ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ነፃነትዋን የጠበቀች፣ ራስዋን የቻለች መንግስት መሆኗን በደም እና በአጥንት ያረጋገጡት ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡
እግራቸውን ለጠጠር፣ ደረታቸውን ለጦር ሰጥተው ጣልያንን ያንጰረጰሩት ፈረሰኞች፣
ፋስሽትን የፈጁት እግረኞች፣ ነጭን መግቢያ ያሳጡት ነፍጠኞች ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡
ለአንድ ጠላት ሶስት እና አራት ተቧድነው ታሪክን የቀየሩት ጀግኖች…አዎን…ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡
አፍሪካ በአውሮፓ ላይ ማመፅዋን ያበሰሩት፣ አምፃም ማሸነፍ መቻሏን በድል ያረጋገጡት ጥቁር ህዝቦች ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡
በፀሃይ ግለት እና በአቧራው፣ በረሃብና በውሃ ጥም ሳይበገሩ ዛሬ የምንወዳት ሀገራችን ተከብራ፣ ታፍራ፣ ከፍ ብላ ሁሌም በነፃነት ትኖር ዘንድ በአደራ የሰጡን አባት እናቶቻችን…ድፍን መጠሪያቸው ኢትዮጵያዊ ፣ የወል ማንነታቸው ኢትዮጵያ ናት፡፡
ለዚህ ነው ከደምና ከአጥንት ተሰርቶ በአደራ የተሰጠንን ኢትዮጵያዊነት ሲያሻን እንደምናጠልቀው፣ ሳያሻን አውልቀን እንደምንጥለው ባርኔጣ የማናየው፡፡
ለዚህ ነው ኢትዮጵያዊነትን እንደ እድሜያችን መቁጠሪያ፣ እንደ ታሪካችን መዘከሪያ፣ እንደ ተበተነ ዘር መቋጠሪያችን የምንቆጥረው፡፡
ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊነት ሞገስ ክብራችን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ብቸኛ መነሻ እና መድረሻችን መሆኗን የምለፍፈው፡፡
ለዚህ ነው ኢትዮጵያዊነት ውሃ ቢሆን እንዳይደርቅ፣ ህዝቡ ደግሞ አሳ ቢሆን እንዳያልቅ የምንጮኸው፡፡
ለዚህም ነው…ዛሬም በኢትዮጵያዊነት ላይ ፀሀይ እንዳትጠልቅ ላይ ታች ለሚሉ፣ በጋለ የሀገር ፍቅር ስሜት ለሚነዱ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ መልካም የድል በዓልን የምንመኘው!