>

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚቆም የነጻነት ትግል እንደማይኖር በተግባር ለማሳየት ዝግጁዎች ነን።

 የአርበኞች ግንቦት 7 ርዕሰ አንቀፅ
የህወሃት አገዛዝ ለዛሬ  የካቲት 23 ቀን 2010 ጠርቶት የነበረው አስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ የካቲት 9 ቀን 2010 የሚንስትሮች ምክር ቤት የተባለው ስብስብ ያወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ346 ድምጽ ድጋፍ በ88 ተቃውሞና በ7 ድምጸ ታዕቅቦ ማጽደቁን አስታውቆአል። ከዚህ የዛሬው የፓርላማ ውሳኔ ሁለት ነገሮችን ማስተዋል ተችሎአል።
1. ያለፈውን ምርጫ መቶ በመቶ በማሸነፍ 547ቱንም የአገሪቱን ፓርላማ መቀመጫ ሙሉ በሙሉ እንደተቆጣጠረ በኩራት ሲደሰኩርና አለምን ሲያስደምም የቆየው የህወሃት/ኢህአደግ አገዛዝ በዛሬው የፓርላማ ውሎ የድጋፍና የተቃውሞ ድምጽ የሰጡ አባላቱ ብዛት 441 ብቻ እንደሆኑ ሲያስታውቅ የተቀሩት 106 አባላቱ የት እንደደረሱ እንኳ መግለጽ አለማቻሉ የደረሰበት የውስጥ ቀውስ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለመሸፈን ከማይችልበት አጣብቂኝ ውስጥ መውደቁን ያስገነዝባል።
2. አገዛዙ እመራበታለሁ በሚለው ህገመንግሥት እንዲህ አይነት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ከፓርላማ አባላቱ የ2/3ኛ ድምጽ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ በግልጽ ተቀምጦ እያለ እና የ547 አባላት 2/3ኛ ድምጽ ማለት ቢያንስ የ365 ሰዎች ድጋፍ ማለት መሆኑ እየታወቀ በምን ሲሌት የ346 አባላት ድጋፍ አዋጁን ለማስጸደቅ ችሎአል እንደተባለ ይዞት የመጣው ተቃርኖ ስላስጨነቀው ይመስላል ቀጥሎ ቁጥሩን ለመለዋወጥ የሚታገለውና በኮረም ሞልቷል ስም ሊያምታታ የሚሞክረው።
ወያኔ ለማናፈስ እንደሚሞክረው የአስቸካይ ጊዜ አዋጁን በፓርላማ ለማስጸደቅ ኮረም ሞላለት አልሞላለት የኢትዮያ ህዝብ በዛሬው ቀን በተካሂደው አስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ ተላለፈ ከተባለው ከዚህ ውሳኔ አንድ ትልቅ ድል ተቀዳጅቶአል። ይሄውም መቶ በመቶ የህወሃት/ ኢህአደግ አባላት መሆናቸው ከሚታወቅ 547 የፓርላማ አባላቱ መካከል 106ቱ ስብሰባው የተጠራበት አላማ በህዝባቸውና በወገናቸው ላይ እልቂትን ለማወጅ እንደሆነ ተረድተው የውሳኔው አካል ላለመሆን  የፓርላማ ስብሰባ ላይ ላለመገኘት መወሰናቸው ፤ 88ቱ ደግሞ በታሪክና በህግ ፊት ተጠያቂ ላለመሆን  አዋጁ እንዳይጸድቅ በግልጽና በድፍረት የተቃውሞ ድምጻቸውን  ማስመዝገብ መቻላቸውና 7ቱ ድምጸ ተአቅቦ በማድረግ በድምሩ 201 አባላቱ ከህዝብ ጋር መወገናቸውን በተግባር ማሳየታቸው ነው ። ይህን እርምጃ የወሰዱት እነዚህ 201 የፓርላማ አባላት ሰሞኑን ቱባ ቱባ የህወሃት ካድሬዎችና የደህንነት መሥሪያቤቱ ሃላፊዎች እያንዳንዱን የኢህአደግ አባል ድርጅት  አመራሮችንና የፓርላማ ተወካዮችን ከቤት ቤት እያሳደዱ በተለመደው ዘዴያቸው ከተቻለ በጥቅም በመደለል ካልሆነ ደግሞ በፍርሃት በማሽመድመድ አዋጁ እንደተለመደው በሙሉ ድምጽ እንዲያጸድቁት ሲፈጥሩባቸው የነበረውን ጫና ሁሉ በመቋቋም የወሰዱት እርምጃ እንደሆነ ይታወቃል። ለነጻነቱ እየተፋለመ ያለው ህዝባችን ይህ አፋኝ አዋጅ በፓርላማው ውስጥ ህወሃት እንደተመኘው በሙሉ ድምጽ እንዳይጸድቅ ላሰናከሉትና ሽንፈት እንዲጎነጭ ላደረጉት በተለይም ደግሞ በድፍረት የተቃውሞ ድምጻቸውን ላስመዘገቡ የፓርላማ አባላት ትልቅ አድናቆት አለው። እነዚህ ወገኖች የህዝባቸውን መከራና ሲቃይ ለማስቆም የሚችሉትን አድርገዋልና በታሪክና በህግ ፊት ብቻ ሳይሆን በወገናቸው ፊትም እራሳቸውን ከተጠያቂነት ነጻ እንዳደረጉ አውቀው ይህ አዋጅ በህዝባቸው ላይ የሚያደርሰው እልቂት እንዳይሳካ ከህዝባቸው ጎን ቆመው እስከመጨረሻው መፋለም ይጠበቅባቸዋል። እዛው ፓርላማ ውስጥ ሆነው ሊያበረክቱት የሚችሉት አስተዋጾ ቀላል እንዳልሆነ እነርሱም ህዝባችንም በሚገባ ያውቁታል። በአንጻሩ እዚያው ፓርላማ ውስጥ በወያኔ እጅ ጥምዘዛ ተሸንፈው ወይም እስከዛሬ ያገኙትን የጥቅም ፍርፋሪ እንዳይቀርባቸው አስበው ወይም ጥቅማቸውን አስልተው ይህ ፋሽስታዊ አዋጅ እንዲጸድቅ የድጋፍ ድምጻቸውን የሰጡ ወገኖች የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር በህግና በታሪክ ፊት ብቻ ሳይሆን በህዝባቸውም ዘንድ የሚጠየቁበት ቀን ሩቅ እንዳልሆነ ሊገነዘቡት ይገባል።  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ቀን ጀምሮ ሰሞኑን በደምቢዶሎና በነቀምቴ ለፈሰሰው የንጹሃን ደም እንዲሁም  ከአሁን ቦኋላ በወገኖቻችን ላይ ለሚፈጸመው ጭፍጨፋ ከህወሃት እኩል ተጠያቂ እንደሚሆኑ መዘንጋት የለባቸውም።
ህዝባችን ለመብቱና ለነጻነቱ የጀመረውን ትግል በሃይል ለመጨፍለቅ እብሪተኞቹ የህወሃት መሪዎች ያወጁት ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምንም መንገድ የታለመለትን አላማ እንዳይመታ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 አገዛዙ ካሰማራው የጸጥታ ሃይል ጋር እየተፋለመ ካለው ህዝባችን ጎን ቆሞ የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ለጠላትም ለወዳጅም በፍጹም ልበ ሙሉነት ይገልጻል። ።
በዘመናዊ ጦር እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የጠላት ጦር የዛሬ 122 አመት አድዋ ላይ አፈር ከድሜ አብልቶ ነጻነቱንና ሉአላዊነቱን አስከብሮ የኖረው ጀግኖች አባቶቻችን የልጅ ልጆች ነንና በአገር ሃብት ዘረፋ ልባቸው ያበጠው የህወሃት መሪዎች የተማመኑበት ጦር ብዛትና መሣሪያ ጋጋት ከጀመርነው የነጻነት ትግል ለአፍታም ቢሆን እንደማያስቆመን በተግባር ማሳያ ጊዜ አሁን እንደሆነ አርበኞች ግንቦት 7 አንዳቺ ጥርጣሬ የለውም ።
ግፍና መከራ በቃኝ ብለህ  የተነሳሄው  የኢትዮጵያ ወጣት ፤ የአገርህን ዳር ድንበር ለመጠበቅ ስትል በመከላኪያ ሠራዊት ፤ በፖሊስ ሃይልና በደህንነት ተቋማት ውስጥ በማገልገል ላይ ያለህ ከህዝብ አብራክ የወጣህ ወገናችን ! ይህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የህወሃት ዕድሜ ማራዘሚያ ሳይሆን የሚመካበት ጉልበትና አቅም መጥፊያው መሆኑን አውቆ እራሱን ለህዝብ ጥያቄ እንዲያስገዛና ሁሉንም ተቃዋሚ ሃይል ባሳተፈ የሽግግር ሂደት ህዝባችን እየተዋደቀለት ወዳለው የዲሞክራሲ ሥርዓት እንድንገባ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 እያካሄደ ካለው ትግል ጎን እንድትሰለፍ  ወገናዊ ጥሪ ቀርቦልሃል ።
በዚህ አጋጣሚ የአዲስ አበባ ወጣት የእስከ ዛሬ ዝምታውን ሰብሮ ዛሬ በተካሄደው የአደዋ ድል በዓል ላይ ያሰማው “ይለያል ዘንድሮ የወያኔ ኖሮና እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም” መፈክሮች ተጠናክሮ እንዲቀጥልና አድስ አበባችን  የወያኔ እብሪትና ጥጋብ ማስተንፈሻ ማሳያ ትግል አደባባይ እንዲሆን አርበኞች ግንቦት 7 ለአዲስ አበባ ወጣት ልዩ ወገናዊ  ጥሪውን ያስተላለፋል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !
Filed in: Amharic