>

እነሆ በዛሬው ዕለት የዐድዋ ድል በፓርላማችን ተደገመ (ዘመድኩን በቀለ)

~ 1888 የዐድዋ የድል ቀን –
~      88  ድል አድራጊ የፓርላማ አባላት ቁጥር
#ETHIOPIA | አዲስአበባ ~ 4ኪሎ ~ ፓርላማ 
~ የዛሬ 122 ዓም የካቲት 23/1888 ዓም አባቶቻችን በእምዬ ምንሊክ መሪነት በዐድዋ ተራሮች ላይ ወራሪውን የፋሽስት ኢጣልያን ጦር አሸንፈው ነጮችን የማሸነፍ አዲስ ታሪክ በዚህች ፕላኔት ላይ አስመዘገቡ ።
~ ከ122 ዓመት በኋላ ዛሬ የካቲት 23/2010 ዓም በኢትዮጵያ ፓርላማም የዐድዋው መንፈስ የወለዳቸው 88 ኢትዮጵያውያን መገኘታቸው ተሰምቷል ። አብዘሰኛዎቹ በዐድዋ ጦርነት ወቅት በፈረሰኝነት ተሳትፈው ጣልያንን ድባቅ የመቱት የጀነራል ታደሰ ብሩ ፣ የራስ ጎበና ደጨው የልጅ ልጆች የሆኑት የኦሮሞ ነገድ አባላት እንደሆኑ ተነግሯል ። ብራቮ ኦሮምያ ኢትዮጵያ ።
~ ወዳጄ !  በሙሉ ድምጽ ያለማጽደቅ ሥራ የሌለው ፣ በእንቅልፍ የናወዘ ፣ በማጨብጨብ መዳፉ የተላጠው ፓርላማ ፣ ተቃውሞ ፣ ድምጸ ተአቅቦ የማያውቀው ፓርላማ በ27 ዓመት ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በድፍረት እጁን አውጥቶ መቃወሙ በራሱ ለእኔ እንደተአምር ነው የምቆጥረው ።
~ 7 ቱም በድምጸ ተአቅቦ የተቆጠሩት ግማሽ ጀግኖች ናቸው ። ህወሓትም ይበላቸዋል ፣ ህዝቡም ይጠላቸዋል ። 88ተ ግን ሙሉ ጀግኖች ናቸው ። እስቲ አንድ ጊዜ ለእነዚህ ጀግኖች ቆም ብለን እናጨብጭብላቸው ።
~ በዛሬው የምክርቤት ውሎ ለወትሮው እንደ ፋብሪካ ምርት ተመሳሳይ አቋምና ጠባይ የነበራቸው የፓርላማ አባላት በድንገት ” ተቃውሞ ” ያሳዩትን የቀድሞ ጓዶቻቸውን በማየት እንደ ልዩ ፍጡር ሲመለከቷቸው እንደነበርም ተዘግቧል ።
~ አቶ ጌታቸው ረዳ የድጋፍ ድምጽ ያልሰጡትን ለመቆጣጠር አንገታቸው እስኪቀነጠስ በተቀመጡበት ሲሽከረከሩ ታይተዋል ። ያልደገፉትን ለመለየት ሲባል አባላቱ ከፊት ለፊታቸው የተቀመጠውን አባዱላን ማየት ትተው ወደኋላ ዞረው ተቃዋሚዎችን ሲቆጥሩ ውለዋል።
~ በዚህ ትርኢት ላይ ልክ እንደምርጫው ጊዜ ዛሬም ቁጥር ሲቀሸብ ፣ አንድ የተከበረ የፓርላማ አባልም ሁለት እጁን ሲያወጣ በካሜራ አይን ገብቶ ተዋርዷል ።
~ በዚህ ቀውጢ ሰዓትም እንቅልፋቸውን የሚለጥጡ አንድ የፓርላማ አባል እንደነበሩና የተፈጠረውን ግርግር ሁሉ ሳይሰሙ በሰላም ወደቤታቸው መሔዳቸው ተነግሯል ። አሁን የእኚ አባል ድምጽ ለማን ነው የሚቆጠረው ።
~ ለማንኛውም ~ 1888 የዐድዋ ድል የተበሰረበት ዕለት ሲሆን ። 88ቱ የፓርላማ አባላት በዛሬው የዐድዋ በዓል ዕለት የዐድዋ መንፈስ የወለዳቸው ጥርት ያሉ ኢትዮጵያውያን ሆነው ተመዝግበዋል ። ወይ 88 !
~ ለማንኛውም ኢትዮጵያችን ለሚቀጥሉት 6 ወራት ያህል ከትግራይ በቀር ሌሎቹ ክልሎች በጓጉንቸር የብረት ቁልፎች መከርቸማቸው ታውጇል ። ነገ የሚሆነውን መጠበቅ ብቻ ነው ። ያለ ፈጣሪ የነገን የሚያውቅ የለም ።
~ እኔ የምለው ዕጩው ጠቅላይ ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ በዛሬው የፓርላማ ውሎ አለመገኘቱ ተነግሯል ። ለመሆኑ ዐብዬ ” አፈገፈገ ወይስ ሸሸ “?
ሻሎም !  ሰላም !
Filed in: Amharic