>
3:00 pm - Friday May 20, 2022

አዋጁ የበላቸው ወጣቶች (በጌታቸው ሺፈራው)

ዛሬ ጠዋት ነው። አንድ በቅርቡ የተፈታ ወዳጄ ደውሎ፣  ባለፈው አመት በታወጀው አዋጅ ከባህርዳር ታፍኖ የተወሰደ ወጣት ቤተሰቦች፣ ወጣቱ ተገድሏል ብለው ማቅ ለብሰው እያለቀሱ እንደሆነ፣ ምን አልባት እስር ቤት ውስጥ የሚያውቀው ሰው ከተገኘ እንዳጣራ ጠየቀኝ። ታፍኖ ተወሰደ የተባለውን ወጣት ፎቶ ቤተሰቦቹ እንዲልኩልኝና እንዳጣራ ለደወለልኝ ጓደኛዬ ነገርኩት። ፎቶው ተላከልኝ። ቂሊንጦ እያለሁ አንድ መሰረት የሚባል ከባህርዳር ታፍኖ የመጣ ወጣት አውቃለሁ።  ከእሱ ጋር አንድ ቤት ታስሮ የነበር ጓደኛዬ ስለነበር፣  የተላከው ፎቶ አንድ ቤት አብሮት ታስሮ የነበረው መሰረት መሆኑን እንዲያረጋግጥልኝ ፎቶውን ላኩለት። አይደለም አለኝ።  እሱ እንዲያረጋግጥልኝ ነው እንጅ እኔም እንዴት እንደተሰቃየ ያወራኝ መሰረት እንዳልሆነ ከፎቶው ተረድቻለው።
ደብዛው  የጠፋው መሰረት
መሰረት አሰፋ ዘሪሁን ባህርዳር ቀበሌ 3  ትንሽ ጣውላ ቤት ነበረችው።  ጥቅምት 20/2009 ዓም ከጠዋቱ አራት ሰዓት ገደማ የማያውቃቸው ሰዎች  የጣውላ ስራ እንዲሰራላቸው ይደውሉለታል። ሙሉአለም አዳራሽ ፊት ለፊት እንደሚገኙ ይጠቁሙታል። ይህ ምስኪን  የስራ ሰው በጠዋቱ ስራ አገኘሁ  ብሎ ወደቦታው ሮጦ ይደርሳል። ያጋጠመው ግን ካሰበው የተለየ ነበር። አሁንም ድረስ ደብዛውን ያጠፋው አጋጣሚ። ኮማንድ ፖስት!
በወቅቱ መሰረት ሁለት ስልኮችን ይዞ እንደነበር ቤተሰቦቹ ይገልፃሉ።  ቴሌ የሚሰራ ሰው ማረጋገጥ እንደቻለው፣ አንደኛው ስልኩ ሙሉአለም አዳራሽ ፊት ለፊት ሲጠፋ፣ ቀሪው ቀበሌ 13 እስኪደርስ አልጠፋም። ከእሱ በተጨማሪ ሌላ ሰው ሲያፍኑም ባገኘው ክፍተት ይሁን እንጃ፣ በአንደኛው ስልኩ ደውሎ ጓደኛውን ማነጋገር ችሏል። መሰረት ባገኘው አጋጣሚ ለጓደኛው ደውሎ “በጥቁር መኪና አፍነው ወደ ቀበሌ 13 ዲፖው አካባቢ እየወሰዱኝ ነው”  ማለት ችሏል። ከዛ በኋላ ስልኩ ተዘግቷል። የመጨረሻው የመሰረት ድምፅ ይህ ብቻ ነበር። ከዛ በኋላ አየሁት የሚል አልተገኘም።  አየሁት የሚል ባለመገኘቱም ቤተሰቦቹ “ሞቷል” ብለው ጥቁር ለብሰዋል። ሀዘን ላይ ናቸው። አንድ ቤተሰቡ “መኮድ አካባቢ ተገድለው የተቀበሩ ወጣቶች እንዳሉ እንሰማ ነበር። መሰረትም ተቀብሯል ብለን ሀዘን ላይ ነን። “ሲል በስልክ ገልፆልኛል።
ቂሊንጦ የማውቀው  ሌላኛው መሰረት
 ዛሬ “ደብዛው ስለጠፋ ቤተሰቦቹ ሀዘን ላይ ናቸው” ተብሎ ፎቶው የተላከልኝ መሰረት፣ ቂሊንጦ የማውቀው መስሎኝ ነበር። ግን አይደለም። በእርግጥ የቂሊንጦው መሰረትንም ታፍኖ የመጣው ከባህርዳር ነው። ይህኛው መሰረት ትውልዱ  ባህርዳር ቢሆንም ኑሮው ቤንሻንጉል ነበር። ለተወሰኑ ቀናት ወደባህርዳር በመጣበት ወቅት “ኮማንድ ፖስት” በተሰኘው ማፈኛ ሰበብ ታፍኖ አባይ ማዶ በሚገኝ አዳራሽ ይታሰራል። ከአርባ ያህል ወጣቶች ጋር ለሁለት ሳምንት ያህል መከራ ከተቀበለ በኋላ፣ አይኑን ታስሮ ወደልታወቀ ቦታ ይወሰዳል። ከጊዜ በኋላ ይህ ያልታወቀ ቦታ አዲስ አበባ መሆኑን እንደተረዳ አጫውቶኛል። ለወራት ጨለማ ቤት ውስጥ ታስሯል። “መርማሪዎች” ተራ በተራ ወጣቶች እየወሰዱ ሲገርፉ እሱም  ተራው ደርሶት  ስቃይ ተቀብሏል። ከባህርዳር ከታፈኑ ወጣቶች መካከል በዛ ሰቆቃ ቤት ውስጥ የሞቱ እንዳሉ አጫውቶኛል።
ሆኖም እሱ እድለኛ ነበር። ከአራት ወር በኋላ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ ችሏል። ከዛ ሰቆቃ ከአራት ወርም በኋላ ቢሆን ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ እድለኝነት ነው። መሰረት ቦሌ ፍርድ ቤት ሲቀርብ፣ መርማሪ ፖሊሱ “በርካታ  ጥይቶችን የሚተፋ የግንቦት 7 መድፍ ፎቶ ተገኝቶበታል፣ የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ፎቶ ሞባይሉ ላይ ተገኝቷል” በሚል በከፍተኛ የሽብር ወንጀል እንዲከሰስለት ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ በጊዜያዊ አዋጁ ብቻ  እንዲከሰስ በማለት 3 አመት ተፈርዶበታል። አሁንም አልተፈታም!
ከአመት በፊት በታወጀው ጊዜያዊ አዋጅ ከቀያቸው የታፈኑ ወጣቶች ዛሬም ደብዛቸው አልተገኘም።  ጊዜያዊ አዋጁ በርካቶችን ሰለባ ስለማድረጉ የሞክሸዎች ታሪክ ማየት በቂ ነው። በርካቶችን በማፈሱ የተነሳ ከአንድ ሰፈር፣ ከአንድ ቤተሰብ፣ ከአንድ ከተማ፣ ሞክሸዎችንም ሰለባው አድርጓል። ባለፈው አመት የታወጀው አፋኝ “ህግ” (የፕሮፌሰር መስፍን  ሕገ አራዊት የተሰኘ አገላለፅ በደንብ ይገልፀዋል) ያሰራቸው ወጣቶች ደብዛ ሳይገኝ፣ ዛሬ ሌላ አፋኝ አዋጅ ታውጇል። አንደኛው መሰረት ሳይገኝ፣ የእነሱ ቤተሰቦች ጥቁር ልብሳቸውን ሳያወልቁ፣ ሕጉ በአርባ ስምንት ሰዓት ፍርድ ቤት ማቅረብን ደንግጎ ከአራት ወር በኋላ ፍርድ ቤት ሲቀርብ “ተመስገን” ያለው መሰረት ሳይፈታ፣ ሌሎች በርካታ ወጣቶችን ለማፈን ዛሬ ሌላ አዋጅ ፀድቋል።
እንደ መሰረት አሰፋ ቤተሰቦች ሁሉ፣ ሌሎች እናቶችም በጊዜያዊ አዋጁ ለዘለቄታው ለጠፉት ልጆቻቸው እያነቡ ይሆናል። እንዲያውም ደብዛው ጠፍቷል ተብሎ የሚለቀስለት መሰረት እድለኛ ይሆናል። ሌሎች “መሰረቶች” ወደ ሌላ ሀገር ሌደው ይሆናል ተብለው ዝም ተብለው ይሆናል። ስልክ ደውሎ፣  ላይ ታች ወርዶ የሚጠይቅላቸው፣ ጥቁር ያልተለበሰላቸው፣ ያልተለቀሰላቸው፣ “ፈልጉልኝ” ተብሎ ፎቶ የማይለጠፍላቸው አዋጅ የበላቸው በርካታ መሰረቶች፣ በርካታ ወጣቶች ይኖራሉ።
(ፎቶው ጥቅምት 20/2009 ዓም ታፍኖ ደብዛው ያልተገኘው የመሰረት አሰፋ ነው። በዚሁ አጋጣሚ እስር ቤት ያገኛችሁት፣ አሊያም ስለመሰረት መረጃ ያላችሁ እንድትጠቁሟቸው ይፍልጋሉ)
Filed in: Amharic