>
5:13 pm - Friday April 19, 7782

የደመቀ መኮነን ኦህዴድን መክዳት፤ የለማ ቡድን መነጠል፤ ጠቅላይነቱና ሌሎችም (ሚኪ አማረ)

የለማ ቡድን የባለፈዉን አመት በደንብ ሲያጠቃ የከረመ ቢሆንም አጨራረስ ላይ ከራሱ ጉድለት ወይም ከሌሎች በደረሰበት ክህደት እንደአጀማመሩ የሚያምር አይመስለም፡፡ የእነ ለማ ቡድን ኦህዴድን እንደተረከበ የመከሩት የነበር ኢትዮጵያን ወደፊት ለማስጓዝ ያለ አማራ ህዝብ የማይታሰብ ነዉ ስለዚህም ከአማራ ህዝብ ጋር እና ከብአዴን ጋር መስራት አለብን የሚል ሃሳብ ይዘዉ በደንብ ሁለቱም ድርጅቶች ተደራድረዉበት ከዛም አልፎ ህዝብ ለህዘብ ግንኙነቱን ጀምረዉት ነበር፡፡ ትልቁ የእነ ለማ ስህተት ብአዴንን አማራ ነዉ ብለዉ መሳላቸዉና ሚስጥር ሳይቀር ለብአዴን መንገራቸዉ ነዉ፡፡ ያም ሆኖ የብአዴን ሊቀመንበር ደመቀ መኮነንን በማመናቸዉና አዲስ አበባ በቅርበት በመገኘቱ ኦህዴዶች ብዙዉን ነገር ከሱ ጋር ለመስራት ሞክረዋል፡፡ እነ ገዱና ንጉሱም የኦህዴድን ሀሳብ በደስታ ተቀብለዉት ባህርዳር ድረስ በመጋበዝ ዉይይት እንዳደረጉ ያታወቃል፡፡
የብአዴን ማፈግፈግ/የደመቀ ክህደት
እነ ለማ ጀማሪ ፖለቲከኞች ናቸዉ፡፡ ጀማሪ ስትሆን ambitious ትሆናለህ፡፡ የሚያጨበጭብልህ ይበዛል፤ተቀባይነትህ ይጨምራል፡፡ በዚህ ዉስጥ ግን የፖለቲካን ተንኮል፤አካሄድና conspiarecy አብረህ ጎን ለጎን እየተማርከዉ ካልሄድክ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ደመቀ መኮነን ላይ ኦህዴደዶች ትልቅ እምነት ጥለዉ ነበር፡፡ ኦህዴድም ባላሰበዉ መንገድ የብአዴን በተለይም የደመቀ መኮነን ክህደት ደርሶበታል፡፡ እጅግ የተዳከመዉ ህወሃት ለኦህዴድ ያን ያህል ከባድ አልሆነበትም ነበር ነገር ግን የብአዴን ከህወሃት ጎን መቆም ባላንሱን ሙሉ ለሙሉ ወደ ህወሃት እንዲያዘነብል አድርጎታል፡፡ በእርግጥ የገዱ ቡድን አሁንም ኦህዴድን ቢደግፍም ነገር ግን ገዱና ደጋፊወቹ ከአዲስ አበባ ፖለቲካ የራቁ ስለሆነ ለኦህዴድ የተፈለገዉን ያህል ጫና ባህርዳር ላይ ሁነዉ ማሳረፍ አልቻሉም፡፡ ብአዴን አዲስ አበባ ላይ የተወከለዉ በደመቀ፤ በበረከትና በከበደ ጫኔ (ካህሳይ) ነዉ፡፡  ደመቀ ማለት የበረከት ታዛዠ ነዉ፡፡ በዚህም የተነሳ የደመቀ ክህደት የኦህዴድን aspiration አጨናግፎበታል፡፡ ኦህዴድም በግልጽ ደመቀን እንዴት እንዲህ ታደርጋለህ ያለዉ ሲሆን ክህደት እንደሆነም ተነግረሮተታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴርነቱን ፈልጎም ከሆነ መነጋገርና መደራደር ይቻል ነበር የሚል ቅሬታ አቅርበዉበታል፡፡
አባዱላና ወርቅነህ ገበየሁ
ኦህዴድ ከነዚህ ሁለት ሰወች ይልቅ ብአዴንን አምኖ ነበር ይባላል፡፡ ሁለቱም በማንኛዉም ግዜ እንደሚንሸራተቱ የነ ለማ ቡድን ያዉቃል፡፡ በ17ቱ ቀን ስብሰባ ላይም ይሄ ነዉ የተባለ ለኦህዴድ የሚጠቅም contribution አላደረጉም ነበር፡፡ እንዲያዉም ከነ ኩማ ደመቅሳና ዲሪባ ኩማ የተለየ አቋም አልነበራቸዉም ይባላል፡፡ እነ ድሪባ ኩማ ያለምንም ማወላዳት ከህወሃት ጎን የቆሙ ናቸዉ፡፡ እንዲያዉም ኦህዴዶች ከነ ኩማ ይልቅ ገዱ ኦህዴድን ጠቅሟል ብለዉ ያስባሉ፡፡ ለማና አብይን የድርጅቱንም የአገሪቱንም ህልዉና አደጋ ላይ እየጣላችሁ ነዉ የሚል ክስና ማስፈራሪ ሲደረደርባቸዉ እንዲሁም እናንተን ከማሰር ወደኋላ አንልም ሲባሉ ገዱ የማይታሰብ ነገር ነዉ እያወራችሁት ያለዉ በማለት ተከላክሏቸዋል ይባላል፡፡ አባዱላን በጎን ህወሃት ወደ ድሮዉ ቦታ እንዲመለስና የሚፈልገዉን ስልጣን ጠቅላይ ሚኒስቴርነትን ጨምሮ መዉስድ እንደሚችል አግባብቶታል፡፡ በጎን ደግሞ ደህንነቶች ለለማና ለዶ/ር አብይ የተጻፈ የእስር ማዘዣ ለአባዱላ በድንገት አስመስለዉ በማሳየት ከስልጣን ማግኘት በላይ ያች በድንገትና በተቀነባበረች ሁኔታ ያያት የእስር ማዘዣ ወረቀት አባብታዋለች ተብሏል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስቴርነት ቦታ
ህወሃት ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚኒስቴር እንደማይሆን ምሎ ተናግሯል፡፡ ኦህዴድም ምክትል መሆን እንደማይፈልግ ምራቁን ትፍ ብሎ ምሏል፡፡ ህወሃት አሁንም አባዱላ በባሌም በቦሌም ተብሎ ቦታዉን ቢይዘዉ ፍላጎት አለዉ፡፡ ኦህዴድን በነባር ሰወች ወደ ነበረበት መመለስ ይፈልጋሉ፡፡ አሁን እንደ አማራጭ የተያዘዉ ኦህዴድን በእነ አባዱላ በኩል ወደ ነበረበት መመለስ አለያም አዲስ ኦህዴድ ህወሃት በሚፈልገዉ መንገድ መመስረት ነዉ፡፡ እነ ለማን የማባረር ፍላጎት ሁሉ ከመቸዉም ጊዜ በላይ በህወሃት ቤት አለ፡፡ ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴርነቱ ስንመጣ አሁን የሚጠበቀዉ የአሜሪካ ፍላገት ነዉ፡፡ በሚቀጥለዉ ሳምንት ወደ አዲስ አበባ የሚመጣዉ የአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ፍላጎታቸዉን ያሳዉቃሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ አሁን ባለዉ አሰላለፍ የዶ/ር አብይ ብቸኛዉ ተስፋ የአሜሪካ አስተያየት ነዉ፡፡ ዶ/ር አብይ የማይሆን ከሆነ ምናልባትም ሽፈራዉ ሽጉጤ የተሸለ እድል አለዉ፡፡ ኦህዴድ ደመቀ መኮነንን ካሀዲ ብሎ የተቸዉ ሰዉ በመሆኑ እሱን ይመርጣሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡
የኦሮሞ አክቲቪስቶች/ተቃዋሚዎች
የኦሮሞ አክቲቪስቶች በተወሰነ መልኩ አዲሱን የኦህዴድ ቡድን የደገፉ ቢሆንም ቀስ በቀስ ግን ምናልባትም በትግሉ ይገባኛል፤ በትግሉ አካሄድና እንዲሁም አገር ቤት ያለዉን አሰላለፍ በሚገባ ባለማወቅ ሊሆን ይችላል መፈራቀቅ በመምጣቱ መጀመሪያ አካባቢ የነበረዉ ድጋፍ አሁን ወደ ተቃዉሞ ተቀይሯል፡፡ኦህዴዶችም ብአዴን ብቻ ሳይሆን የራሳችን ሰወች ለህወሃት አሳልፈዉ ሰጡን የሚል ምሬታ እያሰሙ ነዉ፡፡
የፓርላማ መረጃወች
ህወሃት የትናንትናዉን የፓርላማ ምርጫ ለሚዲያወች ክፍት ያደረገዉ ለሁለት ጉዳይ ነዉ፡፡ አንድኛ በፎቶ በማንሳትና በመቅረጽ አዋጁን የደገፉ የፓርላማ አባላትን ለተቃዋሚዉ በማሳየት ከተቃዋሚዉ መነጠልና ሳይወዱ ወደራሱ እንዲመጡ ለማድረግ ነበር፡፡ ሁለተኛ ያልመረጡትን ደግሞ በገሃድ እንዲታዩ በማድረግ ለወደፊት እነዚህ ናቸዉ ያልመረጡት በማለት ለማሸማቀቅና እዛዉ የፓርላማ አባላቱን ደግሞ እርስ በእርስ እንዲሻኮቱና እንዳይተማመኑ ለማድረግ የታለመ ነበር፡፡ እንጅ ህወሃት ይሄ የአዋጅ ጉዳይ አጨቃጫቂ እንደሆነ እያወቀ በዝግ ያካሂደዉ ነበር፡፡ የህወሃት የረዥም ግዜ የፖለቲካ ልምድ እነዚህን የመሳሰሉ ተንኮሎች ለመቀመር አስችሎታል፡፡
የእነ ለማ እጣ ፋንታ
በአሁኑ ሰአት የእነ ለማ ቡድን እንደበፊቱ ነጻነቱ የለዉም፡፡ እራሱ ኦህዴድ ዉስጥ ያሉ ያላጠራቸዉ ሰወች በህወሃት ታግዘዉ በነሱ ላይ ዙረዋል፡፡ ተጽእኖ ያለዉ ብአዴን ክዷቸዋል (ደመቀ መኮነን፤ ከበደ ጫኔና በረከት ስሞን)፡፡ የዉጪዉ የኦሮሞ ተቃዋሚም እንዲሁ ገሸሽ አድርጓቸዋል፡፡ በቀጣይ ሳምንት ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚኒስቴር ካልሆነ ህወሃት ኦህዴድን እንደገና ለመቆጣጠር ወስኗል ማለት ነዉ፡፡ እነ ለማንና ዶ/ር አብይን ገለል በማድረግ እነ አባዱላን፤ አለማየሁ ተገኑንና ደሚቱን የመሳሰሉ ሰወች እንዲይዙት ይደረጋል፡፡ ዶ/ር አብይ ቀንቶት ጠቅላይ ከሆነ ኦህዴድ ቀጣይ እነ አባዱላንና ደጋፊዎቹን ጠራርጎ እንደ እነ ሙክታር የሚያባራቸዉ ይሆናል፡፡ ቢያንስ በአገሪቱ ላይ ያን ያህል ለዉጥ ባያመጡም በራሳቸዉ በኦህዴድ ዉስጥና በኦሮሚያ ክልል ግን የፈለጉትን ከማድረግ የሚያግዳቸዉ አይኖርም ማለት ነዉ፡፡ ክህደት የበዛበት ኦህዴድ  ወደ አጣብቂኝ መንገድ እየገባ ነዉ፡፡ ተላላኪዉን ኦህዴድ ለማየት ብዙም ሩቅ አይመስለኝም፡፡ እነ ለማና ዶ/ር አብይ በዉጪዉ አለምም ስለታወቁ ምንም ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ የእነ ለማ ፓወር ማጣት ግን ከነሱ ጎን ለነበረዉ ታች ላለዉ ካድሬ መጥፎ ዜና ይሆናል፡፡ ከንቲባወች፤ የዞን አስተዳዳሪዎች፤ፖሊስ ኦፊሰሮች፤ የወረዳ አስተዳዳሪወችና ሌሎች ከህዝቡና ከነለማ ጎን ቆመዉ የነበሩ ሁሉ ይለቀማሉ ማለት ነዉ፡፡ እነዚህ ሰወች low profile ስለሆኑ ብዙም የሚያስታዉሳቸዉ አይኖርም፡፡
መልካም ቀን
Filed in: Amharic