>

መንግስት ዮናታን ተስፋዬን "ተሸንፌያለሁ" ብሎ አምኖ ነው የፈታው! (ጌታቸው ሽፈራው)

ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ ሰልፎች ሲደረጉ መንግስት ዜጎችን መግደል ጀመረ። ሰልፍ ወደሚደረግባቸው ከተሞች ሰራዊቱን እስከ አፍንጫው አስታጥቆ ላከ። ዮናታን በዚህ ወቅት ለሕዝብ በግልፅ መልዕክት አስተላለፈ!

መልዕክቱ “ስብሰባ እና ሰልፋችሁን እስክትጨርሱ መንገዱን ዝጉት” የሚል ነበር። ዮናታን ገዳዮች እንዲዘገዩ ያስተላለፈው መልዕክት እንደወንጀል ተቆጠረበት። ክስ ሆኖ መጣ። እሱም “ሕዝብ መሞት ስለሌለበት ማድረግ ያለበት ይህን ነው። ወንጀል አይደለም። አስተላልፌያለሁ። አሁንም አስተላልፋለሁ። መንገድ መዘጋቱ ብቻ አይደለም። ሕዝብን ከጭፍጨፋ ለማዳን ድልድይም ይሰበር፣ ከመንገድና ድልድይ የሚበልጠው የሰው ሕይወት ነው። ድልድዩን ነገ እንሰራዋለን!” ብሎ አምኖ ተከራከረ። ተፈረደበት። እንደገና ክሱ ተሻሽሎ ከተፈረደበት 6 አመት 6 ወር ወደ 3 አመት 6 ወር ተቀነሰ ተባለ። ከዛ ደግሞ “ይቅርታ ጠይቀንና እንፍታህ” አሉት! ዮናታን ስቆ ተመለሰ! ደግመው ጠየቁት፣ አሁንም ስቆባቸው ተመለሰ! አሰንብተው ፈቱት! አሸንፏቸዋልና አሁንም ይስቅባቸዋል!

ዮናታን ዛሬ ከእስር በሚፈታበት ወቅት ከዝዋይ አዲስ አበባ ያለው መንገድ ዝግ ነው።ሕዝብ መንገድ የዘጋው ገዳዮቹ እንዲዘገዩ ነው! ዮኒም ይህን ነበር ያለው። ዮናታን ወንጀል ነው ሲባል ነገም እሰብካለሁ ያለውን መንገድ ሕዝብ ራሱ ይዞታል!

ነገ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይመጣል ተብሏል። ከዚህም ባሻገር ሕዝብ ሱቁን ብቻ ሳይሆን መንገድም ዘግቶ ተቀምጧል። ሕዝብ የያዘው ትግል ዮናታን የተወነጀለበት ነው። ዮናታን እስሩን ጨርሶ ሚያዝያ 18/2010 ነበር የሚፈታው። በዚህ ሁኔታ ነው ሁለት ጊዜ ይቅርታ ጠይቀህ ውጣ የተባለው። እሱ “ወንጀል አልፈፀምኩም፣ ይቅርታ ልጠየቅ የሚገባኝ እኔ ነበርኩ” ብሎ በአቋሙ ፀንቷል። ቢያሰነብቱትም አቋሙን አልቀየረም።

ዛሬ አድማ የተጀመረበት ቀን ነው፣ ነገ ደግሞ የአሜሪካው ባለስልጣን ይመጣል። ዮናታን የተወነጀለበትን ሰላማዊ ትግል ለማስቆም ዮናታን መፍታት የሚዲያም ሌላም ጊዜያዊ ጥቅም ታቅዷል። ይህም መንግስት ዮናታንን በይፋ ይቅርታ የጠየቀው ያህል ይሰማኛል፣ “ፈርም ብልህ አሻፈረኝ አልክ፣ መንገድ ዝጉ ብለሃል ብዬ ባስፈርድብህም አሁንም እየተዘጋ ነው። ተሸንፌያለሁ!” ብሎ እንደፈታው ይሰማኛል!

ያው ሰው ሲያሸንፍ እንዲህ ይስቃል!

Filed in: Amharic