ዶ/ር አብይን በብርሃን ፍጥነት ከማውገዝ ነገሮችን በጥሞና ማየት መቅድም ነበረበት። ለነገሩ ትዊተር እና ፊስቡክ ላይ በየሰኮንዱ መረጃ በመለጠፍ የተጠመደ አዕምሮ ነገሮችን ለማሰላሰል ፋታ ስለማያገኝ፣ አዳዲስ እይታዎችን ማመንጨት ባንችል የሚገርም አይሆንም፤ እኔም እራሴ አንዱ የዚህ በሽታ ተጠቂ መሆኔን መሸሸግ አልፈልግም። ወደ ዋናው ነጥብ ልመለስ-
ዶ/ር አብይ የወሰዱት እርምጃ በ3 ምክንያቶች ትክክል ነው ብዬ አስባለሁ።።
1ኛ በኢህአዴግ ድርጅቶች አሰራር ሁሉም የፓርላማ አባላት ድምጽ የሚሰጡት ድርጅቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ነው፤ ከድርጅቱ ውሳኔ ውጭ እጁን የሚያወጣ አባል እጁን ይቆረጣል። የብአዴን፣ ህወሃትና ደኢህዴን የፓርላማ አባላት በዚህ አሰራር መሰረት እጃቸውን አውጥተው ከመቆረጥ ድነዋል። ኦህዴድ በዚህ የቆዬ መርህ አልተመራም። በኦህዴድ ውስጥ አዋጁን የሚደግፉ ቡድኖች አሉ፣ የሚቃወሙም አሉ። በዚህ ጉዳይ ድርጅቱ ከሁለት መከፈሉ ግልጽ ነው። ስለዚህ ድርጅቱ የወሰደው አማራጭ፣ ሁሉም አንድ አቋም ከሚይዝ በራሱ ስሜት እንዲወስን ማድረግ ነው። እን አብይ ይህን በማድረጋቸው ድርጅቱን ከሁለት ከመከፈል ታድገውታል። የድርጅቱን አባላት ለማጥራትም ፋታ አግኝተዋል። እነ ለማ አንድ አቋም ያላቸውን አባላት እንደማይመሩ መታወቅ አለበት። በዚያ ላይ የህወሃት ረጅም እጅ አለበት።
2ኛ አብይ የድርጅቱ ሊቀመንበር እንደመሆኑ አይኖች ሁሉ እሱ ላይ እንደሚያርፉ ግልጽ ነው። የኦህዴድ አባላትም ሆኑ የሌሎች ድርጅቶች አባላት የአብይን እጅ ማየት በእጅጉ ይናፍቃሉ። አብይ እጁን አውጥቶ ቢደግፍ፣ አዋጁን የሚቃወሙት የኦህዴድ አባላት ተቃውሞ ያሰሙበታል፣ ቢቃወም ደግሞ አዋጁን የሚደግፉት ይቃወሙታል። አጀንዳው መሰረታዊ ለውጥ ከማምጣት ወደ “ሊቀመንበሩ ይውረድ አይውረድ” ንትርክ ይቀየራል። ኦህዴድን ለመግደል የሚያስቡት ህወሃቶችና ደጋፊዎቻቸው ጥሩ የመከፋፈያ አጀንዳ ያገኛሉ። አብይ ይህን አውቆ በጥበብ ማለፉ ብቃቱን እንጅ ካሃዲነቱን አያሳይም። ምንም ቢሆን አብይ ለማን ሳያማክር ይህን ውሳኔ ብቻውን አልወሰነም። እነሱ ደግሞ ከእኛ በተሻለ የሚበጀውን ያውቃሉ። አብይ ይህን በመወሰኑ ለማ ድርጅቱን እንዲያጠራ ጊዜ ገዝቶለታል።
3ኛ አብይ በስብሰባ አዳራሹ ባለመገኘት ተቃውሞውን መግለጹን ልብ ይሏል። እንዲያውም በስብሰባው ባለመገኘት ተቃውሞውን የገለጸበት መንገድ፣ በአዳራሹ ተገኝቶ እጁን በማውጣት ከሚገልጽበት በላይ ጠንካራ ነው። ለምን? አንድ ዝግጅት ላይ የጋበዝከውና ሁሉም አይኑን የሚጥልበት እንግዳህ ሳይገኝ ቢቀር፣ ለአዘጋጁ ክፍል ትልቅ ሃፍረት ነው። እንግዳው ተገኝቶ ድጋፉን ወይም ተቃውሞውን ቢገልጽ ለዝግጅቱ እውቅና መስጠቱን ያሳያል። እንግዳው መቅረቱን ሳያሳውቅ ወይም ይቅርታ ሳይጠይቅ፣ በዝግጅቱ ላይ ሳይገኝ ከቀረ ግን ለዝግጅቱ ያለውን ንቅት ማሳየቱ ነው፤ እንግዳው በዝግጅቱ ላይ ተገኝቶ ስለ ዝግጀቱ ተቃውሞን ከሚገልጽበት በላይ በዝግጅቱ ላይ ባለመገኘት ዝግጅቱን እውቅና መንሳት ይቻለዋል። መንግስታት ጠንካራ ተቃውሟቸውን የሚገልጹትበት አንዱ መንገድ ይህ ነው። ለዝግጅት እውቅና መንፈግ ። ወያኔዎችስ ኢሳት ላይ የማይቀርቡት ኢሳትን እውቅና ላለመስጠት አይደል። ለእኔ እንደሚገባኝ አብይም የተከተለው መንገድ ይህን ነው፤ በአዳራሹ ባለመገኘት አጠቃላይ ዝግጅቱን እውቅና ነስቶታል። ንቀቱን አሳይቷል።
እነዚህ ምክንያቶች ሲደመሩ አብይ በጥበብ ተቃውሞውን ገልጾ ድርጅቱንም ከመከፋፈል ለጊዜውም ቢሆን ታድጎታል። መጪውን ጊዜ አብረን የምናየው ይሆናል፤ የአብይ ውሳኔ በግል ፍላጎት ወይም ጠ/ሚኒስትር ለመሆን በመፈለግ ላይ የተመሰረተ ነው የሚለውን መከራከሪያ ለመቀበል ዳገት ይሆንብኛል። ሰውዬው በስብሰባ ላይ ባለመገኘቱ ህወሃቶች የሚያወርዱበትን የቦንብ ውርጅብኝ ያዬ ሰው፣ ሰውዬው በህወሃት ጫናና ጠ/ሚኒስትር ለመሆን በመፈለግ የወሰነው ውሳኔው ነው የሚለውን መከራከሪያ በፌደራል መርማሪዎች ድብደባ ካልሆነ በስተቀር ለመቀበል ይከብደዋል።