>

የበረከት ቃለመጠይቅ! (ደረጄ ደስታ)

አቶ በረከት ከጥቂት ቀናት በፊት ከኢቢሲ ጋር ያደረጉትን ቃለመጠየቅ እያየኋቸው ሰማሁት። የአገሪቱ ስጋት የገባቸው አልመሰለኝም። ጭንቅ ላይ ያሉ ሳይሆን የግንቦት ሃያ በዓል የተጋበዙ ይመስላሉ። ወሬያቸው ሁሉ የልማትና የዴሞክራሲ ስኬት ነው። ኢትዮጵያ “በሁሉም መስክ አድጋለቸ የዛሬ 25 እና 27 ዓመት በፊት እንደነበረችው አይደለችም..” የሚለውን ደጋግመው ተናግረዋል። በየጥያቄው መካከል ያንን አስረግጠው መደጋጋማቸው “ሰው ይሔን እንዴት ይቃወማል?” ዓይነት አስመስሎባቸዋል። ለነገሩም ቃል በቃል አይሁን እንጂ እሱንም ብለውታል። አሁን ያለው ስጋትና ጥያቄ ኢትዮጵያ አድጋለች ወይስ አላደጋቸም፣ ወይም የት ነበረች ዛሬስ የት ደረሰች? አይደለም። ጥያቄና ስጋቱ እንደሳቸው አድጋለች ተወንጭፋለች ብለው ለሚያስቡትና በዚያው ፍጥነት ተመልሳ ቁልቁል ብትወድቅስ ወይም እሳቸውን የሚቃወሙት እንደሚሉት አሁንም ከወደቀችበት የበለጠ ጠፍታ ጭራሽ ህልውናዋ እሚያከትም ቢሆንስ…? እሚሉ ጥያቄዎች ናችው።

ለጥያቄዎች መልስ ለመስጠት የተቀመጡት በረከት በጣም ተረጋግተውና አንዳንዴም ተለጥጠው፣ አገሪቱን እያናወጠ ያለውን ማዕበል ከአንድ አምስት ደቂቃ በኋላ እንደሚያልፍ የልጆች ጨዋታ አስመስለው ሲያወሩ ማየቱ ያስደነግጣል። እሚያስደነግጠው ግን ሁሉን ነገር እሚያውቁ በማህበራዊ ቲዮሪ የተራቀቁ መስለው መቅረባቸው ሳይሆን ለዚያች አገር ስሜት አልባ ሆነው መታየታቸው ነው። ምንም እንኳ ቀውስና ነውጡ የሳቸው የትግል ፍሬ መሆኑን ጭምር ባንስተውም፣ ምንም እንኳ በሥልጣን እንጂ በአገር ፍቅር ባለቤትነት ባንጠረጥራቸውም፣ እንደዚያ አብጠውና ተከምረው ለሚያወሩበት ምቾታቸው እሚጨነቁ ሆነው አለመታየታቸው ያስገርማል። አልገባቸውም። ጨርሶ አልገባቸውም። ጠ/ሚ ኃ/ማርያም ሥልጣን የለቀቅኩት የመፍትሔው አካል ለመሆን ነው ብለውናል። የእነ በረከትና ስብሐት መፍትሔ ግን ሥልጣን ላይ መቆየት ነው። ምክንያቱም ያቺ አገር ያለነሱ አይሆንላትም።
ዴሞክራሲና ፍትሕን በማስፈን ረገድ ድርጅታቸው በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች እንደሚኮራ ተናገረዋል። አንደኛው ህጋዊና ፖለቲካዊ እምጃዎችን በመውሰዳቸው። ሁለተኛ ተግባራዊና ተቋማዊ እምርጃዎችን በማከናወናቸው ነው። ህጋዊና ፖለቲካዊ ያሏቸው ህገመንግሥቱን የመሳሰሉ ትላልቅ ሰነዶችና ፖሊሲዎችን በማስተዋወቃቸው ነው። ተግባራዊና ተቋማዊ ያሉት ደግሞ እነሱን በሥራ ማዋላቸው ነው። ድርጅታቸው ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እነዚህን ሲተገብር የኖረ በመሆኑ ይኮራሉ። “34ሺ  እሚደርሱ እስረኞችን ፈተን ለቀናል” ብሎ የተኩራራ መንግሥት አጋፋሪ የሆኑት አቶ በረከት ከሚጸጸቱበት የሚኮሩበት እሚበዛ መሆኑን መረዳት ይቻላል። አሁን የተፈጠረው ችግር እንደሳቸው ገለጻ እነዚያን “ታላላቅ” ድሎች ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር ከተፈጠረች ትንሽ “ክፍተት” የመጣች ናት። “ህገመንግሥቱን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ፣ከሚዲያው እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ከነበረን ግኑኝነት አኳያ የታዘብነው ክፍተት አለ።” ብለዋል። ያው እንደ አለቃቸው አቶ መለስ ቃል አስረግጦ መደጋገም ይወዳሉና “የታዘብነው” የምትለዋን ቃል እንደሚረግጡት ህዝብ እያስረገጡ ደጋግመው ተናገረዋታል። ኢህዴግ ድክመቶችን “ይታዘባል” እንጂ አገር እንኳ እሚያጠፉ ቢሆኑ አይደነግጥባቸውም። ጀግና ነዋ! እና ህዝቡ እነዚህን ግብዝ ጀግኖች ተለውጠው ለውጥ ያመጡልኛል ያደምጡኛል ብሎ ተስፋ አድርጎ ከሆነ ድካሙ በከነቱ ነው። ጨርሶ አይገባቸውም። ወይም የኛ ህዝብ አይደለም ብለዋል!!!
አቶ በረከት አገሪቱ የገንዘብ ችግር እንደሌለባትና ትልቅ የፋይናንስ ሴክተር የፈጠረች መሆኗን ገልጸዋል። የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች እሚቀኑባት ታላቅ አገር መሆንዋን ሁሉ እያነሱ እንደ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጉራቸውን ነስንሰዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ገንዘብ እጅግ ብዙ መሆኑን ማንም አይከራከራቸውም። ጥያቄው ገንዘብ የለም ሳይሆን ገንዘቡ ያለው የትና እነማን ዘንድ ነው እሚለው ነው። በአስነጠሳቸው ቁጥር ውጭ አገር እየሄዱ እሚታከሙ የሙስናው ባለሟል ስለ ኢትዮጵያ ገንዘብና ፋይናንስ ብዙ ባይናገሩ ጥሩ ነበር። የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ለምን ተከሰተ? ታላላቅ ፕሮጀክቶች ለምን መጠናቀቅ አቃታቸው? ግለሰቦች ከባንኮች በሚያወጧቸው የገዛ ገንዘባቸው ላይ ሳይቀር ለምን ገደብ ተጣለ? የኢትዮጵያ መድሃኒት አምራች ፋብሪካዎች ሰሞኑን ጥሬ እቃ መግዣ ገንዘብ ስለሌለን ሠራተኛ እየቀነስን ነው ብለው ለምን መግለጫ ሰጡ? የመድሃኒት እጥረት፣ የሲሚንቶ፣ የብረት… የኑሮ ውድነቱ ለምን ተከሰተ? የአባይ ግድብ እየተሠራ ያለበትን ገንዘብ መክፈያ ጠፍቶ ውስጥ ውስጡን ሩጫ ላይ አይደላችሁም? የራስዎ መንግሥት ጋዜጦች እሚጽፏቸውን የመንግስት ሚዲያዎች እሚያወሩትን እየተመለከቱ ነው? በኦሮምያ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እሚያገኘው 40 ከመቶ አይሞላም። አዲስ በየከተሞች መብራት ውሃ እሚቆራረጠው ለምንድነው?  አሁን ጉዳዩና ገዳዩ ሌላ ሆኖ እሚያስተውለው የለም እንጂ 8 ሚሊዮን ረሀብተኞች እርዳታ እሚፈልጉ መሆኑን የራስዎ መንግሥት ነው የገለጸው። በልማት ላበለጸጋችሁ ህዝብ የዳቦ ስንዴ መግዣ እየጨነቃችሁ አይደለም? ባለፈው ጃናዋሪ ከፓኪስታኑ ኩባንያ ለመግዛት ያዘዛችሁትን 400ሺ ቶን ስንዴ ጨረታ ለምን ሰረዛችሁት? 10 ሚሊዮን ዶላር ቀብድ መክፈል አቅቷችሁ አይደለም? ደግሞ ገንዘብ ሞልቶናል!! የርስዎን ገንዘብ የጠየቅዎት የለም – የአገሪቱን ነው!
አቶ በረከት ስለወቅታዊ ሁኔታ ሊናገሩ ሲመጡ ቢያንስ ቁምነገር ያለው ነገር ይናገራሉ ብዬ ነበር። እሚፎክር እሚገበዝ መንግሥት ሳይሆን የገጠመውን ችግር ተገንዝቦ “እኛም የተቻለንን እናደርጋለን እናንተም አግዙን እባካችሁ፣ ተጋግዘንና ተረጋግተን አገራችንን ከቀውስ እናድን!” ይባላል እንጂ የምን መዘባነን ነው? ወደ ጓዶችዎ እንደፈለጉ፣ ወደ ህዝብ ዞረው ሲያወሩ ግን ይጠንቀቁ ብዙ አዋቂ አለ።
እውነት ነው፣ አንዳንዶቹ ወያኔዎች ኤርትራዊ ናቸው ብለው ስለገመቱ ብቻ ቢያጥላሉዎትም የራስዎ ነገር አልዎት። ከዝንጀሮዎቹ ቆንጆዎች መመራረጥ የግድ ከሆነ መቸም ከነ ደመቀ፣ ደብረጽዮንም ሆነ ቀሪዎቹ ይሻላሉ የተባሉት እርስዎ ነበሩ። ምክንያቱም አሁን ስሙን ለማታነሱት ለባለ ራእያችሁ መለስ ዜናዊ ቅርብ ነበሩ። ከአቶ መለስ ሞት በኋላም የኢህአዴጎቹ የቲዮሪ አባትና የርዕዮተ አለም ሊቅ እንደመሆን ይዳዳዎታል፣ ካድሬ ማጥመቂያ ጽሑፎችን ይጽፋሉ እሚባሉት እርስዎ ነበሩ። ሌሎቹ እንኳ በማንበብና በመጻፍ አይጠረጠሩም። እርስዎም ቢሆን ያ የፈጠረብዎት ስሜት ነው መሰል፣ ሲናገሩ ነገሩን ሁሉ አካዳሚክ ማስመሰል ይፈልጋሉ። እስኪ ባዶ ወረቀትና ብዕር ይዘው ከሰጡት ከዚህ ቃለመጠይቅ ምን ፍሬ ነገር እንደተናገሩ አንድ ሁለት ሶስት ብለው ይጻፉ!! ኢህአዴጎች ችግራችሁ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ሊብራሊዝም፣ ዴቬሎፕመንታል ስቴት ኒዮ ሊብራል… ምንትስ የመሳሰሉትን በየአገሩ እየተሞከሩ የወዳደቁ የአይዶሎጂ ነክ ቃላትን ሰብስባችሁ ቀኑን ሙሉ እሱኑ ስታወሩና ስትከራከሩበት ትውላላችሁ። ስለዚህ ዓለም ሁሉ ከሱ ብቻ የተሠራና እናንተም ያወቃቸው የተራቀቃችሁ፣ በፍልስፍና የመጠቃችሁ ይመስላችኋል። ሰዎቻችሁ ሁሉ ጥራዝ ነጠቅ ሆነው የቀሩት ለዚህ ይመስላል። ይሔ አሁን የመጣው ችግር ግን ያ ቤት ዘግታችሁ ያጠናችሁት ዝባዝንኬ ቲዮሪ እሚፈታው ነገር አይደለም። ቁጭ ብላችሁ የሰቀላችሁት ብዙ ነገር አለ። ስለዚህ ወይ አልገባኝም ወይም አያገባኝም ማለት ያባት ነው!!! አንደበትዎንማ ዘግተው ጆሮዎን ከፍተው ቢቀመጡ ደግሞ ለኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ ነበር !!!
Filed in: Amharic