>
5:13 pm - Tuesday April 19, 9983

ከሰርግ ማግስት የ14 ዓመት ፍርድ (ይድነቃቸው ከበደ)

”አባቴን በማጣቴ የማዝነውን ያህል ኢትዮጵያዬን  በማትረፌ እፅናናለሁ ” ኢ/ር ደረጀ ደበበ ተሰማ 

 በፎቶ ላይ የምትመለከቱት ኢ/ር ደረጀ ደበበ ተሰማ ይባላል። ወልደቱ እና እድገቱ አዲስ አበባ ነው። ለእስር ከመዳረጉ በፊት በሙያው አንቱታን ያተረፈ ብርቱ ኢንጂነር ነው። ለስራ ጉዳይ ከሄደበት ዱባይ ጋብቻ ለመፈጸም ወደ አዲስ አበባ በሚመለስበት ወቅት ከቦሌ ኤርፖርት በደህነነቶች ተይዞ ፣ የሰርግ ስነስርዓት እንዲፈጽም የሁለት ቀን ጊዜ ከተሰጠው በኋላ የጋብቻ ስነስርዓት ከፈጸመ ከሁለት ቀን በኋላ ለእስር የተዳረገ ግለሰብ ነው ። በስም የሚታወቁ ፖለቲኮኞች እና ጋዜጠኞች እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሰሞኑን ከእስር መፈታታቸው የሚታወቅ ነው። ይሁን እንጂ እንደ ኢ/ር ደረጀ ደበበ ተሰማ ያሉ በርካታ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች በተለያየ “የመንግስት” እስር ቤቶች መኖራቸው በቅርብ ከእስር የተፈቱ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች በተለያየ መንገድ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ከእነዚህ መካከል አንዱ ኢ/ር ደረጀ ደበበ ተሰማ ነው ።

ኢ/ር ደረጀ ደበበ ፖለቲካ ውስጥ በቀጥታና በስፋት መሳተፍ የጀመረው በ1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት ቀስተ ደመናን ፓርቲ በመቀላቀል ነው። በተለይ አሁን በአገር ውስጥ ከሌሉና የቀስተ ደመና አመራር ከነበሩበት ምሁራን ጋር በቅርበት ይሰራ ነበር። በኋላ ላይ የአ/አ ም/ቤት የቅንጅት አፈጉባሄ ሆና ከተመረጡት ከወ/ሮ ሸዋዬ ኪሮስ (የዶ/ር ታደሰ ብሩ) ባለቤት ጋር በመሆን በርካታ ፓለቲካዊ “ማቀናጀቶችንና ማስተባበሮችን ” እንደከናወነ ፤ በቅርብ ከእስር ለተፈቱት ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና ፖለቲከኛው ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር በእር ቤት በነበራቸው ቆይታ ገልፆላቸው እንደነበር ነግረውኛል ። ኢ/ር ደረጀ ደበበ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ቆይታ ያደረገ ሲሆን በቀጠናው የተከሰሰበት (የግንቦት 7 ) ድርጅት በአመራርነት ወክሎ ተሣትፎ ያደርግ ነበር በሚሊ ተከሶ በ2003 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የ14 ዓመት ፍርድ ተጥሎበታል። ወደ አገር ውስጥ የገባው ለጋብቻ ሲሆን ባለቤቱ የእንግሊዝ ዜግነት ያላት የኢትዮጵያዊ ናት ።

ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በዝዋይ እስር ቤት በነበረበት ቆይታ ስለ- ኢ/ር ደረጀ ደበበ የታዘበውን ሲገልጽ ” ደረጀ ባመነበት ነገር ላይ በስነ አመክንዮ የማስረዳት ከፍተኛ ኅይል የነበረው/ያለው / በአቋሙ ላይ ፈጽሞ የማያወላውል ፤ ሆኖም በጣም ደግ ፣ የዋህና ለአሳሪዎቹ ሳይቀር ልባዊ ሐዜነታ የሚያሳይ የጀግንነት ሚዛን ነው ” በማለት ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ምስክርነቱን ይሰጣል። ኢ/ር ደረጀ ደበበ ትልቅ ሰብዕናና ፖለቲካዊ አቅም ኖራቸው ልታይ ልታይ ከማይሉ ልሂቃን (Shadow elite leader) አንዱ ነው በማለት፤ ኢንጂነሩን በዝዋይ እስር ቤት በቅርብ የሚያውቁቱ ተፈቺዎች ስለእሱ የናገራሉ ። የእስር ቆይታውን ያሳለፈው በቃሊቲ ሆነ በዝዋይ በጨለማ ቤቶች ሲሆን በደረሰበት በርካታ ጫናዎች ለከፍተኛ የስኳር ህመምና የደም ግፊት በሽታ የተዳረገ ሲሆን በተለያየ ጊዜያት ራሱን እየሳተ በለሊት የህክምና እርዳታ እንዲደረግለት የእስር ቤት በሮችን ማንኳኳት የተለመደ ተግባር እንደነበር ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና ፖለቲከኛው ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር ትውስታቸውን ይገልፃሉ።

ስለ ኢ/ር ደረጀ ደበበ መናገር ስለ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የመናገር ያህል ለልቤ ደስታን የሚሰጠኝ ሰው ነው። የሚለው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ገጠመኞን ሲገልጽ የኢ/ር ደረጀ አባት አቶ ደበበ ተሰማ እሱን ሊጠይቁ ዝዋይ እስር ቤት ሄደው በጠየቁት በሦስተኛው ቀን በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ ። ጋዜጠኛ ውብሸት ስለ ሁኔታ ሲገልጽ ” ደረጀ ለአባቱ ከነበረው ቀረቤታ እና ፍቅር አንፃር በወቅቱ የተሰማውን ሃዘንና የተናገረውን ቃል አልረሣውም [ አባቴን በማጣቴ የማዝነውን ያህል ኢትዮጵያዬን በማትረፌ እፅናናለሁ ] ነበር ያለው። የእሱ ሞራል መነካት በሌላው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይኖረው ነበር የሱ ጭንቀት” በማለት ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በቁጭት እና በሃዘን የእስር ቤት ገጠመኙን አካፍሎኛል። ኢ/ር ደረጀ ደበበ አሁን ላይ በዝዋይ እስር ቤት ይገኛል። ኢ/ር ደረጀ ደበበ በመታሰሩ የሞራል ልዕልናና ፣ታሪካዊ መሰዋዕትነትን እየከፈለ እንደሆነ ፣ በእስር ቤት በተደጋጋሚ እሱ እራሰ እየገለጸ ቢገኝም ፤የእስር ጦስ ይዞ የሚመጣው ነባራዊ እውነት ብዙ ነገር ነው። አሁን ላይ ማንሳት የማያስፈልጉ ማህበራዊ/ቤተሰባዊ/ ምስቅልቅሎች እንደገጠሙት ይነገራል ። ከዚህ ጽሁፍ ጋር ለመያያዝ የተሞከረው ፎቶግራፍ እጅግ በጣም አድካሚ በሆነ መንገድ የተገኘ ነው ፤ ለዚህም ነው ፎቶው ጥራት የጎደለው ። ይህ ከኢ/ር ደረጀ ደበበ ከ100 ገጾች የመጀመሪያ ገጽ ላይ ያለው ብቻ ነው።

Filed in: Amharic