>

"አሜሪካኖች የተለሳለሰ ሽግግር ይፈልጋሉ፤ ወሳኙ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኃይሎች ናቸው"  (ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ)

በኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌን ተከትሎ የአሜሪካ ኤምባሲ ባልተለመደ መልኩ ጠንከር ያለ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። ከዚያ በመቀጠል ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሬክስ ቲለርሰን በኢትዮጵያ ለዓመታት ስለዘለቅው ተቃውሞና በሃገሪቱ ስላለው የፖለቲካ ሁኔታ ከባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር ሃገር ውስጥ ገብተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጉብኝት በተመለከተ  ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ እንደሚሉት አሜሪካን የመሰሉ ሀያላን ሀገራት ከአሁን በፊት ዲሞክራሲያዊ ማሻሻያ አድርጉ፣ ሰብአዊ መብት ጠብቁ፣ የንግግር ነፃነት አክብሩ እንደሚሉ አስታውሰው አሁን ግን በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ቀውስ እንዳሳሰባቸው መታዘባቸውን ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የውጭ ግንኙነት መምህር የሆኑት አቶ አዳነ አለማየሁም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ። አሜሪካውያን ብሄራዊ ጥቅማቸውን ማስከበር ይፈልጋሉ የሚሉት አቶ አዳነ የሁለቱ ሀገራት የአሁኑ ውይይት ይህንን አድርጉ የሚል የአዛዥ ወይም የአለቃ አይነት ውይይት ይኖራል ብለው እንደማይጠብቁ ያስረዳሉ።
አሜሪካውያኑ በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ባይገቡ ደስ ይላቸዋል የሚሉት ፕሮፌሰሩ መድሃኔ ደግሞ ኢትዮጵያን እንደ ሸሪክ ስለሚቆጥሯት አሁን የተፈጠረው ጉዳይ እጅጉን አሳስቧቸዋል ይላሉ።
የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ሀገራትን ስንመለከት ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ ከወጣ እንደ ሰደድ እሳት መስፋፋቱ ስለማይቀር ያሳስባቸዋል ሲሉም ያክላሉ አቶ አዳነ።
ፕሮፌሰር መድሃኔ በበኩላቸው በአካባቢው የየመን መፍረስ፣ የሶማሊያ የፀጥታ ጉዳይ፣ የደቡብ ሱዳን አለመረጋጋትን የመሳሰሉ የአፍሪካ በርካታ ችግሮች ስላሉ ከአሜሪካ ጥቅም አንፃር ተመልክተው የኢትዮጵያ ጉዳይ በከፍተኛ ደረጃ ያሳሰባቸው ይመስላሉ ብለዋል።
አቶ አዳነም የቴለርሰን መምጣት በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ውጤቱ ወዲያውኑ የሚታይ ይሆናል ብለው ባያምኑም፤ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን አለመረገጋት ከቀጠናው ሀገራት ሁኔታ ጋር በማያያዝ ማየት እንደሚቻል ግን ይናገራሉ።
የፕሬዝዳንት ትራምፕ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በዲሞክራሲያዊ ሽግግር ላይ ያተኮረ አይደለም የሚሉት ምሁራኑ፤ የትራምፕ አስተዳደር ቅድሚያ አሜሪካ የተሰኘ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይዞ እንደሚንቀሳቀስ ማስታወስ ያስፈልጋል ይላሉ። እንደ ፕሮፌሰር መድሃኔ ከሆነ አሜሪካውያኑ የሚያዩት ጥቅማቸውን ነው።
የሀገራት መፍረስ ለሽብርተኝነት እና ለአክራሪነት መስፋፋት መንገድ ይከፍታል ብለው ስለሚሰጉ በአፍሪካ ሀገራት ሰላማዊ የሆነ የተረጋጋና የተለሳለሰ የፖለቲካ ሽግግር ቢኖር ይመርጣሉ ሲሉም ያክላሉ ፕሮፌሰር መድሃኔ።
አቶ አዳነም ሆኑ ፕሮፌሰር መድሃኔ እንደሚሉት የትራምፕ አስተዳደር ፖሊሲዎች በሰብአዊ መብት እና የህግ የበላይነት የሚያሳስበውና የሚያስጨንቀው አይደለም። ነገር ግን የቀጠናው ሀገራት ያሉበትን ሁኔታና አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር እንዳሳሰባቸው በግልፅ ይታያል ብለዋል።
አቶ አዳነ አክለውም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ፖሊሲ ስንመለከት ሁለት ገፅታ አለው ይላሉ። አንደኛው አሜሪካ በአፍሪካ ላይ ያላትን ፖሊሲ እና አሜሪካ በፀረ ሽብር ትግሉ ላይ ያላት ፖሊሲ ነው። ይህም አሁን ለቴለርሰን መምጣት እንደ ሰበብ ሊሆን ይችላል ሲሉ ይናገራሉ።
ስለዚህም የትራምፕ አስተዳደር የውጭ ጉዳዩን የሚያካሄድበት ፖሊሲን ሳይሆን፤ በአፍሪካ ቀንድ ደህንነት እና ፀጥታ ላይ ብቻ ያተኮረው ግንኙነት ላይ ለውጥ እንዳደረገ ያሳያል ይላሉ። ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት ያስቀመጡት ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ላይ የአሜሪካ መንግሥት አቋም የተለሳለሰ እንደነበር ነው።
በተጨማሪም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጠንከር ያለ ተፅእኖ መፍጠራቸውንም ሊያሳይ እንደሚችል አቶ አዳነ ይናገራሉ። የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሪፖርቶች ጉዳዩን የበለጠ አፅንኦት እንዲሰጡት እንዳደረጋቸውም ያምናሉ።
ለፕሮፌሰር መድሃኔ ከዚህ ጉብኝት የተለየ የሚያመጣ ትርፍ የለም። ኢትዮጵያ ለአሜሪካ በአካባቢው ዋነኛ አጋር አገር ናት፤ የትራምፕ አስተዳደር አፍሪካን በተመለከተ የተለየ ፖሊሲ አልቀረፀም ሰዎችም አልመደበም ይላሉ። በመቀጠልም የትራምፕ አስተዳደር የሚያሳስበው ንግድ እና አክራሪነት ነው።
የኢትዮጵያን አጋርነት ስለሚፈልጉት በዚህ አንፃር መነጋገር እና መግባባት ነው የሚፈልጉት የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ከዚህ በተረፈ የተለሳለሰ የፖለቲካ ሽግግር ቢኖር ይፈልጋሉ እዚህ ላይ ደግሞ ወሳኙ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታና ኃይሎች ናቸው በማለት ሃሳባቸውን ያጠቃልላሉ።

Filed in: Amharic