>
5:30 pm - Sunday November 1, 4218

የነሳምሶን ማሞ አገር (ዳዊት ሰለሞን)

ሸገር ኤፍኤም አንዳንድ ነገሮች በተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራሙ የአክሰስ ሪልስቴት መስራች የሆኑትን አቶ ኤርሚያስ አመልጋን በማቅረብ አክሲዮን ማህበሩንበተመለከተ አነጋግሯቸዋል ።
ኤርሚያስ ማህበሩን ችግር ውስጥ የዘፈቁትን ዐበይት ጉዳዮች ለመዳሰስ የሞከሩ ሲሆን ነጥቦቹንም ለመዘርዘር ሞክረዋል ።
ባለሐብቱ የችግሩ መባባሻ ዋነኛ ምክንያት ኢትዮ ቻናል የተባለው የአቶ ሳምሶን ማሞ ጋዜጣ መሆኑን በመጥቀስ “የጋዜጣው ባለቤት የ350.000 ቤት ከእኛ ጋር ገዝተዋል ።እኔ ወደ አሜሪካ እንደሄድኩም የእኔ ምክትል ለነበረ ሰው ደውለው አሁኑኑ አንድ ሚልዮን ብር የማትሰጡኝ ከሆነ በጋዜጣ የማደርገውን አውቃለሁ በማለት መዛታቸውን ግለሰቡ ነገረኝ ።እኔም ዝምብሎ ነው ምንም ሊያደርግ አይችልም አልኩት ።በሳምንቱ ግን በጋዜጣው የእኔን ፎቶ በማስደገፍ አንድ ቢልየን ብር ይዞ ተሰወረ የሚል ሰፊ ዘገባ ሰራብኝ ።ይህንን ዘገባ ተከትሎ ቤት ገዢዎቻችን ተራበሹ።ጉዳዩ በዚህ ቢያበቃ ጥሩ ነበር ።አንድ ቀን ይሄው የእኔ ምክትል ከቢሮ ሲወጣ አንድ ሽጉጥ የታጠቀ ሰው መሳሪያውን ደግኖበት ገንዘቡን ትከፍላለህ እያለ ሲያስፈራራው ግርግር በመፈጠሩ ደህንነቶች ሁለቱንም ይዘው ወረዳ ስድስት ፖሊስ ጣቢያ ወሰዷቸው ።ታጣቂው ለወረዳው በአቶ ሳምሶን የተላከ መሆኑን ተናግሯል ።ክስ ተመስርቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ለህይወቱ በመስጋቱ ክሱን አቋርጧል” ።በማለት ተናግረዋል ።
ጋዜጠኞች ለወህኒ ፣ለስደትና ለተለያዩ ችግሮች በሚዳረጉባት ኢትዮጵያ እነሳምሶን ማሞ ግብር ሳይከፍሉ ቢታሰሩ እንኳን ከእስር ቤት በቀጭን ትዕዛዝ በለሊት ይወጣሉ ፣ጨረታ የሚባል ነገር ሳይጎበኛቸው ታላላቅ ዝግጅቶችን በጓሮ በር ይወስዳሉ ፣ለጋዜጣቸው የሚሆን ማስታወቂያ የቢሯቸውን በር አንኳኩቶ ይጎርፋል አልፈው ተርፈውም ጋዜጣቸውን መደራደሪያ በማድረግ ሽጉጥ ታጣቂ ጭምር ያሰማራሉ ።ታዲያ ይህች አገር የእነሳምሶን አይደለችምን?
Filed in: Amharic