>

በእኔ እምነት ኢትዮጵያ በመንታ መንገድ ላይ ትገኛለች - የተስፋ እና የስጋት (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)

ዛሬ መጋቢት 1/2010 ዓ. ለወጣው ውይይት መፅሄት ኢትዮጵያን በሚመለከለት የት ላይ ነን?፣ ወዲት እየሄድን ነው?፣ ምን ይሻላል እና የምሁራኑ ሚና ምን መሆን አለበት ለሚሉት ጥያቄዎች የሠጠውን መልስ ክፍል 1 ተጋብዙልኝ፡-
ውይይት፡ የት ላይ ነን?
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ : በእኔ እምነት ኢትዮጵያ በመንታ መንገድ ላይ ትገኛለች፡፡ እነዚህ መንገዶች አንደኛው የስጋት መንገድ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የተስፋ መንገድ አንደሆነ ይታየኛል፡፡ የስጋት መንገዶቹ በርካታ ቢሆንም በዋናነት መገለጫዎቹ ዘውግ ተኮር መፈናቅሎች እየተበራከቱ መምጣታቸው ነው፡፡ ይህ የማፈናቀል ፖለቲካ የአገሪቱን ስጋት ተኮር የቁልቁለት መንገድ አክፍቶታል፡፡ ሌላኛው የአገሪቱ የስጋት መንገድ መገለጫ የኢኮኖሚ ድቀቱ ሲሆን፤ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ተጨማሪ የስራ እድል መፍጠር ተስኖት ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ያሳየው ድቀት ተጨማሪ ማህበራዊ ቀውሶችን እየፈጠረ ይገኛል፡፡ የኑሮ ውድነቱ ማሻቀብ፤ ተስፋ አልባ ማህበረሰብ እየበዛ እንዲሄድ አድርጓል፡፡ በውጭ ምንዛሬ እጥረት የተነሳ ፋብሪካዎች የምርት መጠናቸው መቀነሳቸው፤ በግዜ ሄደት የፋብሪካ ሰራተኞች ሊበተኑ እንደሚችሉ ፍንጮች መታየታቸው እንዲሁም ከሕዝባዊ ተቃውሞው ጋር ተያይዞ የውጭ ንግዱና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንቱ መዳከሙ የአገሪቱን የፖለቲካል ኢኮኖሚ ቅርቃር ውስጥ ከቶታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የዜጎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር (ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አንቅስቃሴና ሃይማኖታዊ ጉዞወች ወዘተ..) መብት ዋስትና መጥፋቱ አገሪቱን ወደ መፍረስ ጠርዝ እየወሰዷት ያሉ የስጋት መንገዶች ናቸው፡፡
ሌላኛው ጫፍ የመንታ መንገዱ አቅጣጫ የተስፋ መንገዱም ይታይበታል፡፡ ትልቁ የተስፋ መንገድ በአገሪቱ የፖለቲካ አደባባይ ላይ የፖለቲካ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ ብሔራዊ ፍርሃት ተሰብሯል፡፡ ጥንቃቄ የሚያሻቸው ቢሆንም ወጣቶቹ በአስክሬን ላይ እየተራመዱ የማለፍ ድፍረት ተላብሰዋል፡፡ ሌላኛው የአገሪቱ የተስፋ መንገድ በዝግ-በረኝነቱ የምናውቀው ሕወሓት መራሹ የኢሕአዲግ አገዛዝ ፈርዖናዊ እብሪቱ በረድ ብሎለት እንኳን ሊፈታቸው ቀርቶ ቢረሽናቸው እንኳ የማይረካባቸውን የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን በህዝብ ሃይልና ግፊት ለመፍታት ተገዷል፡፡ በዚህ ሂደት አገዛዙ የሚያስመስልበት ድራማዊ ፖለቲካዊ ሞገስ ርቆታል፤ ካባው ተገፏል፡፡ አለኝ የሚለው ማህበራዊ መሰረት ተሸርሽሮ ቀፎው ቀርቷል፤ በደህነነቱና በመከላከያው ክንፍ ላይ ብቻ ተንጠልጥሏል፡፡ ከምዕራባዊያን ጋር ያለው ግኑኝነትም ቢሆን ሻክሯል፡፡ ባልተለመደ መልኩ የሃያላኑ አገራት የአሜሪካና የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተከታታይ አዲስ አበባ መምጣት የጫናውን ልክ ያሳያል፡፡ በሌላኛው ጠርዝ፤ በልዩነት ውስጥም ቢሆን የዲያስፖራው (በተለይም ኢኮኖሚያዊ) የሀይል ሚዛን ወደ አንድ ጥግግት እያሳየ መምጣቱ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ዶላር በህጋዊ መንገድ መላኩን መቀነሱ ከአገር ቤቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር ተያይዞ የለውጡ ተስፋ ፈንጣቂ ሆኗል፡፡ እነዚህን መሰል ተመጋጋቢ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ለአገዛዙ ራስ ምታት ሲሆኑ፤ ህዝቡን ለሰሞነኛ ፈተና ቢዳረጉትም የለውጥ በር ክፉኛ መዶሻዎች መሆናቸው አሌ አይባልም፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በመንታ መንገድ ላይ ነች የምለው፡፡
Filed in: Amharic