>
5:13 pm - Sunday April 18, 3097

እንደ አባዱላ ሂሳብ፣ ሽጉጤም አማርኛ ተሳስተዋል?! (ደረጀ ደስታ)

የመንግሥት ሚዲያዎች የኢህአዴግ ምክር ቤት “የኢሕአዴግ ሊቀመንበር እንደሚመርጥና በኢሕአዴግ አሠራር መሠረት ሊቀመንበሩ ጠ/ሚኒስትር እንደሚሆን አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ገልጸዋል፡፡” ብለው ነበር። አሁን ደግሞ ዛሚ ሬዲዮ ላይ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ፍጹም ብርሃኔ አቶ ሺፈራው ሽጉጤ ያሉት ሀሳብ ፍጹም ስህተትና ከድርጅቱ ህገ ደንብና አሰራር ውጭ ነው ብለዋል። የኢህዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ እንዲሁም ከ4ቱ ድርጅቶች የደቡብ ሊቀመንበር የሆኑት፣ በዚያ ላይ ለጠ/ሚርነትም የተጠረጠሩት አቶ ሽፈራው እማያውቁት ህገ ደንብ መኖሩ አስገርሟል። ነገ አባባላቸው በአማርኛ ስህተት የመጣ መሆኑ ሰበር ዜና ቢሆንብን መዘጋጀት ነው። ፍሬ ነገሩ ዛሬ ስብሰባ የተቀመጠው ሥራ አስፈጻሚ  የጠቅላይ ምኒስትርም ሆነ የድርጅቱን ሊቀመንበር የመምረጥ ሥልጣን የሌለው መሆኑም ተነግሮናል። ከእንቅልፋችን እስክንነሳ ህገደንቡ ካልተቀየረ ለዛሬው ከተነገረን እነዚህን ይዘናል።
• የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው ታኅሳስ ወር. ግምገማ አካሂዶ ነበር።
• በግምገማው  4ቱ ድርጅቶች በተናጥል ምን ማድረግ እንዳለባቸው ውሳኔ አሳልፏል።
• በአሁኑ ስብሰባ ድርጅቶቹ ውሳኔውን ከምን እንዳደረሱት ይገመግማል።
• በግምገማው ከተስማማ ለኢህአዴግ ሊቀመበርና ጠ/ሚ እጩዎች ላይ ይነጋገራል።
• ለምክር ቤቱ እሚቀርቡ 3 እጩ ጠ/ምኒስትሮች ላይም ይመካከራል።
• በቀጣዩ 180 አባላት ያሉት የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ይጠራል።
• ከምክር ቤቱ ከግማሽ በላይ ከተገኙ ምዕላተ ጉባኤው የተሟላ ይሆናል።
• ምክር ቤቱ የኢህአዴግ ሊቀመንበርን ይመርጣል።
• ከ180ዎቹ ቢያንስ 60 ድምጽ ያገኘ አባል የጠ/ምኒስትር እጩ ሆኖ ይቀርባል።
• ም/ቤቱ በጠ/ሚር እጩዎች ካልተስማማ የራሱን እጩዎች ሊጠቁም ይችላል።
• አሸናፊ ሆኖ የወጣው ግለሰብ ለፓርላማው ቀርቦ ጠ/ምኒስትር ይባላል።
• ጠ/ሚ/ር ሌላ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ደግሞ ሌላ ሰው ሊሆንም ላይሆንም ይችላል።
ስለዚህ የአቶ ኃይለማርያምን ራዕይ እሚያስፈጽመውና ህዝባዊ አመጹን ቀጥ ለጥ ሊያደርግ በሚችለው ቀጣዩ ጠቅላይ ምኒስትር ማንነት ህዝቡ ይገረማል። የኢትዮጵያም ህዝብ እስከዛሬ ድረስ በታሪኩ አይቶ እያማያውቀው በመሆኑ ትልቅ “ሰርፕራይዝ” ሊሆን መቻሉ ፍንጭ እየተሰጠን ነው። ቀላጤዎቻቸውም በእስካዛሬው ግምታችን ውድቅ መሆን ከወዲሁ እየተደሰቱ ይመስላል። እኛማ ወግ ደርሶን ይሄ ቢሆን ያ ቢሆን ማለታችን፣ መቸም ያው ከምናምንቴያቸው አይወጡም ለማለት እንጂ የሌላቸውን ደህና ሰው አምጠው ይወልዳሉ ብለን አልሰጋንም። እኛማ በትንቢታችን ማንንም ብታመጡም አታመልጡም እያልን ነው። ይልቅ ሰው እንጂ ጊዜ መግደል እማታውቁ አስቸኳዮች ሆናችሁ ምን ያንቀረፍፋችኋል?! ያው እንደ ሕጻን ልታሞኙን ስለሚያምራችሁ አሻንጉሊታችሁን ስጡንና እንጫወትበት።  ለሰቆቃው ፋታ ይሰጠን ይሆናል እያልን ነው!
Filed in: Amharic